Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገድና ተፅዕኖዎቹን የመቋቋሚያ መንገዶች

የኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገድና ተፅዕኖዎቹን የመቋቋሚያ መንገዶች

ቀን:

በአዲሱ አበባው ደጉ

የአፍሪካ ዕድገት ከቀረጥ ነፃ ዕድል የንግድ ሥርዓት አጎዋ (African Growth and Opportunity Act)፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮችና በአሜሪካ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግና የአፍሪካ አገሮችን የውጭ ንግድ ለማሳደግ ታስቦ በአሜሪካ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2000 የፀደቀ አዋጅ ነው። አዋጁ በየጊዜው እየታደሰ ለበርካታ ዓመታት የአፍሪካ አገሮች ልዩ ከቀረጥ ነፃ ዕድል የንግድ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህም በርካታ የአፍሪካ አገሮች እንደ የቆዳ ምርቶች፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ማሽኖች፣ መለዋወጫዎችና ሌሎች በርካታ የግብርና ውጤቶችን ዝቅተኛውን የጥራትና የአመራረት ደረጃ ማሟላታቸው ተረጋገጦ ወደ አሜሪካ እንዲልኩና የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ኢትዮጵያም ከ20 ዓመታት በላይ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ስትሆን ቆይታለች።

በዚህም እንደ ልብስ፣ ጫማ፣ ጨርቃ ጨርቅና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን ጨምሮ ቡና፣ አትክልቶችንና አበባ ስትልክ ቆይታለች። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ምርቶች አብዛኞቹ በአጎዋ በኩል የሚላኩ ናቸው። ይሁን እንጂ ከሰሞኑ በሰሜን የአገራችን ክፍል ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል በሚል ምክንያት፣ የአሜሪካ መንግሥት ከመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት እንደሚያግድ አስታውቋል። የክልከላው መንስዔ ደግሞ ከኢኮኖሚያዊነቱ ይልቅ ከፖለቲካዊነቱ ጋር የተያያዘ መሆኑ ግልጽ ነው።

ክልከላውን ተከትሎ ምርቶቻቸውን በአጎዋ በኩል ወደ ውጭ የሚልኩ የአገር ውስጥ አምራቾችን በተለይ፣ እንዲሁም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንደ አጠቃላይ ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ወድቀዋል። ከእነዚህም መካከል በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርቱ አምራቾች ይገኙበታል። አምራቾች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ካፒታል በማንቀሳቀስና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት እየተፍገመገመ ለሚገኘው የአገራችን ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሲያስገኙ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት መውጣት እስከ 200 ሺሕ በሚደርሱ ዜጎች ሕይወት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር፣ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት መውጣት አምራቾችን፣ ብሎም ኢኮኖሚውን ክፉኛ እንደሚጎዳው ዕሙን ነው። በመሆኑም የአጎዋንና መሰል ተፅዕኖዎችን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መፍጠር የአገሪቱን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ከማስቀጠል አንፃር ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አጎዋን የመሳሰሉ ዕድሎች ይዘውት ከሚመጡት ጥቅም ጎን ለጎን እንደ ፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያነትም ሊያገለግሉ ይችላሉ፣ አሁንም እየሆነ ያለው ይኼው ነው፡፡ የአጎዋ ሥርዓት ቅድመ ሁኔታዎችና የዕድሉ ተጠቃሚ አገሮች በየጊዜው በአሜሪካ መንግሥት የሚከለሱ እንደ መሆናቸው መጠን፣ የአጎዋ ዕድል አስተማማኝና ዘላቂ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም በአሜሪካ መንግሥት ይሁንታና በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ 

እንደ አጎዋ ክልከላ ዓይነት ክስተት ሲገጥም በአገር ውስጥ ያለውን ገበያ በማጠናከርና ለምርቶቹ ተጠቃሚ መፍጠር እንደ አማራጭ ሊታይ ይችላል። በአገራችን ገበያ ውስጥ የሚገኙ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች አብዛኞቹ ከውጭ አገር የሚገቡ (በኮንትሮባንድም ይሁን በሕጋዊነት) መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል። ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል (በኮንትሮባንድ የሚገቡ ከሆነ ደግሞ ለጥቁር ገበያ መስፋፋት ምክንያት ይሆናሉ)። የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ አገሪቱ ከውጭ ንግድ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ እስከ  80  በመቶ የሚሆነው ከግብርና ውጤቶች፣ ቀሪው  20  በመቶ ደግሞ ከሌሎች ዘርፎች የሚሸፈን ነው፡፡  የውጭ ንግድ ሁኔታዋ ሲታይ ወደ ውጭ ልካ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ለማስገባት የምትከፍለውን  37.5  በመቶ ብቻ ይይዛል (ሙሉ መረጃውን ከዓለም ባንክ ድረ ገጽ ማግኘት ይቻላል)፡፡

ይህ የሚያሳየው አገሪቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያልተስተካከለ የንግድ ሚዛን እንዳላት፣ ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ በበለጠ ከውጭ ለምታስገባቸው ምርቶች ግዥ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ የላቀ መሆኑን ነው። ይህንን የተዛባ የውጭ ንግድ ሚዛን ለማስተካከል ከሚያገለግሉ መንገዶች መካከል ‘ከውጭ በግዥ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ሥልት’ (Import Substitution Strategy) ይገኝበታል። ሐሳቡ በአገር በቀል ሀብት፣ ጉልበትና ዕውቀት ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በመገደብና በአገር ውስጥ በማምረት የመተካት ሥራ ማከናወን ነው።

በእርግጥ ይህ ዓይነቱ ሥልት አሁን ዓለማችን እየተከተለች ካለችው የነፃ ንግድ ሥርዓት (ቢያንስ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ) አንፃር ሲታይ አብሮ አይሄድም። ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ከአጎዋ ተጠቃሚነት የመከልከል ችግር ይኸንኑ ሥልት በመጠቀም ልታቃልል የምትችልበት ዕድል አለ። ከላይ እንደተመለከትነው ኢትዮጵያ የአጎዋን ዕድል በመጠቀም ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች ይገኙበታል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምርቶች በአገር ውስጥ ቢመረቱም፣ ግን በተመሳሳይ ጊዜ በርካታ ከውጭ የሚገቡ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች የአገር ውስጥ ገበያውን አጥለቅልቀውት እንመለከታለን። ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ደግሞ በርካታ የውጭ ምንዛሪ ፈሰስ ይደረግበታል፣ እንቆቅልሹም ያለው እዚህ ላይ ነው።

አንድ ምርትን ምርት በአገር ውስጥ ማምረት ከተቻለ ለምንድነው ከውጭ ዶላር ከፍሎ ማስገባት የሚያስፈልገው? በእርግጥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በውስብስብ ማሽኖች እንደ መመረታቸው መጠን፣ በጥራትም ይሁን በዋጋ ረገድ የተሻሉ መሆናቸው ዕሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዘለቄታዊ የአገር ዕድገትንና የወደፊቱን ልማት ከግምት ውስጥ እስካስገባን ድረስ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስና በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች የመተካት ሥራ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። አብዛኞቹ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች መሠረታዊ የሚባሉ እንደ መሆናቸው መጠን፣ ደረጃቸውን ጠብቀው በተጠቃሚው ፍላጎት ልክ ከተመረቱ የማይነጥፍ የአገር ውስጥ የገበያ ዕድል ይኖራቸዋል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቴክኖሎጂ መሻሻልና ከአሠራር መዘመን ጋር ተያይዞ የሚመረቱ የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ተወዳዳሪ መሆን ችለዋል (ኢትዮጵያ የተጠቀሱትን ምርቶች ከአሜሪካ በተጨማሪ ወደ ቻይና፣ ጣሊያን፣ ታይላንድ፣ ህንድ፣ ሆንግ ኮንግ፣ እንግሊዝና ወደ ሌሎችም ትልካለች)። ታዲያ የአገር ውስጥ የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ምርት ፍላጎትን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ቢቻል በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ማዳን ይቻል ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ዘርፉን በማበረታታት ከፍተኛ ሀብት መፍጠር፣ ቴክኖሎጂን በማላመድ ማጎልበት፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ እንዲሁም የማምረት አቅምን ማጎልበት ይቻላል። ለምሳሌ አንድን የጫማ ማምረቻ ድርጅት ብንወስድ ጫማ ለማምረት እንደ ቆዳ፣ ጨርቅ፣ ክር፣ ማጣበቂያ ማስቲሽ፣ የጫማ ሶልና የመሳሰሉት ግብዓቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹን ግብዓቶች ደግሞ በአገር ውስጥ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ በዚህም በተለያዩ የምርት ደረጃዎች የሚገኙና ጥሬ ዕቃዎቹን የሚያቀርቡና ጫማዎቹን የሚያመርቱ ሠራተኞች የግድ ስለሚያስፈልጉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም የጫማ ፍላጎት ከውጭ አገር በግዥ መልክ በማስገባት የምናሟላ ከሆነ፣ ከላይ የተጠቀሱት በርካታ ጥቅሞች ሁሉ ይቀራሉ ማለት ነው፡፡

አብዛኞቹ ፈጣን ዕድገትያስመዘገቡ የቆዩ የእስያ አገሮችን (ለምሳሌ ቻይናና ህንድን ጨምሮ ሌሎች የሩቅ ምሥራቅ አገሮች) ልምድ ብንመለከት፣ የማምረቻ ዘርፉን በማበረታታትና በመደገፍ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲዎችን በመተግበር የታወቁ ናቸው፡፡ አሁን ግን እነዚህ አገሮች የአገር ውስጥ ፍላጎታቸውን በበቂ ደረጃ ከማሟላት አልፈው፣ ለሌሎች አገሮች በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት የአገራችንን የምርትና ዓለም አቀፋዊ ንግድ ሁኔታ ስንመለከት፣ የምርት እጥረት ባጋጠመ ቁጥር ከውጭ ለማስመጣት ከመቸኮል ይልቅ በአገር ውስጥ በማምረት የሥራ ዕድልን በማስፋትና ሀብትን በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪን በማዳንና የአገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ማሳደግ የሚቻልበትን ዕድል መፍጠር ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ከመተካት ሥራ ባልተናነሰ፣ የአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ለአገር ውስጥ ምርቶች ያላቸውን አመኔታ እንዴት ማሳደግ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ትልቅ የቤት ሥራ ነው የሚሆነው። ምክንያቱ ደግሞ ዜጎች ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የተለየ አተያይ ያላቸውና (በተለይም ከፋሽንና የምርት ብራንድ ጋር በተገናኘ) የአገር ውስጥ ምርቶችን ዝቅ አድርጎ የመመልከት ልምድ እያዳበሩ መምጣታቸው ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርቶች የቱንም ያህል ጥራታቸው የተጠበቀና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ ቢሆን፣ ተፈላጊነታቸው እንዲቀንስ ብሎም አምራቾች ለኪሳራ መጋበዙ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም የአገር ውስጥ ምርቶችን ጥራት ከማሳደግና ዋጋቸውንም ከማመጣጠን ጎን ለጎን፣ ዜጎች ለአገር ውስጥ ምርት ያላቸውን አመለካከት የመቅረፅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

የአገር ውስጥ ምርቶች ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች በተሻለ ደረጃ በአገር ውስጥ መመረት እንደሚችሉ፣ ዋጋቸውም የተሻለ መሆኑን፣ የአገር ውስጥ ምርት ስንጠቀም በተዘዋዋሪ አገራችንን እየደገፍን መሆኑን፣ ወዘተ. በመጥቀስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት ጠቃሚ ነው። የአገራቸውን ምርት በመጠቀም ረገድ የሚታወቁት ህንዶች ናቸው፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ አጋጣሚውን ተጠቅመው የአገራቸውን ምርት ገዝተው በመጠቀም ለአገራቸው የቻሉትን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። የአገር ውስጥ ምርትን መጠቀም በተዘዋዋሪ የአገርን ኢኮኖሚ ማበረታታት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። የአገር ምርትን የመጠቀም አካሄድ ከኅብረተሰቡ በተጨማሪ መንግሥትም ሊያበረታታውና ሊከተለው የሚገባ አካሄድ ነው። አብዛኞቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከውጭ በገቡ ነገር ግን በአገር ውስጥ መመረት በሚችሉ ዕቃዎች የተሞሉ ናቸው (እዚህ ላይ አንባቢያን የራሳቸውን ትዝብት ማስቀመጥ ይችላሉ)። ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ ሼልፎች፣ ምንጣፎች፣ የተለያዩ የወረቀት ምርቶች፣ ብዕር፣ የቢሮ ማስዋቢያዎችና የመሳሰሉት ዕቃዎች በአገር ውስጥ መመረት የሚቻሉ ነገር ግን ከውጭ በዶላር ከሚገቡ ምርቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህልን ማዳበር የአገር ውስጥ አምራቾችን ከማበረታታትና የውጭ ምንዛሪን ከማዳን አንፃር ጉልህ ፋይዳ ስላለው ሊታሰብበትና ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ዓለም አቀፍ የገበያ ዕድሎችን በማፈላለግ በመጠቀም ኢትዮጵያ ከአጎዋ ያጣችውን ዕድል ማካካስ የምትችልበትን ዕድል ይፈጥራል። ይህንንም ለማድረግ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ጥራት፣ ደረጃና ተወዳዳሪነት ማሳደግና ለምርት ተጠቃሚዎች የምርት ምልክት ዕውቅና መፍጠር ያስፈልጋል። ከዚህም ሌላ አጎዋን የመሳሰሉ ዕድሎችን ከሚያቀርቡ አገሮች ጋር በቅርበት መሥራት አሌ ሊባል የማይገባው ተግባር ነው። ለምሳሌ በቅርቡ የቻይና መንግሥት የአፍሪካ አገሮች የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን ከቀረፅ ነፃ ወደ ቻይና መላክ ይችላሉ ሲል አስታውቋል። ይህንን መሰል ዕድሎችን በመጠቀም የውጭ ንግዱን ማሻሻል፣ ብሎም ከአጎዋ የታጣውን ጥቅም ማካካስ ይቻላል እላለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...