– በአውሮፓ ኅብረት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጄኔቫ በሚገኘው የተመድ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ዓርብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባካሄደው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ ላይ፣ የመንግሥታቸውን አቋም የተመለከተ ንግግር ያደረጉት በስዊዘርላንድ የኢትዮ አምባሳደር አቶ ዘነበ ከበደ፣ ታሪክ ራሱን ደግሞ ኢትዮጵያ ከ85 ዓመታት በኋላ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በተመድ የጄኔቫ ጽሕፈት ቤት መቆሟንና አሁንም ለባለብዙ ወገን የዓለም አስተዳደር ያላት ፅኑ እምነት፣ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ እንዳልረዳት ገለጹ።
ኢትዮጵያ የዓለም ሕዝቦች የጋራ ደኅንነት እንዲከበርና የጋራ ትብብርና የባለብዙ ወገን ሥርዓት የሰፈነበት ዓለም አቀፋዊ አስተዳደር እንዲሰፍን ባላት ፅኑ እምነት፣ የተባባሩት መንግሥታት መሥራች አገር እንደሆነች የገለጹት አምባሳደሩ፣ ከ85 ዓመታት በፊት በፋሽስታዊው የጣሊያን መንግሥት የተፈጸመባትን ወረራ፣ በጄኔቫ የዓለም መንግሥታት መድረክ ተገኝታ የደረሰባትን በደል በማቅረብ፣ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ያደረገችው ጥረት ሰሚ ጆሮ ማጣቱን አስታውሰዋል።
ከ85 ዓመታት በኋላ ዓርብ ታኅሳስ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በጄኔቭ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተገኘችው በተመሳሳይ ሁኔታ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እንደሆነ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥቷን ለመከላከል፣ ሰላምንና የወደፊት ሕዝቦቿን ዕጣ ፈንታ የማረጋገጥ መብቷን ለማስከበር በመሞከሯ፣ በሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ላይ ቀርባ የፖለቲካ ጥቃት እንዲደርስባት መደረጓን ተናግረዋል።
‹‹ከ85 ዓመታት በኋላ እዚህ ጄኔቫ ላይ ታሪክ ራሱን ደግሟል፡፡ ለባለብዙ ወገን ሥርዓት ለመፍጠር ያለን ቁርጠኝነት አገራችንን ለመጠበቅ አልረዳንም›› ያሉት አምባሰደሩ፣ ‹‹ከ85 ዓመታት በኋላም መልቲላተራሊዝም እንደገና በኒዮኮሎኒያሊስት አስተሳሰብ እየተጠለፈ ነው፤›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከውስጧ የተነሳ አዋኪ የገጠማት ቢሆንም፣ ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ለመፈጸም የሚተጉ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለመጫን ይህንን የውስጥ አዋኪ ኃይል በመደገፍ እያጎለበቱት እንደሚገኙና በዚህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እየፈተኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዘመናዊ ቅኝ ገዥዎች ምክንያት የበርካታ አገሮችን መፍረስንና አለመረጋጋት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያየን በመሆኑ በቃ ሊባል ይገባል ያሉት አምባሳደር ዘነበ፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ተልዕኮና ሥራ፣ የእነዚህ ኃይሎችን ድብቅ የፖለቲካ ዓላማዎች ማራመድ እንዳልሆነም በአጽንኦት ተናግረዋል።
‹‹ባለፈው የቅኝ ግዛት ወረራ ለመከላከል ብቻችንን ቆመን ነበር። ዛሬ ግን ብቻችንን አይደለንም። ኢትዮጵያ የገጠማትን ዓይን ያወጣ የፖለቲካ ጫና ከሌሎች አገሮች ጋር ተባብራ የባለብዙ ወገን የዓለም አስተዳደር እንዲሰፍን ትታገላለች፤›› ብለዋል።
በአውሮፓ ኅብረት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ለማጽደቅ በተሰጠው ድምፅ፣ የውሳኔ ሐሳቡ በ21 አገሮች ድጋፍ በ15 አገሮች ተቃውሞና በ11 አገሮች ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፀ ጸድቋል።
ውይይቱ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በተካሄደበት ወቅት፣ ካሜሮን የአፍሪካ ቡድንን በመወከል የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አፍሪካዊያን እንደሚቃወሙ ቢገለጽም፣ የተሰጠው ድምፅ ይፋ ሲደረግ ግን ከአፍሪካ አገሮች መካከል ሱዳን፣ ሴኔጋል፣ ሊቢያ፣ ማላዊና ቶጎ ድምፀ ተዓቅቦ ማድረጋቸው ታውቋል።
የፈቀደው የውሳኔ ሐሳብ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጋር በጥምረት ያደረጉት ምርመራ ውጤትን መነሻ በማድረግ፣ ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲሰማራ የሚወስን ነው።
ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድኑ የአንድ ዓመት ቆይታ እንዲኖረውና የሚላከው ቡድን ከሚያደርገው ምርመራ በተጨማሪ፣ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ የሚደረግበትን፣ እርቅና ተጠያቂነት የሚሰፍንበትን እንዲሁም፣ ሰብዓዊ ጥሰት የደረሰባቸው ማገገም እንዲችሉ ምክረ ሐሳብና የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት እንደሚኖረውም ይገልጻል።
የውሳኔ ሐሳቡ ቢፀድቅም የኢትዮጵያ አምባሳደር ውይይቱ ሲጀመር አንስቶ የውሳኔ ሐሳቡ ቢፀድቅ እንኳን፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጸዋል።