Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ90 በመቶ በላይ ማድረሱን ገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት በተለያዩ የባንክ አገልግሎቶች እስከ 200 በመቶ የሆነ አፈጻጸም በማሳት የትርፍ ምጣኔውን ከ90 በመቶ በላይ ማድረሱን ገለጸ፡፡

ባንኩ የ2013 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደታወቀው፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በማሻገር ሁለተኛው የግል ባንክ መሆን ችሏል፡፡

ባንኩ አገልግሎት እየሰጠባቸው ባሉ ዘርፎች ሁሉ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበበትን ውጤትም በዝርዝር አቅርቧል፡፡

ከቀረበው ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ፣ የሰጠው ብድር፣ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ፣ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውና በሌሎች የባንኩ የአገልግሎት ዘርፎች ያስመዘገበው ውጤት ከአምናው ከ76 በመቶ እስከ 200 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውንም በ90 በመቶ በማሳደግ ከታክስ በፊት 2.05 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡

በቀድሞው የፕላንና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ መኮንን ማንያዘዋል የቦርድ ሊቀመንበርነትና በቀድሞው የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ፕሬዚዳንትነት እየተመራ ያለው አቢሲኒያ ባንክ፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ አፈጻጸም ካሳየባቸው መካከል አንዱ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ዕድገት ሲሆን፣ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም 88.8 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡    

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ማንያዘዋል ባቀረቡት ሪፖርት፣ ለአንድ የንግድ ባንክ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ዋነኛ መሠረቱ ተቀማጭ ገንዘብን ማሳደግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባንካቸው ተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ላይ ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጦ በመንቀሳቀሱ ከዓመት ዓመት የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ በ2013 ሒሳብ ዓመት የተሰበሰበውን ተቀማጭ ገንዘብ አምና ከተሰበሰበው በሦስት እጥፍ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

እጅግ የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበበት ነው የተባለው የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ከቀዳሚው ዓመት የ41.25 ቢሊዮን ብር ወይም 86.6 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ይህም አጠቃላይ የባንኩን ተቀማጭ ገንዘብ መጠን አምና ከነበረው ከ47.63 ቢሊዮን ብር ወደ 88.88 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አስችሎታል፡፡

‹‹ከተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የቁጠባ ሒሳብ ድርሻ 65.5 በመቶ በመያዙ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ እንዳይዋዥቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህም ባንካችን በትክክለኛ የዕድገት ጎዳና ላይ እንዳለ አመላካች ነው፤›› ያሉት አቶ መኮንን፣ ከተሰበሰበው አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ 9.3 በመቶ ድርሻ የያዘው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተቀማጭ ገንዘብ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል የሚቻለው በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ስኬት ላይ ተመሥርቶ በመሆኑ እንደተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት ሁሉ፣ በ2014 ሒሳብ ዓመትም ተቀማጭ ገንዘብ የማሰባሰቡ ሒደት ላይ ባንኩ ጠንክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ አዳዲስ ባንኮች ወደ ገበያው የሚገቡ ከመሆኑ አንፃርና በተጨባጭ ካለው ከፍተኛ ፉክክርና ኢትዮጵያ ካለችበት ውስብሰብ ችግር አኳያ ፈታኝ ቢሆንም፣ ባንኩ በዋናነት ዘመናዊ የባንክ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግና የላቀ አገልግሎት በመስጠት ተመራጭና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመጓዝ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡

ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠንም በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት የታየበትና በቀዳሚው ዓመት ከሰጠው ከእጥፍ በላይ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም. ባንኩ የሰጠው ብድር የ105.9 በመቶ ወይም የ39.4 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ሲያሳይ፣ የብድር ክምችቱ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 76.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ባንኮች ከብድር አመላለስ ጋር በርካታ ተግዳሮቶች እየገጠማቸው መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን፣ አቢሲኒያ ባንክ ግን በዚህ ረገድ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ በሒሳብ ዓመቱ ለብድር ከሰጠው ገንዘብ 12.99 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የጠቆሙት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ፣ ይህ የብድር አመላለስ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 200 በመቶ ወይም የ8.72 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡  

በውጭ ምንዛሪ ግኝት ረገድም ያስመዘገበው ዕድገት በኢንዱስትሪው ከታየው በእጅጉ ከፍ ያለ ስለመሆኑ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡ ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ 753.16 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ352.85 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ88 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡

በውጭ ምንዛሪ ግኝት አብዛኛዎቹ ባንኮች ዕድገት ከ30 በመቶ የዘለለ ካለመሆኑ አንፃር፣ የአቢሲኒያ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዕድገት በቀዳሚነት እንዲቀመጥ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ የሀብት መጠኑን ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለ ሁለተኛው የግል ባንክ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ የደረሰበት አጠቃላይ የሀብት መጠን 103.5 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ከነበረው 56.89 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ46.96 ቢሊዮን ብር ወይም የ82.5 በመቶ ዕድገት አለው፡፡ ከአጠቃላይ የሀብት መጠኑ ውስጥ ብድርና ቅድመ ክፍያ 75.45 ቢሊዮን ብር፣ ጥሬ ገንዘብና ገንዘብ አከል ሀብት 12.1 ቢሊዮን ብር፣ የብሔራዊ ባንክን ቢል ጨምሮ የተደረጉ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች 7.52 ቢሊዮን ብር፣ ቋሚ ንብረት 5.73 ቢሊዮን ብርና ሌሎች 3.03 ቢሊዮን ብር ድርሻ ይዘዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ ካፒታል ወደ 8.65 ቢሊዮን ከፍ ማለቱን የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አኃዝ ጋር ሲነፃፀር የ2.97 ቢሊዮን ብር ወይም የ52.35 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ መቁሟል፡፡

የተከፈለ ካፒታል መጠኑን ደግሞ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው ከ3.15 ቢሊዮን ብር ወደ 5.18 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ባንኩ የደረሰበት የተከፈለ የካፒታል መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ64.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ባንኩ የሒሳብ ዓመቱ ጠቅላላ ገቢውን ለመጀመርያ ጊዜ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለ ሲሆን፣ በዓመቱ ውስጥ ያስመዘገበው ጠቅላላ ገቢ 10.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ4.4 ቢሊዮን ብር ወይም የ79 በመቶ ዕድገት አለው፡፡ ይህንንም በዋና ዋና የገቢ ምንጮች ውስጥ ከብድር ወለድ የተገኘ ገቢ 77 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡ ከአገልግሎት ክፍያ 15 በመቶ፣ እንዲሁም ከኮሚሽን ገቢ ስምንት በመቶ ሲሆን ቀሪ ከሌሎች የገቢ ምንጮች የተገኙ ናቸው፡፡

በ2013 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ የባንኩ ጠቅላላ ወጪ 8.15 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚያመለክተው ሪፖርት፣ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ከተመዘገበው ወጪ አንፃር የ3.56 ቢሊዮን ብር ወይም የ77.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ወጪ መጨመር በዋናነት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በማደጉ ነው፡፡ ይህ ለአስቀማጮች የተከፈለው ወለድ ከባንኩ ዓመታዊ ጠቅላላ ወጪ የ33 በመቶ ድርሻ ድርሻ ይዟል፡፡ ለሠራተኞች የተከፈለው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የ39.6 በመቶ፣ ለቅርንጫፎች የሚከፈለው የኪራይ ወጪን ጨምሮ ለአጠቃላይ አስተዳደራዊ ወጪዎች 16.6 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውም ከታክስ በፊት 2.05 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ90 በመቶ ዕድገት አለው፡፡ እስካሁን ሪፖርታቸውን ካቀረቡት ባንኮች ሁሉ ከፍተኛው የትርፍ ዕድገት መጠንም ነው፡፡

ከአቢሲኒያ ቀጥሎ ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት ያሳየው ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፍ ዕድገቱ 61 በመቶ ነው፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ መጠን ዕድገት አንድ አክሲዮን የሚያስገኘውን ትርፍ ምጣኔም ከቀደሙት ዓመታት የበለጠ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በአጠቃላይ ከ45.7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

እነዚህም ድጋፎች ለአዲስ አበባ ከተማ ተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፣ ለተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ለመንግሥትና ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተሰጡ ይገኙበታል፡፡   

አቢሲኒያ ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 97 አዳዲስ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 608 አድርሶታል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት 8,146 ሠራተኞች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች