- ለልጆቹ የተቀጠሩት አስጠኚዎች እንዴት ናቸው?
- ምን ይሆናሉ ብለህ ነው፣ ደህና ናቸው።
- መቼ ስለጤንነታቸው ጠየቅኩሽ?
- ውይ የእኔ ነገር…
- ባህሪያቸው እንዴት ነው? እየተከታተልሽ ነው?
- ውሎ አድሮ ካልተቀየሩ በስተቀር እስካሁን ጥሩ ናቸው፣ ከልጆቹም ጋር ጥሩ ተግባብተዋል፡፡
- ያልኩሽንስ አረጋገጥሽ?
- ምን ነበር ያልከኝ?
- የመታወቂያቸውን ጉዳይ ነዋ?
- አዎ፣ የታደሰ ነው፣ አረጋግጫለሁ!
- ባቢስ ትምህርት ከጀመረ በኋላ እንዴት ነው?
- እስኪ የእሱን ነገር ትምህርት ቤት ሄጄ ለመጠየቅ አስቤያለሁ?
- ለምን? ምን ተፈጠረ?
- በየቀኑ ከተማሪዎች ጋር እየተጋጨ ነው የሚመጣው።
- እየተጋጨ?
- አዎ፣ እከሌ አላጫውት አለኝ… እከሌ መታኝ… እያለ በየቀኑ እያላዘነ ነው የሚመጣው።
- ይኼማ የተለመደ ነው… ትምህርት ገና መጀመሩ ስለሆነ ነው፡፡
- እኔም እንደዚያ ብዬ ንቄው ነበር።
- እና…
- ሰሞኑን ግን ካልተገዛልኝ ትምህርት ቤት አልሄድም ማለት ጀምሯል።
- ምን ካልተገዛልኝ ነው የሚለው?
- ድሮን፡፡
- ድሮን?
- አዎ፣ መፍትሔ መሆኑ ነዋ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአንድ የአውሮፓ ዲፕሎማት ጋር እየተወያዩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር እንደምን አሉ?
- ጤና ይስጥልኝ አምባሳደር፡፡
- ዛሬ ለምን ላገኝዎት እንደፈለግኩኝ ሳይገምቱ አይቀርም ብዬ አስባለሁ።
- በጭራሽ አላውቅም… ነገር ግን በሰሜኑ ቀውስ ዙሪያ እንደሚሆን ከቀደሙት ግንኙነቶቻችን መጠርጠር ይቻላል።
- እርግጥ ነው በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ነው፣ የሰሜኑ ግጭት በቅርቡ ሰላማዊ መፍትሔ እንደሚያገኝ አመላካች ነገሮች በማየታችን ደስተኛ መሆኔንም በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ ነው።
- አዲስ አመላካች ነገር አለ እንዴ?
- በሰሜኑ ወገን የታያውን የአቋም ለውጥ አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- አልሰማሁም፣ የአቋም ለውጥ አለ እንዴ?
- ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ፍላጎታቸውን ለተመድ ገልጸዋል፣ ተመድም ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
- አምባሳደር እነዚህን ሰዎች በደንብ የተረዷቸው አልመሰለኝም።
- እንዴት?
- ይህ እኮ የተለመደ ተግባራቸው ነው… በተለይ ጥሩ ምት ባረፈባቸው ወቅት ሰላማዊ መፍትሔን ያነሷታል፣ ትንሽ አቅም ያገኙ ጊዜ ደግሞ ሰላማዊ መፍትሔን ይጥሏትና ሌላ ነገር እንደሚሉ ይታወቃል።
- ሌላ ምን ይላሉ?
- ጦርነቱ አልቋል… ከዚህ በኋላ የምታድኑት ከተማ የለም ይላሉ።
- ክቡር ሚኒስትር አሁን ግን ቁርጠኛ ይመስላሉ።
- እንደዚያ ካመኑ ቁርጠኛ መሆናችሁን አሳዩ ይበሉልኝ።
- በይፋ ከመግለጽ በላይ እንዴት አድርገው ሊያሳዩ ይችላሉ ክቡር ሚኒስትር?
- ቢያንስ ሁለት ነገር በማድረግ ቁርጠኝኘታቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ?
- ይንገሩኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንደኛውና ቀዳሚው የተኩስ አቁም ማወጅ ነው፣ ሌላው ሰላማዊ መፍትሔ ለመፈለግ በእነርሱ በኩል የሚወክሉትን ሰው ወይም ቡድን ማሳወቅ ነው።
- ክቡር ሚኒስትር እንደዚያ ከሆነ በእናንተ በኩልም አንድ ዕርምጃ በመራመድ ቁርጠኝነታችሁን በተግባር መግለጥ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፣ ተሳሳትኩ?
- ተሳስተዋልም… አልተሳሳቱምም ማለት ይቻላል።
- እንዴት?
- አንደኛ አገረ መንግሥቱን የሚመራ አካልን ነፍጥ ካነገቡ ስብስቦች ጋር ማነፃፀር ስህተት ነው፣ ነገር ግን ይህ አካል ለእነሱ ብሎ ሳይሆን ባለበት መንግሥታዊ ኃላፊነት ቁርጠኝነቱን ማሳየት ያለበት በመሆኑ ትክክል ነው።
- እስማማለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጥሩ፣ እንደዚያ ከሆነ መንግሥት ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ለማድረግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ በመላክ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፣ ጥረቱንም እየቀጠለ ነው። ይህንንም የሚያውቁ ይመስለኛል።
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፣ ነገር ግን በእነሱ በኩል በአገራዊ ምክክሩ መሳተፋቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፣ ይህን ሳያረጋግጡ ተኩስ አቁም ለማወጅ የሚቸገሩ ይመስለኛል፣ ስለዚህ በእናንተ በኩል ማስተማመኛ ቢሰጥ ጥሩ ነው።
- የምን ማስተማመኛ? ሁሉም የፖለቲካ ኃይል በምክክሩ እንደሚሳተፍ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከማስቀመጥ በላይ ምን ማስተማመኛ ሊሰጥ ይችላል?
- የሽብር ፍረጃው ካልተነሳ በምክክሩ መሳተፍ እንደማይችሉ የታወቀ ነው፣ ስለዚህ…
- ተው… ተው… አትጨርሰው…
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- እሱ የሚያሳስብ አይደለም።
- እንዴት አያሳስብም ክቡር ሚኒስትር?
- መፍትሔ ስለተቀመጠለት አያሳስብም፡፡
- አልገባኝም?
- አንደኛ በምክክሩ የሚሳተፈው የፖለቲካ ሐሳብ ነው፣ ሁለተኛ ምክክሩን የሚመራው ኮሚሽን ያለ መከሰስ መብት እንደሚኖረው በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል።
- ስለዚህ?
- ስለዚህ የሽብር ፍረጃውን ማንሳት ሳይሆን ተጠያቂ ማድረግ ነው የሚያስፈልገው ለማለት ነው፣ በጣም አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ በሕግ አግባብ ለብቻው ማየት ይቻላል።
- ይህንን ጉዳይ ለብቻው ማየት ይቻላል?
- አዎ፣ በሕጉ መሠረት ለብቻው ማየት ይቻላል?
- እንዴት?
- የአሸባሪነት ፍረጃ የሚነሳበት የሕግ ሥነ ሥርዓትን ተከትሎ ማንሳት ይቻላል፣ ወደዚህ ለመግባት ግን ከእነሱ የሚጠበቀውን መፈጸም አለባቸው።
- ምንድነው በዋናነት የሚጠበቅባቸው?
- እጅ መስጠት ብቻ!