Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የከተማ አስተዳደሩ ያልተመለሱ መሥሪያ ቦታዎችን በተመለከተ ውሳኔ ለማሳለፍ መቸገሩን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • አንዳንዶቹ ቦታዎች ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ የተያዙ መሆናቸው ታውቋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳር ለአምስት ዓመታት በሚቆይ የኪራይ ውል ለኢንተርፕራይዞች ተሰጥተው ሳይመለሱ ዓመታትን ያስቆጠሩ በተለምዶ አርከበ ሱቅ በመባል የሚታወቁ የመሥሪያ ቦታዎችን በተመለከተ ውሳኔ ለማሳለፍ መቸገሩ ተገለጸ፡፡

የመሥሪያ ቦታዎቹ ለሌሎች ቦታ ፈላጊዎች መተላለፍ የነበረባቸው ቢሆንም አሁን የያዟቸው ኢንተርፕራይዞች፣ ‹‹ሌላ ቦታ የምንከራይበት አቅም የለንም፤›› በማለታቸው፣ አንዳንዶቹ መሥሪያ ቦታዎች በአንድ ኢንተርፕራይዝ ተይዘው ከ10 ዓመት በላይ ማስቆጠራቸው ታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በሥራ ፈጠራ ለተደራጁ ከአሥር ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች እንደ ሼድ፣ የማኑፋክቸሪንግ ሕንፃና የኮንዶሚኒየም ንግድ ሱቆችን ጨምሮ 4,100 በላይ ቦታዎችን በዝቅተኛ ኪራይ መስጠቱን፣ የአስተዳደሩ የመሥሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስመሮም ብርሃኔ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩ ቦታዎቹን የሰጠው ኢንተርፕራይዞቹ በአምስት ዓመት ውስጥ አቅም ፈጥረው በመልቀቅ ለአዲስ ኢንተርፕራይዞች እንዲያስረክቡ ታስቦ ቢሆንም፣ ቦታ ከተሰጣቸው ከአሥር ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ ከ4,100 በላዩ አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ እንደሆናቸው አስረድተዋል፡፡ ሳይመለሱ ቆይተዋል የተባሉት ቦታዎች ከ290 ሺሕ በላይ ካሬ ሜትር እንደሆኑም ታውቀዋል፡፡

የኪራይ ጊዜያቸው ካለፈ ኢንተርፕራይዞች ውስጥም 894 ያህሉ ቦታውን ይዘው ከአሥር ዓመታት በላይ እንደሆናቸውና አንዳንዶቹ ይኼ አሠራር መተግበር ከጀመረበት ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ መሥሪያ ቦታውን ይዘው እንደቆዩ ተገልጿል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ይኼንን አሠራር የተገበረው ኢንተርፕራይዞቹን ለመደገፍ እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው፣ መሥሪያ ቦታዎቹ የተከራዩበት ከፍተኛ ዋጋ በካሬ ሜትር 50 ብር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ አራተኛ ዓመታቸው ላይ እስኪደርሱም የኪራይ ዋጋውን ሙሉ ለሙሉ እንደማይከፍሉ አክለዋል፡፡

ይሁንና በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የያዙትን ቦታ ሳይመልሱ አምስት ዓመት አልፏቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን ላይ በከተማዋ ለሚገኙ የመሥሪያ ቦታ ፈላጊ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ቦታ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ ‹‹ቦታ ፈላጊ ወጣቶች ተጠቅመዋል ይበቃቸዋል፤›› ሲሉ እነሱ ደግሞ፣ ‹‹የት እንሄዳለን ይላሉ፤›› በማለት የተናገሩት አቶ አስመሮም፣ በዚህ የተነሳ የከተማ አስተዳደሩ ለዓመታት ውሳኔ ለማሳለፍ ተቸግሮ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ ብዙዎቹ ኢንተርፕራይዞች አሁን ካሉበት የመሥሪያ ቦታ ቢለቁ ሌላ ቦታ ላይ የሚቋቋሙበትን አቅም አልፈጠሩም፡፡ በዚህም የተነሳ ከዚህ በፊት መሥሪያ ቦታ እንዲለቁ ከተደረጉት ኢንተርፕራይዞች ውስጥ አብዛኛዎቹ እንደከሰሙ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ሌላ ግን የአንዳንድ ኢንተርፕራይዞች አባላት በኪራይ የተሰጣቸውን ቦታ ለሌሎች በማከራየት ተጨማሪ ጥቅም እያገኙ መሆኑ እንደተደረሰበት ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ከኢንተርፕራይዞቹ ቦታውን የተከራዩት ሰዎች እየተንቀሳቀሱ ያሉት ቦታው በተሰጣቸው ኢንተርፕራይች ንግድ ፈቃድ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ለይቶ ዕርምጃ ለመውሰድ መቸገሩን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የአራት ወራት ሥራ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት የምክር ቤቱ አባላት ይኼ ችግር መፍትሔ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ይኼ ችግር ባለበት ሊቀጥል እንደማይገባ ተናግረው፣ የመሥሪያ ቦታ የያዙ ኢንተርፕራይዞችንና አዲስ የመሥሪያ ቦታ ፈላጊዎችን ችግር የሚፈታ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲቀርብ አሳስበዋል፡፡

የመሥሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስመሮም ብርሃኔ፣ ቢሮው የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ ጥናት ማድረጉን ያስታወቁ ሲሆን፣ በቅርቡ ለካቢኔ አባላት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አስመሮም ገለጻ፣ አሁን ላይ ከተማ ውስጥ የመሥሪያ ቦታ ከማቅረብ ይልቅ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ለኢንተርፕራይዞች የሚሆን ኢንደስትሪ ፓርክ መገንባት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር እንደዚህ ዓይነት ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 100 ሔክታር መሬት መረከቡን ያስታወቁ ሲሆን ዲዛይኑ ተሠርቶ ማለቁንም ተናግረዋል፡፡

ገንብቶ ለማጠናቀቅ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ይጠይቃል የተባለው ይኼ የኢንዱስትሪ ፓርክ የከተማ አስተዳደሩ ከያዛቸው አሥር ገደማ ሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች