Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ምዕራቡ ደካማ ዓብይን ነው የሚፈልገው›› አቶ ገብርኤል ንጋቱ፣ የአትላንቲክ ካውንስል ከፍተኛ ባልደረባ

አቶ ገብርኤል ንጋቱ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክና የዓለም ባንክ የመሳሰሉ ተቋማት የሠሩና እየሠሩ የሚገኙ የተመሰከረላቸው የፖሊሲ አማካሪ ናቸው፡፡ አቶ ገብርኤል የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊና ፕላኒንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢኮኖሚ ጥናት ላይ ትኩረት በማድረግ በሕዝብና ዓለም አቀፍ አስተዳደር፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ልማት ከፕትስብረ ዩኒቨርሲቱ አግኝተዋል፡፡ በሐርቫርድና በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሁ ተጨማሪ ትምህርት ወስደዋል፡፡ ከ25 ዓመታት በላይ ከፍተኛ የፖሊሲና የፕሮግራም አመራር ልምድ ያላቸው አቶ ገብርኤል፣ እ.ኤ.አ. በ2019 እስከሚያበቁ ድረስ በአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ክልላዊ ልማት ዳይሬክተር ጄኔራል በመሆን ለዓመታት አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በአሜሪካ እ.ኤ.አ. ከ1961 ጀምሮ በሥራ ላይ የቆየው የጥናትና ምርምር ማዕከል የሆነው የአትላንቲክ ካውንስል ከፍተኛ ባልደረባም ናቸው፡፡ አሁን በዓለም ባንክ አማካሪ የሆኑት አቶ ገብርኤል የተለያዩ አገሮችን ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ግጭቶችን የተመለከቱ በርካታ ጽሑፎችንም አበርክተዋል፡፡ አቶ ገብርኤል ንጋቱ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ግጭትን በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ካሉ ዓለም አቀፍ ፍላጎቶች ጋር በማስተሳሰር፣ እንዲሁም የጦርነቱን የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚና የሰብዓዊ ኪሳራዎችን በማንሳት ከብሩክ አብዱ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተዘጋጅቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ንግግራችንን ለመጀመር የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለምን ይኼንን ያህል ትኩረትን ከዓለም አቀፍ ኃያላን አገሮች ሊስብ ቻለ የሚለውን ብናነሳ ወደድኩ፡፡ እነዚህ ፍላጎቶች መቼ ነው መፈጠር የጀመሩት? እነዚህ አገሮችስ ከዚህ ቀጣና ምንድነው የሚሹት?

አቶ ገብርኤል– እንግዲህ ጥያቄው ለምንና መቼ የሚል ነውና ለምን በሚለው እጀምራለሁ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለምዕራቡም ሆነ ለምሥራቁ ዓለም እጅግ ወሳኝ የሚባል ሥፍራ ነው፡፡ ቀጣናውን ብትመለከት፣ ከግብፅ የስዊዝ ቦይ (Suez Canal) ይነሳና በቀይ ባህር አርድጎ ወደ ህንድ ውቅያኖስ የሚወርድ ብቸኛው የአውሮፓና የእስያ መገናኛ የውኃ ላይ መንገድ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የዓለም የነዳጅ ግብይት በዚህ መስመር ይተላለፋል፡፡ ቀጣናው ከፍተኛ የሆነ የዓለም የነዳጅ ንግድ መተላለፊያ የሆነ ጠባብ ማነቆ ባብ ኤል መንደብ የሚባል ከጂቡቲ ጠረፍ ጥቂት ራቅ ብሎ የሚገኝ ሥፍራም አለው፡፡ ይኼንን ማነቆ የሚቆጣጠር ማንኛውም አካል የአውሮፓንና የእስያን ንግድ ይቆጣጠራል፡፡ አርባ በመቶ ያህል የአውሮፓና የእስያ ንግድ በዚህ ሥፍራ የሚተላለፍ ስለሆነ የባህር ሎጂስቲክስ ጠቀሜታ ያለው አካባቢ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅና በተወሰነ ደረጃ በአውሮፓ መካከል የሚገኝ ስትራቴጂካዊ ቀጣና ነው፡፡ በቀይ ባህር የአፍሪካ ወገን ቆመህ አሻግረህ ብትመለከት ሳውዲ ዓረቢያን፣ የመንን፣ እንዲሁም እስራኤልንና ግብፅን ጨምሮ ሰፊውን የዓረብ ዓለም ማየት ትችላለህ፡፡ አፍሪካንና መካከለኛውን ምሥራቅ የሚያስተሳስር ሰርጥ አልያም ድልድይ የሆነ ሥፍራ ነው፡፡ በዚህ ስትራቴጂካዊ ቀጣና ምክንያት፣ በርካታ የምዕራቡ እንዲሁም የዓረቡ ዓለም አገሮች ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ከጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶች ጋር እንዲሁ በተሳሰረ በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ወደ ምሥራቅ ፊቱን አዙሮ ቀይ ባህርን የሚመለከት መሬት መያዝ፣ ለአብነት የወታደራዊ ካምፕ አልያም የባህር ኃይል ማረፊያ ካለ የዓለም አቀፍ የባህር ላይ እንቅስቃሴን መቆጣጠር ያስችላል፡፡ በዚህ አካባቢም ነው የበርካታ ኃያላን አገሮች የባህር ኃይሎች ላይ ታች ሲሉ የሚታዩት፡፡ አምስት ወይም ስድስት የተለያዩ አገሮችን የባህር ኃይል የያዘችውን ጂቡቲን ተመልከት፡፡ ይኼ ለዚህች መሰል ትንሽ አገር እጅግ ብዙ ነው፡፡ ሆኖም ጂቡቲ በባብ ኤል መንደብ ጫፍ ላይ የምትገኝ አገር ስለሆነች ሁሉም የባህር ኃይሉን የሚያደራጅበትን መሬት ይሻል፡፡ የኤርትራን አሰብ ደግሞ ተመልከት፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባው የሩሲያ የባህር ኃይል ካምፕ አሁን ከባህሩ ወዲያ ባለችው የመን፣ በሁቲዎች ላይ የአየር ጥቃት ለመሰንዘር በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል፡፡ ከላይ ወደ ሰሜን ደግሞ ሱዳን አለች፣ ቱርኮች በሱአኪን ደሴት መሬት ለማግኘት እየጣሩ ነው፡፡ በተመሳሳይ ኳታርም ያንን ሥፍራ ለመቆጣጠር ትሞክራለች፡፡ ሩሲያም በዚህ አካባቢ የውኃ አካላት ላይ የባህር ኃይሏን ለማኖር አንዴ ስምምነት ስታደርግ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስትሰርዝ ቆይታለች፡፡ ይኼንን ማድረግ የእነዚህ አገሮች ሰርጓጅ መርከቦች በማንም ሳይታዩ አልፈው መጥተው፣ ነዳጀ ሞልተው መውጣት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባህር አካባቢ ኑባሬ ማግኘት የኢኮኖሚ፣ የጂኦ-ስትራቴጂክ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ምክንያቶች አሉት፡፡

ይኼ ፍላጎት መቼ ጀመረ ስንል ደግሞ እኔ ሁሌም የነበረ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሆኖም ግን የፍላጎቶች ጉልህነት ሲዋዥቅ ቆይቷል፡፡ የስዊዝ ቦይ ከመፈጠር ጀምሮ፣ ቦዩን የፈጠሩት ፈረንሣይና እንግሊዝ አውሮፓን የሚያገናኝ መስመር ነው የገነቡት፡፡ ይኼም ነጥብ መቀይር የሆነ ይመስለኛል፡፡ ቀጣናው ሁሌም የንግድ ቀጣና የነበረ ሲሆን፣ የቅመም ንግድ የሚያከናውኑ ህንዳውያን፣ ዓረቦችና አፍሪካውያን በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ ላይ ታች እያሉ በየብስ እስከ ታንዛኒያ፣ ዛንዚባር፣ እንዲሁም ሞዛምቢክ ድረስ፣ በዚያኛው ወገን ደግሞ እስከ ህንድና ኦማን ድረስ የዘለቀ ንግድ ነበራቸው፡፡ የህንዳውያ የቅመም ንግድና ተያያዥ እንቅስቃሴዎች ለመቶዎች ዓመታት ሲከናወን ነበር፡፡

ሆኖም፣ የቅርብ ዓመታት የፍላጎቶች ማየል የመጣው መጀመርያ በስዊዝ ቦይ መከፈት፣ ሁለተኛ ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ በታየው አለመረጋጋት ነው፡፡ ለአብነት በቅርቡ በሳዑዲ ዓረቢያና በኳታር መካከል አለመግባባት ተከስቶ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱን ወገን የሚደግፉ እንደ ቱርክ ያሉ አካላት በምሥራቅ አፍሪካ መርገጫ ለማግኘት ሲጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወዲህ ያለ ቁልፍ የውኃ ላይ መተላለፊያ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ዓረቦቹና ኢራን፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በየመን ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ቀጣናውን እጅግ ይፈልጉታል፡፡ እንደሚባለው የየመን የሁቲ ታጣቂዎች የሚደገፉት በኢራን ነው፡፡ ስለዚህም ዓረቦቹ በቀይ ባህር ያላቸውን ፍላጎት ሲያጎሉ ተስተውለዋል፡፡

አዳዲሶቹ ኃያላን እየሆኑ ወደመጡት ቻይናና ሩሲያ ስንመለከትም፣ ለቀጣው ያላቸው ፍላጎት ይታያል፡፡ ቻይና የአፍሪካ ቀንድን ወደ አፍሪካ አኅጉር መግቢያ አድርጋ ነው የምትመለከተው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ የመዝለቂያ በር አድርገው ይመለከታሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ትልቅ ፍላጎት አላቸው፡፡ ሩሲያ ደግሞ እዚሁ ቆይታለች፡፡ በ1970ዎቹ የሶማሊያውን ዚያድ ባሬ ሲደግፉ ነበር፡፡ በኋላም ወገን ቀይረው በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ጊዜ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ሲደግፉ ነበር፡፡ በሱዳንም እንዲሁ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ሁሌም ለሩሲያዎች ፋይዳ ነበረው፡፡ የሰዎች ለሰዎች ጉድኝት፣ እንዲሁም የወታደራዊ ወዳጅነትና የንግድ ፍላጎቶች አሏቸው፡፡ እንግሊዞችም እንዲሁ በቀጣናው ቆይተዋል፡፡ ግብፅን፣ ከፊል የመንን፣ ሶማሊያንና ሱዳንን ቅኝ ገዝተዋል፡፡ ስለዚህም በቅኝ ግዛት ዘመን በአንድም በሌላም መንገድ በቀጣናው ነበሩ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አሜሪካኖቹ የቃኘው ጦር ሠፈር በአስመራ ነበራቸው፡፡ አሁን ደግሞ በጂቡቲ ግዙፍ የሆነው ካምፕ ሌሞነር አላቸው፡፡ ሁሉም እዚሁ የነበሩ ሲሆን፣ ፍላጎታቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መጥቷል፡፡

ሪፖርተር እንግዲህ በቀጣናው ከቀይ ባህር ወዲህና ወዲያ ያሉ አገሮችን ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ በዚህ ቀጣና ያላት ሥፍራ ምንድነው?

አቶ ገብርኤል፡- ኢትዮጵያ በቀጣናው መልህቅ የሆነች አገር ናት፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር የምትገናኝ አገር አይደለችም፡፡ ሆኖም በሕዝብ ቁጥሯ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚና በወታደራዊ አቅሟ ከፍተኛነት ኢትዮጵያ የቀጣናው ኃያል ሆና ቆይታለች፡፡ ጂቡቲን ብትመለከት የጂቡቲ ኢኮኖሚ የአገልግሎት ኢኮኖሚ ሲሆን፣ ያ አገልግሎት ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚሰጥ ነው፡፡ ሶማሊላንድም እንዲሁ የጂቡቲን መስመር የምትከተል ነው የምትሆነው፡፡ በፕሬዚዳንት ፎርማጆና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መካከል ጠንካራ ግንኙነት በመፈጠሩም የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት መልካም እየሆነ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዘመን ኢትዮጵያ የቀጣናው ደኅንነት ማዕከል ነበረች፡፡ ለበርካታ ጊዜያት ኢትዮጵያ ሶማለያ በመግባት የኢስላሚክ ኮርት (በኋላም አልሸባብ) አባላትን ስታሳድድ ከመቆየቷም ባለፈ፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የአሚሶም ጦር አካል ሆናም ሆነ በተናጠል በሶማሊያ ወታደሯን አስፍራለች፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ግንኙነት ውጥረት የሚታይበት ቢሆንም፣ አሁን በተፈጠረው ሰላም ሳቢ ሁለቱም አሁን ወደፊት እየተመለከቱ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ መልህቅ ሆና ቆይታለች ማለት እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ባትኖር የመላ ቀጣናው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ውል ይፈርሳል፡፡ በኢትዮጵያ የሚፈጠር አንድ ችግር መላ ቀጣናውን የሚያናጋ ሲሆን፣ ቀጣናውን ይዞ እንደሚወድቅም እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ቀጣናውን አንድ ላይ የምትይዝ ሙጫ ናት፣ መላ ቀጣናው የሚሾርባት ዘንግ ናት፡፡

ሪፖርተር፡እንዳለመታደል ሆኖ ግን ቀጣናው ከግጭቶችና ከተራዘሙ ጦርነቶች ነፃ ሆኖ አያውቅም፡፡ በቀጣናው ካሉ ፍላጎቶች አንፃር ይኼ እንዴት ሊታይ ይችላል?

አቶ ገብርኤል፡ ትክክል ብለሃል፡፡ ቀጣናው ከግጭቶች ተላቅቆ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ግጭቶች ከፊሉ የእጅ አዙር ጦርነት ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ፍላጎቶች ከበስተጀርባ ስለሚገኙ፡፡ ያለፉትን 50 ዓመታት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ብትመለከት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ለኃያላን አገሮች ፍላጎቶች ተገዥ ነበሩ፡፡ በአንዱ ወገን ሶቪየቶች ሲኖሩ፣ በሌላኛው ወገን ደግሞ አሜሪካ ትገኛለች፡፡ ከዚያም ሥፍራ ይቀይራሉ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን አመፀኞቹ እኛው ብንሆንና ተዋጊዎቹ እኛው ብንሆንም፣ የእኛ ጦርነቶች በሌሎች ይቀጣጠላሉ፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነትም ከበስተጀርባ ሌላ እጆች ነበሩ እላለሁ፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መካከል የተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት አልነበረም፡፡ እርግጥ ነው ለጦርነቶቹ ራሳችን ነን ኃላፊነት መውሰድ የሚኖርብን፡፡ ወደ ጦርነት መግባትም ቢሆን የእኛው ጥፋት ነው የሚሆነው፡፡ ቢሆንም ግን በውጭ ኃይሎች የሚጨመርበት ነዳጅ አለ፡፡

የእኛ ፍላጎቶችም ተቀያያሪ ነበሩ፡፡ የአገር ግንባታ ሒደቱ አቅጣጫ ሲቀያይር የነበረ ቀጣይ ሒደት ነው፡፡ ሶማሊያ ነፃነቷን ያገኘችው በ1960ዎቹ፣ ኤርትራ በ1990ዎቹ እንዲሁም ሱዳን በ1960ዎቹ ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ግንባታና የድንበር ማካለል ጉዳዮች ነበሩባቸው፡፡ ስለዚህም ልዩነቶች ሊኖሯቸው፣ ግጭቶች ሊፈጠሩ፣ እንዲሁም ተስፋፊ መንግሥታት ሌሎች ላይ ለአመፅ ሊያነሳሱ ይችላል፡፡ ውጤቱም ወደ ጦርነት መግባት ይሆናል፡፡ እኔ በሕይወቴ የማስታውሰው፣ ባንተም የሕይወት ዘመን ተመሳሳይ እንደሚሆን የምገምተው፣ ቀጣናው ሙሉ ለሙሉ ሰላም ሆኖ እንደማያውቅ ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን የአማፅያን እንቅስቃሴ፣ ጦርነት፣ ወዘተ ነበር፡፡ ምናልባትም ጂቡቲ ትሆናለች በተለየ ሁኔታ ሰላማዊ ሆና የቆየችው፡፡ ከዚያ ውጪ ጦርነት መቀስቀስና ሕይወትን ማጣት በማይገባቸው ጉዳዮች እርስ በርስ ለመጋጨት ምክንያት አናጣም ነበር፡፡ ነገር ግን የውጭ ፍላጎቶች ሁሌም ሁኔታዎችን ያባብሱ ነበር፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ነው የቀጣናውን ግጭቶች የምመለከተው፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ ቀጣናው በቅርቡ እያስተናገዳቸው ካሉ ግጭቶች አንዱ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ነው፡፡ በትግራይ ክልል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የጀመረው ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ትኩረት ሲስብ ተስተውሏል፡፡ ኢትዮጵያ ይኼ የውስጥ ጉዳዬ ነው ብላ ብትከራከርም፣ በተለይ ከምዕራቡ ዓለም ጦርነቱን ማስቆም በሚል ምክንያት ተፅዕኖዎች ሲያይሉ ይታያል፡፡ ለመሆኑ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ያለው ፍላጎት ምንድነው?

አቶ ገብርኤል፡- ኢትዮጵያ በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ተገድዳና ተገፍታ የገባችበት ሁኔታ ነው፡፡ የሕግ ማስከበር ተብሎ የጀመረው ዘመቻ፣ እኔ አሁንም የሕግ ማስከበር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደ ሙሉ ጦርነት የተሸጋገረ ሲሆን፣ በሕወሓት ኃይሎች ምክንያትም እየተባባሰ የመጣ ነው፡፡ ወንድም ወንድሙን ሲገድል፣ እንዲሁም እህት እህቷን ስትገድል ማየት ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያ ይኼንን መሸከም አትችልም፣ ኢትዮጵያውያን ይኼንን መሸክም አይችሉም፣ አይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለይም ትግራዋይ ይኼንን እንደማይፈልጉት ለሕወሓት አመራሮች ትልቅ መልዕክት ይመስለኛል፡፡ ምንም ቢሆን ጉዳያቸው በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ያላት አገር ናት፡፡ ይኼም ግጭቶችን ለመፍታት መሠረት ሊሆን ይገባል እንጂ፣ ወደ ግጭት መግባት መፍትሔ አይሆንም፡፡

በዚህ ውስጥ የምዕራቡ ዓለም ፍላጎት ድርብርብ ነው፡፡ ቀዳሚውና ዋናው ፍላጎታቸው ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሰብዓዊ ድጋፍ ማስገባትን የተመለከተ ነው፡፡ ይኼንን ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶች በአፋርና አማራ ክልሎች በተመሳሳይ የሚታዩ ቢሆንም ቅሉ፣ እነዚህን ለመጥቀስ ያቅማማሉ፡፡ በእርግጥ በትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት በመኖሩ ድጋፉን ማድረስ እጅግ የሚደነቅ ተግባር ነው፡፡ ማንም ይኼንን አይክድም፡፡ በእርግጥ በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ መንግሥት 70 በመቶ የሰብዓዊ ድጋፍ ዕርዳታን ያቀርባል፡፡ ማንም የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶች በትግራይ እንዳሉ ባይክድም፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶች ግን የሌሎች ፍላጎቶች መሸከሚያ የትሮይ ፈረስ ነው የሆነው፡፡ ሙሉ የሰብዓዊ ድጋፍ መስመር የተከፈተላቸው ቢሆንም፣ 70 በመቶ የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረሰ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፣ ምዕራቡ አይደለም፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ ሀቀኛ ፍላጎት ቢሆንም ይኼ ጥልቅ የሆነው ፍላጎት የፊት ለፊት ገጽታ ነው እላለሁ፡፡

በእኔ ዕይታ የምዕራቡ ዓለም ቢያምንበትም ባያምንበትም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ደስተኞች አይመስሉም፡፡ ሕወሓት ላይ የተነሳን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወጣትና በኃይል የተሞሉ ሲሆኑ፣ ሰፊ የሆኑ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ጀምረው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ የተመረጡ ሕጋዊ ተቀባይነት ያላቸው የኢትዮጵያ መሪ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ምርጫዎችን እከታተላለሁና ይኼኛውን የኢትዮጵያ ምርጫ ከየትኛውም ጋር ባስቀምጠው ነፃ፣ ፍትሐዊ እንዲሁም ፉክክር የታየበት ነበር፡፡ እርግጥ ነው በወንጀል ተጠርጥረው በእሥር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኛ እስረኞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውጪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን ለማቅረብ ነፃ ነበሩ፣ ነፃ የአየር ሰዓት ተሰጥቷቸው ነበር፣ በአደባባይ ተሟግተዋል፣ ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች በስተቀር በመላው አገሪቱ መንቀሳቀስ ይችሉ ነበር፣ በምርጫም ተሳትፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በማይመች የአየር ሁኔታ ውስጥ ሆነው በሰላማዊ መንገድ ድምፅ በመስጠት ብስለታቸውን፣ ሥልጡንነታቸውን፣ እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባራቸውን ያስመሰከሩበት ነው፡፡ በምርጫው ኢትዮጵያውያን እንዲህ የተደራጁና የተቀናጁ ሆነው ማየት እጅግ የሚያስደስት ነበር፡፡ የተወሰኑ ወጣ ገቦች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ቅሬታዎች ለምርጫ ቦርድ ቀርበው የሚታዩበት ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ የሆነ አሠራር ተመሥርቶ ነበር፡፡

እንግዲህ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መሪ አላት አገሪቱ፡፡ የሥልጣናቸው ከፊል ይሁንታ የመጣው ጠንካራ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸውና የኢትዮጵያን አጀንዳ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ የሚያስተጋቡ መሆናቸው ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ምዕራባውያንን ያስጨንቃቸዋል፡፡ ምዕራባውያን በቀጣናው ያላቸው ፍላጎት መረጋጋትን ማስፈን ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ መረጋጋት እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ በጦር ቀጣናው ፍላጎታቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ቢሆንም፣ እንዳልኩት እርሱ የሌላ ፍላጎት ሽፋን ነው፡፡ ነገር ግን በጠቅላላ በኢትዮጵያም ሆነ በመላ ቀጣናው የእነሱ ቀዳሚ አጀንዳ ቀጣናውን የተረጋጋ ማድረግ ነው፡፡ ሶማሊያ የተረጋጋችና በአልሸባብ እጅ የማትወድቅ እንድትሆን፣ ኢትዮጵያም፣ ኬንያም፣ ወዘተ የተረጋጉ እንዲሆኑ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ለእነርሱ የቀጣናው መረጋጋት መልህቅ ናት፡፡

የተረጋጋች ኢትዮጵያን ቢሹም ግን እንደ ዓብይ አህመድ ያለ ጠንካራ፣ ነፃና ኢትዮጵያዊ የሆነ መሪ እንዲኖራት ደግሞ አይፈልጉም፡፡ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ደስ ብሏቸው ነበር፡፡ እንደ ግለሰብ የሚወደዱ፣ ወጣት፣ ጎበዝ፣ የተማሩ፣ ሐሳባቸውን መግለጽ የሚችሉ፣ እንዲሁም ለራሳቸውም ሆነ ለአገራቸው ማሰብ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም ጥገኝነት የተላቀቁና በተቻላቸው አቅም የኢትዮጵያን ፍላጎት ብቻ የሚያራምዱ ናቸው፡፡ ከዋሽንግተንም፣ ከቤጂንግም፣ ከሞስኮም፣ ከአቡ ዳቢም፣ ከጅዳም እኩል የሚወዳጁ ናቸው፡፡ አጀንዳቸውም ኢትዮጵያ ብቻ እንጂ ሌላ የለም፡፡ ይኼ ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር ያልሆነ መሪ ስለሆነ ያሳስባቸዋል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት አቶ መለስ ዜናዊ ጠንካራ መሪ የነበሩ ቢሆንም፣ እነሱ የፈለጉትን የሚያደርጉላቸው ሰው ነበሩ፡፡ የሚፈልጉትን በማድረግ በቀጣናው የእነሱን ፍላጎት ሲያስፈጽሙ ነበር፡፡ በተራቸው አቶ መለስና መንግሥታቸው ኢትዮጵያውያንን ሲጨቁኑ ፊታቸውን ያዞራሉ፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ የነበረው የአዲስ አበባ ዕልቂት ቢታወቅም ሱዛን ራይስ መቶ በመቶ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነበር አሉ፡፡ ባራክ ኦባማም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ አመሠገኗቸው፡፡ ይኼ እውነታው እንዳልነበረ ግን በደንብ ያውቁታል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሰዎች ይመቿቸው ስለነበረ ምንም ቢሆን ይደግፏቸው ነበር፡ በእኔ ዕይታ ዓብይን በዚያ ቅርፅ ሊገጥሙ አልቻሉም፡፡ እጅግ ነፃ፣ ሲበዛ ኢትዮጵያ ተኮር ናቸውና፡፡ ይኼም ያሳስባቸዋል፡፡ አየህ በርካታ ሰዎች የምዕራቡ ዓለም ዓብይን ሊያስወግድ ይፈልጋል ብለው ያምናሉ፡፡ እኔ ግን ዓብይን ሊያስወግዱ ይፈልጋሉ ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ሊያዳክሟቸው ይፈልጋሉ፡፡ በሰሜኑ ያለው ጦርነት ሲጀመር ወዲያውኑ ወጥተው አላወገዙትም፡፡ እስከ ዛሬም የባይደን አስተዳደር ስለግጭቱ በርካታ ነገሮችን ያለ ቢሆንም፣ ‹‹ይኼ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጠ መንግሥት ላይ የተቃጣ ጦርነት ነውና አቁሙ፤›› አላለም፡፡

በቅርቡ ለአትላንቲክ ካውንስል በጻፍኩት ጽሑፍ በአዲስ አበባ የተፈጠረውንና በካርቱም የተፈጠረውን አወዳድሬ ነበር፡፡ በካርቱም ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በወታደራዊው ኃይል ተጠቅተው፣ ከሥልጣን ተወግደው የቤት ውስጥ እስረኛ ተደረጉ፡፡ አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ሐሳብ ለመሰንዘር ቀዳሚ ነበረች፡፡ የምዕራቡ ዓለም አጋሮቿን አስተባብራም ተቀባይነት የለውም ስትል ተደመጠች፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ባይሆኑም በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተሾሙ ስለሆኑ በአስቸኳይ ወደ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ጠየቁ፡፡ ይኼንንም አስረግጠው ተናገሩ፣ ትክክልም ነበሩ፡፡ የወታደሩ የሥልጣን ጠለፋ ተቀባይነት እንደሌለው በመናገር ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ፡፡ ከድንበሩ ወዲህ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት ሥልጣን ለመንጠቅ በሚሻ አማፂ ቡድን ጥቃት ተሰነዘረበት፡፡ አሜሪካ ልታደርግ የቻለቸው ትልቁ ነገር ቢኖር ሁለቱንም ወገኖች ቁጭ ብላችሁ ተነጋገሩ ማለት ነበር፡፡ ይኼንን ነው እንግዲህ እኔ ሐሳዊ እኩልነት የምለው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ተከትሎ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ከሚሻ አማፂ ጋር አስተካከሉት፡፡ ይኼ ለእኔ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መርሆዎችን መቃረን ነው፡፡ ለዚህ የሚታየኝ ብቸኛው ምክንያት የምዕራቡ ዓለም የተዳከመ ዓብይን የሚፈልጉ መሆናቸውን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥትም ሆነ የተለያዩ ተመልካቾች የምዕራቡ ዓለም ዓለም በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ እየሠራ ነው ቢሉም፣ እርስዎ ደግሞ አይደለም እያሉ ነው፡፡ እንዲህ ለማለት ያስቻለዎት ግምገማ ምንድነው?

አቶ ገብርኤል፡- ይኼ እኮ ዓብይን ስለሚወዱ አልያም ፍቅር ተጠናውቷቸው አይደለም፡፡ በቀላሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ ማምጣት የሚያስከፍለው ዋጋ ሊታሰብ የሚችል እንደማይሆን ስለሚገባቸው ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ፍላጎት ውጪ የሚሆን ማንኛውም የመንግሥት ቅየራ ጥረት፣ ከአርባ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ተናግረዋልና ከዚህ ፍላጎታቸው በተቃራኒ መሄድ መላ ቀጣናውን እሳት የሚያለብስ ነው የሚሆነው፡፡ ይኼ የመከሰቱን ዕድል የምዕራቡ ዓለም በሚገባ ያውቀዋል፡፡ በፖለቲካ፣ በፋይናንስ፣ በኢኮኖሚና በሰብዓዊ መለኪያዎች የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡

ነገር ግን እንዳልኩህ እጅግ ጠንካራና ኢትዮጵያን የሚያቀነቅን ዓብይን አይፈልጉም፡፡ እንዲቆዩ ይሻሉ፣ ግን በእነሱ ተገዥነት ብቻ፡፡ ይኼ ጦርነት ሲጠናቀቅና በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎችም ሰላም ሲመለስ የዓብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ጎረቤት አገሮች፣ እንዲሁም ወደ ምዕራና ምሥራቁ ዓለም ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ከፍቶ አቋሙን ማስረዳትና ከምዕራቡም ሆነ ከምሥራቁ ዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት ማደስ ይኖርበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ትክክል ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የተመረጡ መሪ ናቸውና በምዕራብም፣ በምሥራቅም፣ በደቡብም ሆነ በሰሜን የኢትዮጵያን ፍላጎት ማስጠበቅ ነው ሥራቸው፡፡ እሳቸው እያደረጉት ያለውም ይኼንን ነውና ሌሎቹ ያሳስባቸዋል፡፡ ነገር ግን እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ያሉ የተዛቡ አረዳዶችን ለማስተካከል መሞከር ከእሳቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ በአሜሪካ አዎንታዊና ቀና አመለካከት አለ፡፡ ከጥቂት የሕወሓት ወዳጆች በስተቀር አሜሪካኖች ኢትዮጵያን በተመለከተ አዎንታዊ ምልከታ ያላቸው ሲሆን፣ ግንኙነቱን ለማስተካከል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ዳያስፖራውና ሁሉም በጋራ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ስለዚህ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት የማይቻልና እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ሊያስቡት አይችሉም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን የሚተካና በ100 ሚሊዮን ኢትዮጵያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሰው ማግኘት ዘበት ነው፡፡ ሕዝቡ መሪውን መርጧል፣ እርሱም መሪያቸው ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ሪፖርተር፡ከምዕራቡ ወደ ኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎች አንዱ ገጽታ ኢኮኖሚያዊ መልክ ያለው ሲሆን ይኼም እስከ ማዕቀብ የዘለለ ነው፡፡ አንድ ሚሊዮን ለሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ከሚፈጥረው የቀረጥ ነፃ የአጎዋ ዕድልም ኢትዮጵያን ለማስወጣት ዕቅድ አለ፡፡ ጦርነት ኢኮኖሚ የሚያሟጥጥ ሆኖ ሳለ፣ ይኼ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገሮች ፈታኝነቱ ያይላል፡፡ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖና የምዕራቡ ዓለም ጫና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ምንድነው?

አቶ ገብርኤል፡- እርግጥ ነው ይኼኛውም ሆነ የትኛውም ጦርነት ኢኮኖሚን ያወድማል፡፡ እንደ መታደል ሆኖ ኢኮኖሚው ጠንካራ ሆነና ጉዳቱን መቆጣጠር ተችሏል፡፡ ነገር ግን ጉዳቱ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡ የየቀኑ የጦርነት ወጪ በመቶ ሚሊዮኖች ነው፡፡ ይኼ ገንዘብ ትምህርት ቤቶችን፣ ክሊኒኮችንና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ይውል ነበር፡፡ በውጭ ምንዛሪ ላይ ያለው ተፅዕኖም ከፍተኛ ነው፣ በተለይ ከወጪ ንግድ ቅነሳ ጋር ተያይዞ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን ቀንሷል፣ በዚህም የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ይቀንሳል፡፡ የኢትዮጵያ ገንዘብ (ብር) የግብይት ጥንካሬም ይፈተናል፡፡ በጠቅላላው ኢኮኖሚው በከባድ ጫና ሥር ነው ያለው፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚውን በጥንቃቄ እየመሩ እንዳይወድቅ ለማድረግ እየተጣጣሩ የሚገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ሰዎች ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ የፋይናንስ ሚኒስትር ሰዎች እጅግ የሚደነቅ ሥራ የሠሩ ቢሆንም ሊያደርጉ የሚችሏቸው ነገሮች ውስን ሲሆኑ፣ ጊዜም ይገድባቸዋል፡፡ የቁጥር ማስረጃዎችን ብትመለከት ኢኮኖሚው በትንሹም ቢሆን ማደጉን ይቀጥላል፡፡ ሆኖም የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነት፣ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የቁሳቁስ እጥረት ሃይ ባይ ያስፈልገዋል፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ግብርናን የመሳሰሉ ቁልፍ ዘርፎች መልካም አፈጻጸም ያሳያሉ፡፡ የዘንድሮ ዝናብ መልካም ነበር፡፡ ስለዚህ የተትረፈረፈ ምርት ይኖራል ዘንድሮ፡፡ ምንም እንኳን በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ የተከሰተና በተወሰኑ ቦታዎች ያሉ ምርቶች ያልተሰበሰቡ ቢሆንም፡፡ በአጠቃላይ ግብርና መልካም አፈጻጸም ይኖረዋል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችና የጥሬ ዕቃዎች እጥረት ቢኖር ኢንዱስትሪም መልካም አፈጻጸም ያሳያል ብዬ አስባለሁ፡፡ በጠቅላላው በተለይ በቂ የወጪ ንግድ ስለማይኖር በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ጫና ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ፡፡ የዚህን ጉዳት ማየት እንጀምራለን፡፡

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ አጎዋ የሚመጣው፡፡ አጎዋ ኢትዮጵያ የምትሳተፍበትና በየዓመቱ በጥቂት ሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት ምርት የምትሸጥበት የወጪ ንግድ ማበረታቻ ሥርት ነው፡፡ ማስያዝ ካለብኝ አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንደማታስወጣ እርግጠኛ ነኝ እላለሁ፡፡ ምንም ዓይነት የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ምክንያታዊነት የለውም፡፡ ከዚህ ባለፈም ከዳያስፖራውና ከተለያዩ የአሜሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ፖለቲካንና ንግድን ማስተሳሰር የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች እየጎሉ ነው፡፡ እዚህ ጋ ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሉ ሰዎች እየተሳሳቱ ያሉት፡፡ ማዕቀቦች የሚፈለገውን ውጤት አያስገኙም፡፡ ማዕቀቦች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሣሪያዎች አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ ቀውስ አለ፣ ግን ይኼንን የሚፈታው ዲፕሎማሲ እንጂ ማዕቀብ ሊሆን አይችልም፡፡ ማዕቀቦች ቀውሶችን ለመፍታታ የመጀመርያ አማራጭ መሆን የለባቸውም፣ የመጨረሻ እንጂ፡፡ አሜሪካ ዲፕሎማሲን ሳትሞክር ነው ወደ ማዕቀብ የሄደችውና ለዲፕሎማሲ ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለዲፕሎማሲ ዕድል ከተሰጠ በኋላ ማዕቀብ መጨረሻ ላይ ሊመጣ ይችላል፡፡ አሜሪካ ንግድን ከፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር ማስተሳሰሯ ስህተት ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ካሉ፣ በየትኛውም ጦርነት እንዳሉ ይታመናል፡፡ ይኼንን ለመፍታት የሚኬድባቸው የፖለቲካ ሒደቶች ያሉ ሲሆን፣ ማዕቀብ ለመጣል ማስፈራራት ግን የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታት የሚውል መሣሪያ አይደለም፡፡ ማዕቀብ የሚጣል አይመስለኝም፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ አትጥልም፡፡ ኢኮኖሚው የተደቆሰ ቢሆንም ሳይበገር ቆይቷል፡፡ ጦርነቱ እንዳቆመም የመልሶ ግንባታ ሥራው በፍጥነት ይጀመራል፡፡ ከዳያስፖራው ከፍተኛ የሆነ የመልሶ ግንባታውን የመደገፍ ፍላጎትና መነሳሳት አለ፡፡ በዚህ ጦርነት አንድ መልካም ነገር ተገኘ ቢባል እኔ እስከ ማስታውሰው ድረስ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ባልታየ መልኩ ኢትዮጵያውያንን ከመሪያቸው ጀርባ ማሠለፉ ነው፡፡

ሪፖርተር  እርስዎ የገንዘብ ሚኒስቴር ሰዎች ኢኮኖሚውን በጥንቃቄ መርተውታል ብለዋል፡፡ የፋይናስ ሚኒስቴር እስከ ዛሬ የጦርነቱን ተፅዕኖ መቋቋም የተቻለ ቢሆንም፣ ጦርነቱ ከዚህ በላይ የሚራዘም ከሆነ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ደግሞ ይናገራሉ፡፡ ጦርነቱ የሚራዘም ከሆነ የሚያስከትለው ፈተና ምንድነው?

አቶ ገብርኤል፡– ግጭቱን ለዘለዓለም ማቆየት እንችላለን ብዬ አላምንም፡፡ በፍፁም አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ሳይቀር እስከ ጥግ ተለጥጣለች፡፡ በፍላጎትና በአቅርቦት ወገን የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወስደው ነው ኢኮኖሚው እስካሁንም እንዲሄድ የተደረገው፡፡ አቅርቦትን የምትገታ ከሆነ ኢኮኖሚው እየተጨራመተ ይመጣና ትንሽ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ሁኔታውም ሲባባስ በዓለም አቀፍ ገበያ የኢትዮጵያ የብርድ ደረጃ ዝቅ ይላል፡፡ የደረጃ አውጪ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን ቦንድ ወደ ማይረባ ደረጃ (Junk Status) ያወርዱታል፡፡ ይኼም የውጭ ምንዛሪ ክምችቱና የብር የግብይት አቅም እንዲቀንሱ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በተራዘመ ጦርነት በርካታ አምካኝ ተፅዕኖዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ጦርነቱን በፍጥነት መጨረስና ለሰላም ዕድል በመስጠት ኢትዮጵያን መልሶ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ትግራይ ተደቁሳለች፣ መልሰን መገንባት ይኖርብናል፡፡ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ሌሎችም ክልሎች እንዲሁ ተጎድተዋል፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ መቆም አለበት፣ ትኩረታችንም ኢትዮጵያን መልሶ ወደ መገንባት መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እንዳሉት ጦርነቱ ዕድሜ ልኩን መቀጠል አይችልም፡፡ አሁን ከአንድ ዓመት በላይ ዘልቋልና እንዴት ወዴት እያመራ ይመስላል ጦርነቱ?

አቶ ገብርኤል፡ ሕወሓት ወደ አማራና አፋር ክልሎች የሚያደርገውን መስፋፋት ማቆም አለበት፡፡ አሁን ጦርነቱ ትግራይ ውስጥ አይደለም፣ ትግራይ ምንም ጦርነት የለም፡፡ ይኼ ደግሞ እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ንግግር ጭምር ነው፡፡ እነዚህን አካባቢዎች የተቆጣጠሩ አካላት በምንም መንገድ ይሁን መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼ ከሆነ በኋላ ለግጭቱ ምክንያት የሆነው ምንም ይሁን ምን በጠረጴዛ ዙሪያ ሊፈታ ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ አለኝ ካለ ሒደት ያለው ሲሆን፣ በሕወሓቶች በራሳቸው የተሠራ ሕገ መንግሥት አለ፡፡ ጦርነት የዚህ ሒደት አካል አይደለም፡፡ ሕወሓት ጦርነቱን ማቆም አለበት፣ አዋኪ ኃይል እንዲሆን ሊፈቀድለትም አይገባም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ነውና እንዲህ ሊሆን ይገባል፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር አቻ የሆነ የትግራይ መከላከያ ኃይል የሚባል አገላለጽ ቅቡል ሊሆን አይችልም፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ኃያል ሠራዊቶች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ በብሔራዊ ውይይት አማካይነት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ሊዳኙት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ ሁሉ እንዲሆን ጦርነቱ መቆም አለበት፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው መመለስ ይኖርባቸዋል፣ መልሶ ግንባታውም መጀመር ይኖርበታል፡፡ ይኼ እንዲሆን ሰላም መምጣት ይኖርበታል፣ ሰላም እንዲመጣ ደግ የሕወሓት ኃይሎች የተቆጣጠሩትን ቦታ መልቀቅና ወደ ትግራይ መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚያ የፖለቲካ ሒደቱ መጀመር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን የጦርነትን የኢኮኖሚ ተፅዕኖዎች ተመልክተናል፣ ጦርነትም የመንግሥትን ካዝና እንደሚያራቁት ዓይተናል፡፡ ጦርነት ከዚህም ባለፈ ለጦርነት የሚገባው ጠንካራና ወጣት ኃይል ነውና የሠራተኛውን የሕዝብ ክፍል የሚጎዳ ነው፡፡ ካመላከቷቸው ጉዳዮች አንፃር ሲታዩ መንግሥት ከጦርቱ መጠናቀቅ በኋላ ምን የቤት ሥራዎች ይጠብቁታል?

አቶ ገብርኤል ንጋቱ፡ እንግዲህ በጦርነት ውድነት ከተስማማን፣ ሰላም ደግሞ ይበልጥ ይወደዳል፡፡ መጀመርያ በጦርነቱ ሳቢያ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ወዘተ የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው ሊመለሱና ሊቋቋሙ ይገባል፡፡ ሕይወታቸው ሊቀጥልና ከተቋረጠበት ሊጀምር ይገባል፡፡ እዚህ እንግዲህ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው፡፡ ሌላው ደግሞ በፈቃደኝነት ጦርነቱን የተቀላቀሉ ከሚሊዮን በላይ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ሥራቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ኑሯቸውን ትተው ለአገራቸው ለመዝመት የወጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ሊደገፉ ይገባል፡፡ ለአገራቸው ሕይወታቸውን ሰጥተው ሲያበቁ በየጎዳናው የሚንከራተቱ ሥራ አጦች ሊሆኑ አይገባም፡፡ ይኼ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለእነዚህ ወጣቶች የሥራ ዕድል፣ የቢዝነስ ዕድል፣ እንዲሁም የግብርና ዕድል የመፍጠር ከፍተኛ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ እርሻ ሊያርስ ያልቻለ የማኅበረሰብ ክፍል እንዳለው ሁሉ፣ ያረሰውንና የዘራውን ያጣም አለ፡፡ እነዚህን መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ሁሉ አንድ ላይ ስታደርጋቸው ከወታደራዊ ወጪ ውጪ፣ በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ወጪ ይጠይቃል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደጠቀስኩት በኢኮኖሚ አገላለጽ ሰላም ከመንግሥት ረገድ በሚጠይቀው ፍላጎት መሠረት እጅግ ውድ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው የምዕራቡ ዓለም ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ በዚህ ጊዜ ወዳጅነቱን ማስመስከር ያለበት፡፡ በጦርነቱ መወገን ሳይሆን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ለመልሶ ግንባታ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ጦርነቱ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ ኢትዮጵያ ልትፈታው ትችላለች፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን መልሶ ለመገንባት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተመረጠው መንግሥት ጎን በመቆም፣ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መወገንና ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ዳያስፖራው ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አገራቸውን ለመገንባት ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በላይ ይኼንን የሕዝብ ክፍል በእጅጉ የምትፈልግበት ጊዜ ሲሆን፣ ለእኛ የመጣ ትልቅ ዕድልም ነው እላለሁ፡፡ ለአውሮፓውያን አዲስ ዓመት/ለገና ወደ አገር ቤት ለመመለስ የሚደረግ ትልቅ እንቅስቃሴ እንዳለ ስገልጽ ደስታ እየተሰማኝ ሲሆን፣ በሁሉም ዘርፎች የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት ከጦርነት በኋላ ወታደር የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል ትጥቅ ስለማስፈታት፣ ከዘመቻ መመለስና ከሕዝብ ጋር መልሶ ስለመቀላቀል (Disarmament, Demobilization And Reintegration (DDR)) ሲናገሩ ስሰማ፣ ይኼንን ማድረግ ከማድረጉ በላይ ሲነገር ቀላል ይመስላል ብለው ነበር፡፡ አገሪቱ ከጦርነቱ በኋላ ፊቷን ወደ አምራች ዘርፉ ስትመልስ በዚህ ረገድ ሊገጥማት የሚችለው ጫና ምን ሊሆን ይችላል?

አቶ ገብርኤል፡- እውነት ነው ትጥቅ ማስፈታት፣ ከዘመቻ መመለስና ከሕዝብ ጋር መልሶ መቀላቀል (DDR) ሲነገር ቀላል ይመስላል፡፡ መሣሪያ አስመልሰህ ሲቪል ሁኑ ስትል ሕይወታቸውን የሚመሩበት ሥራ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አርሶ አደሩ ምናልባት ወደ ቀዬው ሲመለስ እርሻው በሌላ ሰው ተወስዶበት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከኅብረተሰብ ጋር መቀላቀል ራሱን የቻለ ፈተና ያስከትላል፡፡ ለአብነት የወልቃይትና የጠገዴን እንዲሁም አካባቢውን ውሰድ፡፡ በዚህ ቦታ ይኼንን ማድረግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የመሬቱ ቀዳሚ ባለቤቶች የሆኑት አማሮች መልሰው አካባቢውን ተቆጣጥረዋልና፡፡ ስለዚህ ከዚህ የተፈናቀሉ ትግራዋይ ይኖራሉና መሬትና የተለያዩ ግብዓቶች ቀርበውላቸው ሊስተናገዱ ይገባል፡፡

መልሶ ከሲቪል ነዋሪው ጋር መቀላቀልም ራሱን የቻለ ፈተናዎች አሉት፡፡ ማኅበራዊ ቅልቅል አስቸጋሪ ሊሆን ይችል፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ከፍተኛ የፋይናንስ ጫና ይኖረዋል፡፡ ሰዎችን በሉ ሂዱና ሕይወታችሁን ቀጥሉ ልትል አትችልም፡፡ ምክንያቱም ሕይወታቸው ተዛብቷልና፡፡ የተዛባው ደግሞ አንተ ለጦርነት ስለጠራኃቸው ነው፡፡ የእርሻ ወቅት አልፏል፣ ሰብል አልተሰበሰበም፣ ከብቶችም ጠፍተዋል፡፡ ኑሯቸውን ለመጀመር የመንግሥትን ድጋፍ የሚሹ ነው የሚሆኑት፡፡ ይኼ ምን ያህል ሊያስወጣ እንደሚችል ለማስላት ጊዜ የሚጠይቅ ውስብስብ ሥራ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን በቢሊዮኖች የሚቆጠር እንደሚሆንና ሲመጣም ፍላጎቱ አንዴ እንደሚመጣ እርግጠኛ ሆኜ ልነግርህ እችላለሁ፡፡ አፋሩን እስከ ማለማ አማራው ይቆየኝ፣ ኦሮሞን እስከ ማሰፍር አፋር ቆየኝ ልትል አትችልም፡፡ ሁሉም አንዴ ነው የሚመጣው፡፡ አገሪቱ ደግሞ ያንን ማድረግ አቅሙ አላት፡፡ በአዲስ አበባ ላሉ ዲፕሎማቶች ያለኝ ጥሪ በፖለቲካ ጣልቃ መግባትን አቁመው አገሪቱን መልሶ በመገንባት ላይ እንዲያተኩሩ ነው፡፡ ፖለቲካውን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ተውትና አገሪቱ ከገባችበት አዘቅት ትወጣ ዘንድ በመልሶ ግንባታ አግዙ እላለሁ፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...

‹‹የኢትዮጵያን የውስጥ ችግሮች ሁሌም የሚያባብሰው ከውጭ የሚመጣ አስተሳሰብ ነው›› ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር) የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር የውጭ ግንኙነት ኃላፊም ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት አሥርት ዓመታት ታሪክ አስተምረዋል፡፡...