የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት፣ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌላ የአገሪቱ አካባቢ የአገር መከላከያ ሠራዊቱን የማስፈር ሙሉ መብት እንዳለው አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆነ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የእስያና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ዲፕሎማቶች ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በተመለከተ ማክሰኞ ታኅሳስ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት ማብራሪያ ነው ይህንን የተናገሩት፡፡
ሰሞኑን የአገር መከላከያ ሠራዊትና ጥምር ኃይሎች በወሰዱት የተቀናጀ ዕርምጃ አከርካሪውን የተመታው የሕወሓት ኃይል፣ ከአማራና ከአፋር ክልሎች በገዛ ፈቃዱ ለቆ እንደወጣ የሚያስወራውን ሐሰት ነው ብለዋል፡፡
‹‹አሸባሪው ሕወሓት በደረሰበት ምት ይዟቸው የነበሩ አብዛኛው የአፋርና የአማራ አካባቢዎችን በማስለቀቅ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ሥር አድርዋል፡›› ያሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ‹‹የሽብር ቡድኑ ለሰላም ሲል በወረራ ከያዝኳቸው አካባቢዎች ለቅቂያለሁ ማለቱ ከተጨባጩ እውነታ ጋር ተቃራኒ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. በመንግሥት የተወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ባለመቀበል ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በንፁኃን ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን፣ የመሠረተ ልማትና ሃይማኖታዊ ተቋማትን ማውደሙን፣ ሕፃናትንና ሴቶችን መድፈሩን አብራርተዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ፣ የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው አካላት አስተባባሪነት የተላለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ ተፈጻሚ እንደማታደርግ ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር ተግባራዊ ማስተካከያዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እንዳላት ገልጸው፣ ቀደም ሲል የተመድ የሰብዓዊ መብት ተቋምና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባደረጉት የጋራ ምርመራ የቀረቡትን ምክረ ሀሐቦች ተግባራዊ ለማድረግ ተግባራዊ አንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እያደረገች ሳለ የተላለፈ ውሳኔ መሆኑን ለዲፕሎማቶቹ አስረድተዋል፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች የፈጸማቸውን ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች በማውገዝ ምርመራ እንዲካሄድ ውሳኔ ማስተላለፍ እንደተሳነው አስታውሰው፣ ይህንን ተግባር ቢያከናውን ኖሮ ያስመሰግነው ነበር ብለዋል።