Monday, February 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ በ400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ባለ 60 ፎቅ ሕንፃ ሊያስገነባ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ በርዝመቱ ከፍተኛ የሚባለውን ባለ 60 ፎቅ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ፣ በ400 ሚሊዮን ዶላር (አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ተመን 20 ቢሊዮን በላይ ይሆናል) በሆነ ወጪ ሊያስገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የመጀመርያው፣ በአፍሪካ ደግሞ ሦስተኛው ረዥሙ የሚሆነው የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም. ይጀመራል፡፡

የባንኩን ሕንፃ ለመገንባት በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ተወዳድረው፣ ‹‹ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ›› የተባለው ኩባንያ አሸናፊ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኩባያው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ረዥሙ የተባለውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመገንባት ላይ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ግዙፍ ግንባታዎችን በማካሄድ ይታወቃል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ መገንባቱ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ትልቁና ‹‹አደይ አበባ›› የሚል ስያሜ የተሰጠውን ብሔራዊ ስታዲዮም ከ2.47 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

የአቢሲኒያ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤትን ሕንፃ ለመገንባት ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበው ሌላ አንድ ኩባንያ ብቻ ነበር ተብሏል፡፡ ኩባንያውም ‹‹ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን›› የተባለው ኩባንያ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከባንኩ በተገኘው መረጃ መሠረት ለግንባታው መጀመርያ በወጣው ጨረታ ተሳታፊዎች ባለመቅረባቸው፣ በሁለተኛው ጨረታ ሁለቱ የቻይና ኮንትራክተሮች ቀርበው ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ የተሻለ ውጤት በማምጣቱ አሸናፊ ሊሆን መቻሉ ታውቋል፡፡   

ይህ የመዲናዋ ረዥሙ ሕንፃ ጠቅላላ ርዝማኔው 270 ሜትር መሆኑን የገለጹት አቶ በቃሉ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ካለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በ72 ሜትር ይበልጣል፤›› ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ከሦስቱ ረዣዥም ሕንፃዎች መካከል አንዱ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል፡፡  

የአቢሲኒያ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ አጠቃላይ የግንባታ ወጪው 400 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ ግንባታውን በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዟል፡፡

ባንኩ ሐሙስ ታኅሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዳስታወቀው፣ ሕንፃው የሚገነባው በልደታ ክፍለ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን በሚገኘው 9,763 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡ ከጨረታው አሸናፊ የቻይና ኩባንያ ጋር በዋጋና በሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ድርድር ተጠናቅቆ ውል ለመፈራረምና ወደ ሥራ ለመግባት ዝጅግት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ይህንን ሕንፃ ሊበልጡ የሚችሉት በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካና በግብፅ እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች ናቸው ተብሏል፡፡

የዚህ ግዙፍ ሕንፃ ግንባታ መጀመር አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ከማነቃቃትና የአገርን ገጽታ ከመገንባት አንፃር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ያመለከቱት አቶ በቃሉ፣ እንዲህ ያለ ግዙፍ ግንባታ በዚህ ወቅት መጀመሩ ለአገር ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት በዋና መሥሪያ ቤትነት የሚጠቀምበት ከአያት ሪል ስቴት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በገዛው ጅምር ሕንፃ ላይ ነው፡፡ ከዋና መሥሪያ ቤቱ ግንባታ በተጨማሪ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች 16 ይዞታዎች ያሉት መሆኑን፣ በእነዚህ ይዞታዎቹ ላይ ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ላይ ግንባታ መጀመሩ ታውቋል፡፡ በሌሎቹ ላይም ግንባታ ያካሂዳል ተብሏል፡፡ ከይዞታዎቹ መካከል አንዱ የሆነውንና ከአያት ሪል ስቴት የተረከበው ባለ15 ፎቅ ሕንፃ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ፣ ‹‹ጃንግሱ ኢንተርናሽናል ኢቲሲጂ›› ከተባለ የቻይና ኮንትራክተር ጋር ተዋውሎ የማጠናቀቂያ ሥራው እየተከናወነ ነው፡፡

አቢሲኒያ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን ከ103 ቢሊዮን ብር በላይ አድርሷል፡፡ የ2013 የሒሳብ ዓመት ከቀዳሚው ዓመት የ90 በመቶ ዕድገት ያሳየ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ከታክስ በፊት 2.05 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች