Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢትዮጵያን ዕድገት ለማስቀጠል በኅብረት እንጓዝ!

በናታን ዳዊት

አንድነታችንና ትብብራችን ብዙ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአገር ላይ የደረሰው ውድመት አቻ የማይገኝለትና የመጨረሻውን የክፋት ጥግ ያሳየበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህንን ፈታኝ ወቅት በአሸናፊነት ለመወጣት የኢትዮጵያውያን በጋራ መቆም ወሳኝ ነው፡፡ በአንድነት መቆማችን ሊከሰት ይችል የነበረውን ጥፋት ከመቀነሱም በላይ ወደ መጨረሻው የአሸናፊነት ምዕራፍ እያሸጋገረንም ነው፡፡

አገር ማፍረስ ድረስ ምኞት የነበረው ይህ ቡድን ምኞቱን ለማሳካት በውጭም በውስጥም ያደረገው ጥረት ቀላል ባይሆንም፣ ክፋቱን የተረዱ ምኞቱ መሳካት የለበትም ያሉ በአንድነት በመቆማቸው ችግሩ እየተቀለበሰ ነው፡፡

 አንድነትና ትብብር ምን ማለት እንደሆነ በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያሳዩበትን መንገድ በሌሎች አገር የመገንባትና የማልማት ሥራዎች ላይ እንዲውልም ይፈለጋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያልተቋረጠ ርብርባቸውና ጩኸታቸው ብዙ ለውጥ ያመጣ ቢሆንም፣ አሁንም ከፊታቸው ብርቱ ሥራዎች የሚጠብቃቸው መሆኑ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡

ትብብሩ ሁሉም በየፊናው የሚችለውን በማድረግ ጭምር የታየ ነው፡፡ አሁን የገባንበት ፈተና በሕይወት ጭምር ዋጋ እየተከፈለበት ነው፡፡ ይህ ስለኢትዮጵያ ተብሎ እየተደረገ ያለው ርብርብ የሕወሓትን ምኞት እያተነነና ቡድኑም የኢትዮጵያ ሕመም የማይሆንበት ደረጃ ላይ እያደረሰ ነው፡፡

ይህ ቡድን በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች የፈጸማቸው ዘግናኝ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በቢሊዮን የሚገመት ንብረት እንዲወድም አድርጓል፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸው ሳያንስ የሰው እጅ ጠባቂዎች እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፡፡ ሚሊዮኖችን የሚያገለግሉ የጤና ተቋማት ፈራርሰው ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል፡፡ በደሃ አቅም የተገነቡ መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት በቢሊዮኖች እንድናወጣ ያስገድደናል፡፡

ጦርነቱ ያደረሰብንን የሥነ ልቦና ጫና ለማከም የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ ቡድኑ ያደረሳቸው ጥፋቶች በሙሉ ለዓለም በመጥፎ ምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ያደረሰውን ውድመትም ወደነበረበት ለመመለስ የምናደርገው ርብርብ የድሉ መደምደሚያ ሊሆን ይገባል፡፡ የጠላት ሽንፈት የበለጠ የሚሆነውም የወደሙ ከተሞችን ወደነበሩበት ስንመልስና አገራችንን ለማዳን ያሳየነውን ርብርብም በአገር ማሳደጉ ሥራ ላይ ስናውለው ነው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕይወታቸውን የገበሩ ወገኖቻችንን ቤተሰቦቻች ስንደግፍ፣ ለድሉ መገኘት አካላቸውን ላጡ ወገኖቻችን አለንላችሁ ስንላቸውና ለከፈሉት መስዋዕትነት ጎንበስ ስንላቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ከመፍረስ ያዳኑ ወገኖቻችንን ውለታቸውን በአግባቡ መክፈል ያስፈልጋል፡፡

በኢኮኖሚ አንፃርም ኢትዮጵያን ሊያሳድጉ በሚችሉ ዘርፎች ሁሉ በጨዋነት ሌት ተቀን መሥራትንም ይጠይቀናል፡፡

ለሁሉም ግን አገራችንን ለማዳን ዛሬ እየታየ ያለው ስሜት ከላይ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጀምሮ በተግባር የታየ በመሆኑ ይህንኑ መልካም መንገድ ተከትሎ ትብብርን አጠናክሮ ታላቋን አገራችንን ለማሳደግ የበለጠ የምንተጋበት ወቅት መሆን አለበት፡፡

ከፊታችን የሚጠብቀን ብዙ ሥራ አለ ስንልም በእርግጥም ከባድ መሆናቸውን ተገንዝበን ለዚያ መዘጋጀት እንዳለብን ለመጠቆም ነው፡፡ ሊገጥሙን የሚቸሉ ተግዳሮቶችን ሁሉ ተቋቁመን ለቀጣዩ ትውልድ መልካም ነገር ለማሻገር ሁሉም በወኔ ሊሠራ የሚችልበት ወቅት ካለ አሁን ነው፡፡

 የፖለቲካ አመለካከታችን እንደተጠበቀ ሆኖ አገር የማሻገሩ ሥራ ላይ ያለ ልዩነት በጋራ ከሠራን የማንለውጠው ነገር አይኖርም፡፡

የዘር ፖለቲካ ጦሱ ብዙ መሆኑን ከዚህ በላይ የምንማርበት ወቅት የለም፡፡ በብሔር የተደራጀ ቢዝነስ ሳይቀር መጨረሻው ምን እንደሆነ ሰሞኑን በዚህ ጋዜጣ ላይ አንበሳ ባንክ የገባበትን ችግር አንድ ምሳሌ ማድረግ ይቻላልና ፖለቲካችንንም ሆነ ቢዝነሳችን ከብሔርተኝነት አደረጃጀት ማራቅ ሌላው የቤት ሥራችን መሆን አለበት፡፡

ለማንኛውም ጠላቶቻችንን ነገም ሌላ አጀንዳ ይዘውብን እንደሚመጡ ብናውቅም ደግሰውልን የነበረውን እጅግ አደገኛ ጥፋት ዛሬ ላይ እያሸነፍን የመጣነው በጋራ በመነሳታችን በመሆኑ አገርን እያለማን የሚነሱብን ጠላቶች በጋራ ማንበርከክ ልምዳችን ሊሆን ይገባል፡፡

ትብብራችን ጠላቶቻችንን ለማንበርከክ ብቻ አለመሆኑንም በማመን ከጦርነትና ከከፋፋይ አስተሳሰብ በመውጣት መተኪያ የሌላት አገራችንን በጋራ ክንዳችንና ትብብራችን እናስቀጥላት፡፡ እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለው የጋራ ድምፃችን ይሁን፡፡

ኢትዮጵያን እኛው መገንባትና ማልማት እንችላለን የሚባለው በእጃችን ያለውን ሀብት አስተማማኝ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ተባብረን ከሠራን ብዙ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የሰው ኃይልም ስላለን ጭምር ነው፡፡

ለአፍሪካውያንም ምሳሌ ሆነን የኢትዮጵያን ስም ነገም ለማስጠራት ትብብራችን ይቀጥላል ለዚህ ሁሉ በቅን ልቦና በቅን መንፈስ በኅብረት እንጓዝ!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት