Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሶማሌ ክልል በድርቅ ምክንያት ከ146 ሺሕ በላይ እንስሳት መሞታቸው ተገለጸ

በሶማሌ ክልል በድርቅ ምክንያት ከ146 ሺሕ በላይ እንስሳት መሞታቸው ተገለጸ

ቀን:

  • ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 3.4 ሚሊዮን ከፍ ማለቱ ተገልጿል

በሱማሌ ክልል በሚገኙ 78 ወረዳዎች ላይ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በሁለት ወራት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከ146 ሺሕ በላይ ከብት፣ ግመልና ፍየሎች መሞታቸውን የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ከሚገኙት 11 ዞኖች ውስጥ በዘጠኙ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና በሲቲ ዞን ውስጥ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት፣ በክልሉ የሚገኙ ዕርዳታ ፈላጊ ዜጎች ቁጥር ወደ 3.4 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ ተገልጿል፡፡

የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ በሽር ዓረብ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙት 11 ዞኖች ውስጥ ዘጠኙ ዝናብ ያገኙ የነበሩት ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ በመኸርና በበልግ ወራት ነው፡፡ ይሁንና በ2013 ዓ.ም. ከሚያዝያ እስከ ሰኔ የቆየው የበልግ ወቅት የዘነበው ዝናብ ዝቅተኛ በመሆኑና አሁን እየተጠናቀቀ ባለው የመኸር ወቅት ሙሉ በሙሉ ባለመዝነቡ በክልሉ ውስጥ የተከሰተው ድርቅ ስድስት ወራት ሆኖታል፡፡ እነዚህ ዞኖች አሁን እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ወር ድረስ ማግኘት የነበረባቸውን ዝናብ ባለማግኘታቸውና ደረቅ የሆነው የበጋ ወቅት እየገባ በመሆኑ ድርቁ ይቀጥላል የሚል ሥጋት እንዳለ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህም ምክንያት አሁን በተከሰተው ድርቅ 3.4 ሚሊዮን የደረሰው የዕርዳታ ፈላጊ ዜጎች ቁጥር በትንሹ አራት ሚሊዮን ይደርሳል የሚል ግምት መቀመጡን አቶ በሽር ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው፣ ‹‹የሚቀጥሉት አራት ወራት ትልቅና ከባድ ፈተና እንደ ክልል ያጋጥመናል፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ያለው ድርቅ በተለይ በዳዋ፣ አፋሌር፣ ሸበሌና ኮራይ ዞኖች ተፅዕኖው እንደከፋ የተገለጸ ሲሆን፣ ድርቁን መቋቋም ያቃታቸውና አቅም ያላቸው ነዋሪዎች እንስሳቶቻቸውን በመኪና እየጫኑ ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ወደ ጅግጅጋ አቅራቢ መምጣታቸው ታውቋል፡፡ ይሁንና እንስሳቶቻቸው በድርቁ እጅጉን በመጎዳታቸው በጉዞ ላይ እያሉና ከመኪና ሲወርዱ ሕይወታቸው እያለፈ እንደሚገኝ አቶ በሽር ተናግረዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ዞኖች ላይ እየሞቱ ያሉት እንስሳት ቁጥር ሪፖርት ባለመደረጉ፣ ባለፉት ሦስት ወራት ገደማ ውስጥ የሞቱ እንስሳት ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የሶማሌ ክልል አስተዳደር ድርቁ እንደሚከሰት በማሰብ ባለፈው ዓመት ላይ ‹‹የድርቅ ምላሽ ዕቅድ›› እንዳዘጋጀ ያስታወሱት ቡድን መሪው፣ ዕቅዱ እንደ ጤና፣ ውኃና መጠለያ ባሉ ስምንት ዘርፎች የሚያስፈልገውን ሀብትና ዝግጅት የዳሰሰ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዕቅድ መሠረት በክልሉ በድርቁ የሚፈጠረውን ችግር መቅረፍ 60 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ እስካሁን ከመንግሥት፣ ከዓለም የምግብ ፕሮግራምና ከሌሎች ረጂዎች የተገኘው ግን ከ23 ሚሊዮን ዶላር የሚያልፍ አይደለም፡፡

ዕቅዱ ላይ የተፈጠረውን ከ33 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት ለመሙላት የክልሉ መንግሥት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ማፅደቁንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም 50 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የዕርዳታ ቁሳቁስ ለማቅረብ ቃል መግባቱን ተናግረዋል፡፡

በድርቁ ምክንያት ተፈናቅለው ለሚመጡ ሰዎች ዕርዳታ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ በሽር፣ የመጠጥ ውኃ፣ የእንስሳት መኖና ምግብ እጥረት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ የውኃ እጥረትን ለመቅረፍ የመኪና ቦቴዎችን በመከራየት ውኃ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፣ አንዳንድ ወረዳዎች ባላቸው ርቀትና የመንገድ ምቹ አለመሆን ምክንያት በታሰበው መጠን ውኃውን ለማቅረብ አይቻልም የሚል ሥጋት እንዳላቸው የቡድን መሪው ጠቁመዋል፡፡

አቶ በሽር፣ ክልሉ ቆላማና ሰብል በብዛት የማይመረትበት በመሆኑ የእንስሳት መኖ ችግርም እንዳለ የተናገሩ ሲሆን፣ የመኖ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ወደ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ጥሪ የማድረግ ሐሳብ እንዳለ አንስተዋል፡፡ ‹‹ይሁንና ኦሮሚያ ክልል ራሱ ቦረናና ጉጂ አካባቢዎች ድርቅ በመከሰቱ የተነሳ የመኖ ዕርዳታ ሊቀርብ የሚችው ከራሳቸው ከተረፈ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ የተገኘው ትንበያ፣ ከሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም. አንስቶ የሚገባው ቀጣዩ በልግ ላይ የሚኖረው የዝናብ መጠን ከመደበኛው ዝቅተኛ እንደሚሆን ማሳየቱ ታውቋል፡፡ ስለዚህም ድርቁ ከአንድ ዓመት በላይ ሊዘልቅ ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩን አቶ በሽር ዓረብ ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...