የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንዲበራከት የራሳቸው የሆነ ድርሻ አላቸው የተባሉ በድንበር አካባቢ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች፣ ከድንበር ምን ያህል ርቀት ላይ ሊገነቡ ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ ምክረ ሐሳብ ቀረበ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተጠናቀቀው ሳምንት አስቀድሞ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ምርቱ ለከፍተኛ ኮንትሮባንድ ንግድ የተጋለጠ በመሆኑ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ክለሳ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ሕግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በተለይ በ2011 ዓ.ም. ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለቁጥጥር አዳግቶ ነበር፡፡ ይህም የሆነው ኢትዮጵያ ያላት መልክዓ ምድርና ከጎረቤት አገሮች ጋር የድንበር ተዋሳኝነት ለነዳጅ ኮንትሮባንድ መስፋፋት የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ስለፈጠረ ነው፡፡
ሆኖም በ2011 ዓ.ም. ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ውሳኔ የንግድ ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የቀድሞው የማዕድንና የነዳጅ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን ነዳጅ እንዲያጓጉዙ ስምሪት የተሰጣቸው ተሽከርካሪዎችን የመቆጣጠር ሥራ (ዲስፓች ኮንትሮል) ተፈጥሮ እንደነበር አስታውቀው፣ የጋራ ጥምረቱ ነዳጅን ድንበር ላይ ሳይሆን ገና ተሽከርካሪዎቹ አቅጣጫ ሲቀይሩ ይይዟቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡በዚህም መንገድ በወቅቱ ትልቅ ሥጋት በመፍጠር ኮንትሮባንዲስቶችን አደብ ማስገዛት ተችሎ ነበር፡፡
ዘዴው እንደማያፈናፍናቸው የተረዱት ኮንትሮባንዲስቶች ሌላ ዘዴ እንዳመጡ ያስታወቁት አቶ ሙሉጌታ፣ ዘዴው ስምሪት የተሰጣቸው ተሽከርካሪዎች አቅጣጫ ሳይቀይሩ ሄደው ድንበር ላይ ባሉ ማደያዎች ምርቱ እንዲከማች ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ድንበር ላይ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ምርቱ እየተከማቸ በበርሜል በቀላሉ ወደ ጎረቤት አገሮች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚወጣበት መንገድ አንዱ የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ መልክ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ድንበር አካባቢ የሚተከሉ ማደያዎች ፍቃድ እንዴት መሰጠት ይገባል የሚለውን በአገር ዓቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ እየተከታታለው እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር የምትዋሰንበት ድንበር የተያያዘና ቅርብ ስለሆነ ተቀባይ አካላት ድንበር ላይ ስለሚገኙ በቀላሉ ነዳጅ ከአገር የሚወጣበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በሶማሌላንድ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ማደያ ያላቸው አካላት እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፣ ከዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ በይፋ የሚታወቁ ሲሆኑ በይፋ የማይታወቁም አሉ፡፡ባለቤታቸው የማይታወቁት ማደያዎች የማናቸው? የሚለው በምርመራ የሚታወቅ ይሆናል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በኢትዮጵያ ድንበርም ሆነ በሌላኛው የጎረቤት አገር የሚገኙት ማደያዎች በግልፅ የሚታይ ግንኙነት ባይኖራቸውም ድርጊቱን የሚያቀላጥፉበት ስውር ጉዳይ እንዳለ መረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡
የነዳጅ ኮንትሮባንድን ድንበር ላይ ቁጭ ብለን እንከላከል ከማለት ባለፈ ሥርዓት መስፈን ይገባዋል ያሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ማደያዎች በድንበር አካባቢ በምን ያህል ርቀት ነው ሊከፈቱ የሚገባው የሚል ሥርዓት ሊበጅ ስለሚገባ ጉዳዩ በዚህ ወቅት በጥናት መልክ ተዘጋጅቶ እንደቀረበ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከጎረቤት አገሮች ጋር በጉዳይ ላይ በቅንጅት ሊሠራበት እንደሚገባ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በሌላ በኩልም ድንበር አካባቢ ላሉ ከተሞች የሚገባው የነዳጅ ኮታ የሚመጥን ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ፍቃድ የሚሰጠው አካል ሊሠራበት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች በተመለከተ ጉዳዮ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የጋራ ጥናት ማድረጋቸውን ተገልጿል፡፡
የጋራ ጥናቱ ድርጊቱን ለመከላከል ከጉምሩክ ቁጥጥር አንስቶ እስከ ሕግ አተገባባር ያሉትን በማስቀመጥ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች የዳሰሰ ጥናት እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
የጋራ ዳሰሳ ጥናቱን መሠረት ተደርጎ እየተወሰዱ ያሉና ወደ ፊት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ለአብነትም በጅግጅጋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ላይ የነዳጅ ኮንትሮባንድ የመያዝ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነና፣ ምርቱ በተጠናከረ መጠን እየተያዘ በሄደ ቁጥር በኮንትሮባንዲስቶቹ ላይ ሥጋት ስለሚፈጠር ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡