Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጎምቱዎቹ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች የዕውቅናና የክብር ኒሻን ተሸለሙ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በማገልገልና ለኢንዱስትሪው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁለት ጎምቱ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች የሕይወት ዘመን አስተዋጽኦ የዕውቅናና የብር ኒሻን የክብር ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡

ይህ የክብር ሽልማት የተበረከተላቸው አንጋፋዎቹ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉና አቶ ፀጋዬ አምሲ ሲሆኑ፣ ዕውቅናውንም የሰጣቸው የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ነው፡፡

ማኅበሩ ለሪፖርተር በላከው መረጃ፣ ሁለቱም በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መሆናቸውን ገልጾ፣ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ከ58 ዓመታት በላይ፣ አቶ ፀጋዬ አምሲ ደግሞ ከ46 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ስለመሆናቸው አመልክቷል፡፡

ለሁለቱ ጎምቱ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች የተበረከተውን የብር ኒሻን የክብር ሽልማት ያበረከቱላቸው የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ያሬድ ሞላ ናቸው፡፡

 የዕውቅና የሽልማት ፕሮግራሙን አስመልክቶ ማኅበሩ በላከው መግለጫ፣ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ለባለሙያዎች ዕውቅና የሚሰጥ መርሐ ግብር ከኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ለረዥም ጊዜ ይጠብቁ እንደነበር ገልጸው፣ ይህንን ለመጀመርያ ጊዜ ላዘጋጁት የመድን ሰጪ ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባላት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪዎች በሌሎች አገሮች እንዲገኙና የመድን ኢንዱስትሪው የራሱ የሆነና ገለልተኛ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዲኖረው ለረዥም ዘመን መታገላቸውን ገልጸዋል፡፡

ጥረታቸው በመንግሥት ተቀባይነት እንዲያገኝ እንደሚገፉበትና ማኅበሩም በዚህ ጥረት መግፋት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

 አቶ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ እንዲህ ያለው ዕውቅናና ሽልማት መበረታታትና መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ዕውቅናና ሽልማት የመስጠት ጅምሩ ከታች ያሉትን ወጣት ባለሙያዎች እንደሚያበረታታና በተሻለ መልኩ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አክለዋል፡፡

የኢንሹራንስ ባለሙያዎቹ በተለይ ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ አንጋፋ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመመሥረትና በመምራት የበለጠ የሚታወቁ ናቸው፡፡ አቶ ፀጋዬ አዋሽ ኢንሹራንስን ከምሥረታው ጥንስስ ጀምሮ በማደራጀትና ከ25 ዓመታት በላይ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት በመምራት የዘለቁ ናቸው፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ደግሞ የኅብረት ኢንሹራንስ ዋነኛ መሥራች፣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚና የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ማገልገላቸው በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ አቶ ፀጋዬ በአዋሽ ኢንሹራንስን ከ25 ዓመታት በላይ ካገለገሉ በኋላ በክብር የተሸኙ ሲሆን፣ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ደግሞ በዋናነት በኅብረት ኢንሹራስ የተመሠረተውን ኅብረት ባንክ አሁንም በቦርድ ሊቀመንበርነት እየመሩ ናቸው፡፡

ማኅበሩ እንዲህ ያለውን የዕውቅና ፕሮግራም በየዓመቱ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች