Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ራሳቸውን የሚያስተናግዱባቸው ማሽኖች መትከሉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹ ያለ ሰው ዕገዛ መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችሉ አሥር ‹ሰልፍ ሰርቪንግ› ማሽኖችን፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ላይ መትከሉን ገለጸ፡፡

ማሽኖቹ በቦሌ፣ በቸርችል፣ በካዛንቺስ፣ በጊዮርጊስ፣ በለቡና ሌሎች የኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፎች ያሉባቸው አካባቢዎች መተከላቸውን ኢትዮ ቴሌኮም ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡ ተጠቃሚዎች እነዚህን ማሽኖች በመጠቀም የአየር ሰዓት መሙላት፣ አዲስ ሲም ካርድ ማውጣትና የመስመር ስልክ ቢል መክፈል ይችላሉ፡፡

ደንበኞች ማሽኑ ውስጥ ገንዘብ በማስገባት ስልካቸው ላይ የአየር ሰዓት እንዲሞላ ማድረግ የሚችሉ ሲሆን፣ በማሽኖቹ ላይ አዲስ ሲም ካርድ ለማውጣት የሚያስፈልጉ መረጃዎች መሙላት ፎቶግራፍ መነሳትም እንደሚቻል ተገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቴሌ ብር ተጠቃሚዎች ማሽኖቹን በመጠቀም ገንዘብ ማውጣትና ማስገባት የሚችሉበትን አማራጭ በማካተት፣ የማሽኖቹን ሥራ ለማስጀመር እየሠራ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

በተተከሉት አሥር ማሽኖች ላይ የሚደረገው የሶፍትዌርና የሌሎች የቅድመ ሙከራ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር የባንክ የክፍያ ማሽኖችን (ኤቲኤም) በመጠቀም የአየር ሰዓት መሙላት እንዲቻል ለማድረግ ጥናት እየተጠና መሆኑን ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ እንዴት ከሁሉም ባንኮች ሲስተም ጋር ማገናኘት እንደሚቻል ከኢቲስዊች (ETSwitch) እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ደንበኞቹን 64 ሚሊዮን የማድረስ ዕቅድ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በዚሁ ዓመት የ5ጂ ኔትወርክ የማስጀመርና በተመረጡ ቦታዎች ላይ 24 ሰዓት የሚሠሩ ቅርንጫፎችን የመክፈት ሐሳብ አለው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም አብዛኛውን የአየር ሰዓት ሽያጩን በኤሌክትሮኒክስ የአየር ሰዓት መሙያ ዘዴዎች እያደረገ ሲሆን፣ ሦስት ዓመት በፊት የ‹‹ይሙሉ›› አገልግሎት አስተዋውቆ ነበር፡፡

በካርድና በወረቀት የሚቀርበውን የአየር ሰዓት ሙሌት የሚያስቀረው ‹‹ይሙሉ›› በተዋወቀበት ጊዜ ቸርቻሪ ባለ ሱቆች በስፋት ሲጠቀሙበት ተስተውሎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን የአየር ሰዓት ለመሙላት ‹‹ይሙሉ›› ጥቅም ላይ ሲውል አይታይም፡፡  ኢትዮ ቴሌኮም የይሙሉ አገልግሎት ሥራ ላይ የዋለው በ‹‹USSD›› እና ‹‹SMS›› የመሸጫ ቻናሎች ብቻ በመሆኑ፣ ‹‹በሚገባው›› እና ‹‹በተቀላጠፈ›› መንገድ ለቸርቻሪዎች አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን ገልጿል፡፡ አገልግሎቱ የአቅም ውስንነቶች ነበሩበትም ተብሏል፡፡

‹‹ይህንን ችግር ለመቅረፍ የይሙሉን ሲስተም የማዘመንና የማሳደግ ሥራዎች በሰፊው እየተሠራ ይገኛል፤›› ያለው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ነገር ግን የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር ዲስትሪቡሽን (EVD) አገልግሎት ከይሙሉ በተሻለ በአከፋፋዮች፣ በቸርቻሪዎችና በደንበኞች ተመራጭ መሆኑ ‹‹ይሙሉ›› በፍጥነት እንዳያድግ እንዳደረገው አስታውቋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረውና በካርድ ሲቀርብ የነበረውን የአየር ሰዓት እየተካ ያለው የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር ዲስትሪቡሽን (EVD) የሚስጥር ቁጥሩ ሳይሸፈን የአየር ሰዓቱ በወረቀት ታትሞ የሚሸጥበት አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ የአየር ሰዓት መሙያ ዘዴ ኢትዮ ቴሌኮም የአየር ሰዓቱን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ለአከፋፋዮች በጅምላ የሚሸጥ ሲሆን፣ አከፋፋዮቹ በቸርቻሪዎቻቸው በኩል በአገር ውስጥ እያተሙ የአየር ሰዓቱን ለደንበኞች ይሸጣሉ፡፡

ተቋማቱ ይኼ ዘዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሽያጭ ድርሻን ማስመዝገብ እንደቻለ ገልጾ፣ በአሁኑ ጊዜ በኤሌክትሮኒክስ የመሙያ ዘዴ እየሸጠ ካለው 83 በመቶ ውስጥ 63 በመቶውን የሚሸፍነው የ‹‹ኢቪድ›› የአየር ሰዓት መሸጫ ዘዴ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይኼም ቀደም ሲል ተቋሙ ለካርድ ማሳተሚያ ያወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ‹‹በከፍተኛ ደረጃ›› ለማስቀረትና ካርዱ ከታተመ በኋላ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚከፈለውን የትራንስፖርት ወጪን ለመቀነስ እንደረዳ ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ከአጠቃላይ ተጠቃሚዎቹ ውስጥ 17 በመቶ ብቻ ለአየር ሰዓት ሙሌት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎትን እየተጠቀሙ አለመሆኑን አስታውቆ፣ የካርድ አየር ሰዓት ሙሌት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ሊደርስ በማይችልባቸው ገጠራማ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አክሏል፡፡

ተቋሙ የኤሌክትሮኒክስ የአየር ሰዓት ሙሙያ ዘዴ አጠቃቀም 83 በመቶ መድረሱን ገልጾ፣ ‹‹ለወደፊትም የኤሌክትሮኒክስ የአየር ሰዓት መሙያ ዘዴ በአማካይ ከ80 በመቶ ሊበልጥ እንደማይችል፣ ይህም የዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ጋር እኩል መሆኑን መረዳት ተችሏል፤›› ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች