Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፐርፐዝ ብላክ ከትልልቅ ኢንቨስተሮች ጋር በጥምረት የሚሠራበትን አዲስ አማራጭ ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በግብርና፣ በኢኮሜርስ፣ እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን ለማከናወን ከአምስት ወራት በፊት ወደ ሥራ የገባው ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ፣ ከትልልቅ ኢንቨስተሮች ጋር በጥምረት እሠራበታለሁ ያለውን አዲስ አማራጭ ይፋ አደረገ፡፡

ድርጅቱ በተመሠረተ በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሺሕ በላይ ባለ አክሲዮኖችን እንዳፈራ ያስታወቀ ሲሆን፣ በደቡብ ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ አካባቢ ያገኘውን 400 ሔክታር መሬት መሠረት በማድረግ ከትልልቅ ኢንቨስተሮች ጋር በጥምረት እሠራበታለሁ ያለውን አዲስ የባለ አክሲዮንነት አማራጭ ‹‹ፍራንቻይዝ ሼር ሆልደር ሞዴል›› አስተዋውቋል፡፡

ይህ ከድርጅቱ ጋር በጥምረት ለመሥራት የፈለጉ ኢንቨስተሮች የተለየ ጥቅም ያገኙበታል የተባለው አማራጭ፣ ኢንቨስተሮች ልዩ ናቸው የተባሉትን አክሲዮኖች ከድርጅቱ በመግዛት ወደ ሥራ የሚገባበት መሆኑን፣ በዚህም ኢንቨስተሮች ከገዙት አክሲዮን  የሚገኘው ዓመታዊ ትርፍ ድርሻ እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪም የ50 በመቶ የትርፍ ተካፋይ የሚያደርጋቸው እንደሆነ አማራጩ ይፋ በተደረገበት መድረክ ተገልጿል፡፡

የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሐ እሸቱ (ዶ/ር)፣ ‹‹ባለ ሀብቶች ለእርሻ ሥራ ለማዋል ያሰቡትን ገንዘብ አክሲዮን የሚገዙበትና ፐርፐዝ ብላክ ከሚተገበረው የእርሻ ልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር ይፋ አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ይፋ ባደረገው አሠራር መሳተፍ የሚፈልግ ባለ ሀብት፣ ለአንድ ሔክታር የእርሻ መሬት 100 ሺሕ ብር መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ለዚህም ልማት ይሆን ዘንድ፣ 400 ሔክታር ለእርሻ ልማት የሚውል መሬት በጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ አካባቢ እንዳገኘ ተገልጿል።

ፍስሐ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በቀረበው አማራጭ አንድ ግለሰብ በቀጥታ ገንዘቡን ወደ እርሻ ከሚያስገባ ይልቅ፣ በዚህኛው አማራጭ የፍራንቻይዝ ሼርን የሚገዛበት ሲሆን፣ ገንዘቡ በቀጥታ ለእርሻ ሳይሆን የሚውለው በአክሲዮን ደረጃ የሚቀመጥ ነው፡፡

አክሲዮኑ ለሁለት ጥቅም የሚውል ሲሆን፣ በአንድ በኩል ፐርፐዝ ብላክ ከሌሎች ሥራዎች የሚያገኘውን ጥቅም ክፍፍል ለማግኘት የሚያስችል ሲሆን፣ ፍርንቻይዝ ሼር በሚባለውና በሔክታር ጥቅም በሚያስገኘው አማራጭ ደግሞ በሔክታር 100 ሺሕ ብር የገዛ ባለ አክሲዮን፣ ከሔክታሩ ልማት ከሚገኘው ትርፍ 50 በመቶ የሚያገኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ አገር የፍራንቻይዝ ሞዴል የሚቀርብብት መንገድ ሰዎች ፈቃድ ወስደው በእርሻ መሬት ላይ ራሳቸው ኢንቨስት የሚያደርጉበትና ለኩባንያው በየዓመቱ የፍራንቻይዝና የሮያሊቲ ክፍያዎች የሚፈጸሙበት ሲሆን፣ ፐርፐዝ ብላክ ባቀረበው አማራጭ ላይ ባለ አክሲዮኖች ከሮያሊቲና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ክፍያዎችን እንደማይከፍሉ፣ የሚከፍሉት ገንዘብ በአክሲዮን መልክ እንደሚያዝላቸው፣ አክሲዮናቸውን ሸጠው መውጣት በፈለጉ ጊዜ ሸጠው የመውጣት መብታቸው የተጠበቀ እንደሆነ ፍስሐ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ባለ አክሲዮኖች ከአንድ በላይ የባለ አክሲዮን ባለቤትነት ድርሻ  ያላቸው ሲሆኑ፣ ከባለ አክሲዮን ባለቤትነት መውጣት የፈለገ ባለድርሻ ያለውን ድርሻ ሸጦ የሚወጣበት አማራጭ ሌላው ለባለ አክሲዮኖች የተቀመጠ አማራጭ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በግለሰብ ደረጃ የግብርና ሥራ ውስጥ ገብቶ ከመሥራት አንስቶ፣ በሥራው ላይ የሚደርሱ አሉታዊ ችግሮች ለብቻ መወጣት እንደሚጠበቅ የተገለጸ ሲሆን፣ ባለ አክሲዮኖች ከሌሎች ባለ አክሲዮኖች ጋር ሆነው በሚሳተፉበት ኢንቨስትመንት ከመደበኛው አክሲዮን እንቅስቃሴ በሻገር በተሻለ ሁኔታ ጥቅም የሚያገኙበትን አማራጭ ፐርፐዝ ብላክ እንዳቀረበ ተመላክቷል፡፡

ድርጅቱ በተንቀሳሽ ተሽከርካሪዎች የጀመረውን የግብርና ውጤቶችን ለኅብረተሰቡ የማቅረብ እንቅስቃሴ በቋሚ ሱቆች ለማድረግ ባቀደው መሠረት፣ ሊከፍት ካቀዳቸው አንድ ሺሕ ከሚደርሱ ሱቆች የመጀመርያውን ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ እንደሚከፍት ተገልጿል፡፡

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ከአምስት ወራት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የግብርና ምርቶችን በተሽከርካሪዎች እያዘዋወረ መሸጥ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች