ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ምክንያት በማድረግ የውጭ አገር ዜጎች የሆኑ መምህራኖቻቸው የወጡባቸው አምስት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች፣ በከፊል የኦንላይን ትምህርት እንዲሰጡ ፈቃድ መስጠቱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በኦንላይን እንዲያስተምሩ ፈቃድ የተሰጣቸው ሳንፎርድ፣ አይሲኤስ፣ ሊሴ ገብረማርያም፣ ጀርመንና ቤንግሃም የተባሉት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ መምህራኖቻቸው የውጭ አገር ዜጋ እንደሆኑ በሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራት ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አሁን በኦንላይን እንዲያስተምሩ ፈቃድ ከሰተጣቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሦስቱ ትምህርት በማቋረጣቸው ምክንያት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የነበሩ ናቸው፡፡
የአሜሪካ፣ ፈረንሣይና ጀርመን ትምህርት ቤቶች መምህራኖቻቸው ከአገር የወጡት በኤምባሲያቸው ጥያቄ እንደሆነ የተናገሩት ሙሉቀን (ዶ/ር)፣ የትምህርት ቤቶቹ አስተዳደሮች ሌላ መምህራንን መተካት መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡ የመምህራኖቻቸውን መሄድ ተከትሎ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶቹ የመማር ማስተማር ሒደቱን ሙሉ ለሙሉ ሊያቋርጡ እንደነበርም ሙሉቀን (ዶ/ር) አክለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚያስረዱት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ባላቸው ‹‹ከፍ ያለ›› ደረጃ ምክንያት፣ የሚቀጥሩትም ዓለም አቀፍ ምዘና ወስደው የምስክር ወረቀት ያላቸው መምህራንን ነው፡፡ ‹‹ይኼንን በቶሎ ማድረግ እንደማይችሉ ከተነጋገርን በኋላ መምህራንን እስኪቀጥሩ ድረስ በከፊል በኦንላይን እንዲያስተምሩ ፈቅደንላቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
ትምህርት ቤቶቹ በኦንላይን ማስተማር ቢፈቀድላቸውም ቅጥር ግቢያቸውን መዝጋት እንደማይችሉና ለተማሪና ለመምህራኖቻቸው ክፍት የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ ሙሉቀን (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፣ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማር ማስተማር ሥራው እየተካሄደ ያለው ቅይጥ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ከአገር የወጡ መምህራኖቻቸው ካሉበት የኦንላይን ትምህርት ሲሰጡ ኢትጵያዊ መምህራን ደግሞ በግቢ ውስጥ የገጽ ለገጽ ትምህርቱን እንደቀጠሉ ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ተማሪዎቹ የኦንላይን ትምህርቱንም ቢሆን በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ እንዲከታተሉ ነው የተነጋገርነው፤›› ብለዋል፡፡
ጥቅምት ወር ላይ አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣሉን ተከትሎ፣ ጥቂት የማይባሉ አገሮች ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ያሳሰቡ ሲሆን፣ አሜሪካ፣ ፈረንሣይና ጀርመን ከእነዚህ አገሮች መካከል ናቸው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ይኼንን ተከትሎ ትምህርት መስጠት ላቋረጡት ሳንፎርድ፣ ቤንግሃምና አይሲኤስ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሰጥቶ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሚኒስቴሩ ያለ በቂ ምክንያት የትምህርት ሥራውን ማቆም እንደማይችሉ ለሰባት የማኅበረሰብና 19 ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች እንዳስታወቀ ገልጿል፡፡
ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) እንደተናገሩት የትምህርት ቤቶቹ ከአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት በዓል በኋላ፣ መምህራኖቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ የሚል እምነት ስላላቸው ሚኒስቴሩ የመምህራን መቅጠሪያ ጊዜ ላይ ገደብ አላስቀመጠም፡፡ እንደተጠበቀው መምህራኑ በተባለው ጊዜ የማይመለሱ ከሆነ ትምህርት ሚኒስቴር ተወያይቶ ዕርምጃ እንደሚወስድ የትምህርት ጥራት ዳይሬክተር ጄኔራሉ አስታውቀዋል፡፡