Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየውኃ አካል ዳርቻ ረቂቅ አዋጅ የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

የውኃ አካል ዳርቻ ረቂቅ አዋጅ የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

ቀን:

የውኃ ዳርቻን ለመከላከል፣ ለመጠበቅና አጠቃቀምን ለመወሰን በሚል በ2012 ዓ.ም. በቀድሞው የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን የተዘጋጀው የውኃ አካል ዳርቻ ረቂቅ አዋጅን ለማፀደቅ የመጨረሻ የማስተካከያ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ረቂቁ ከተዘጋጀ ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ከተሞች ውይይትና ምክክር ሲደረግበት የቆየ ሲሆን፣ ወደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተመርቶም ማስተካከያዎች እንዲደረጉበት መመለሱ ተሰምቷል፡፡ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢኮኃይድሮሎጂ ዘርፍ የበላይ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ዘሪሁን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ዓቃቤ ሕግ በረቂቁ ላይ የሰጠው አስተያየት ተስተካክሎ በድጋሚ ተልኮ የነበረ ቢሆንም፣ አዲሱን የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አወቃቀር ተከትሎ የተቋማት ስያሜና ተግባር ላይ ለውጥ በመደረጉ በድጋሚ ማስተካከያ ማድረግ ግድ ብሏል፡፡

የውኃ ዳርቻ ረቂቅ አዋጅ ሁሉንም የአገሪቱን የውኃ አካላት ማለትም ሐይቅ፣ ግድብ፣ ወንዝ፣ ረግረጋማ ቦታና የከርሰ ምድር ውኃዎችን የሚመለከት ነው፡፡ የውኃ አካላቱ ከእርሻ፣ ከኢንዱስትሪና ከከተሞች ፍሳሽ ለሚመጣ ብክለትና ደለል እንዳይጋለጡ ጥበቃ የማድረግ ሐሳብ ያለው ነው፡፡ ይኼንን ዓይነቱን ጥበቃ በማድረግ የውኃ አካላቱን ከደለል፣ ከብክለትና ከመጤ ዓረም መጠበቅ እንደሚቻል ታምኖበታል፡፡ እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጻ፣ ረቂቅ አዋጁ በተለይ በአገሪቱ የተለያዩ የውኃ አካላት ላይ እየተስፋፋ ያለውን የእንቦጭ ዓረም ለመከላከል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

የእንቦጭ ዓረም ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ የታየው በ1956 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ አካባቢ በሚገኘው አባ ሳሙኤል ግድብ ላይ ቢሆንም፣ ሥርጭቱ በእጅጉ የተስፋፋው በ2003 ዓ.ም. በተከሰተበት የጣና ሐይቅ ላይ ነው፡፡ አቶ ዮሐንስ እንቦጭ ጣና ላይ ለመስፋፋቱ የውኃ ዳርቻው አለመጠበቁ ትልቁ ምክንያት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ በዙሪያው ካሉት እርሻዎች ወደ ውኃ ውስጥ የሚገባው ደለልና ማዳበሪያ ለመጤ አረሙ ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የሐይቁ በፈር ዞን የለም፣ በእርሻ  ምክንያት ተወግዷል፤›› ያሉት አስተባባሪው፣ በዚህም ምክንያት በጣና ሐይቅ የተከሰተው የእንቦጭ ዓረም ከሌሎች አከባቢዎች ይበልጥ ሥርጭቱ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የእንቦጭ መጤ ዓረም በኢትዮጵያ ‹‹ወራሪ ዓረም›› ተብሎ የተለየው በ2000 ዓ.ም. ሲሆን በሻላ፣ በአቢጃታ፣ በዝዋይ፣ በጣናና በቆቃ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ላይ ታይቷል፡፡ በተለይ በጣና፣ በቆቃና በዝዋይ ሐይቆች ላይ ወረርሽኝ በሚባል ደረጃ መስፋፋቱም ተገልጿል፡፡ መጤ ዓረሙ የውኃ አካላቱን የትነት መጠን በመጨመር እንዲደርቁ የሚያደርግ ሲሆን፣ ወደ ውኃ ውስጥ የሚገባ ደለል ታጥቦ እንዳይወጣ በማድረግም የውኃ አካላት በደለል እንዲሞሉ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የጀልባና የውኃ ላይ አዕዋፋትን እንቅስቃሴን ከመገደቡ በተጨማሪም፣ በውኃ ውስጥ ያሉ እንስሳት ኦክስጅን እንዳያገኙ ያግዳል፡፡

 በ2013 ዓ.ም. በጣና ሐይቅ የተከሰተውን እንቦጭ ለማስወገድ በተካሄደው ዘመቻ በሐይቁ ላይ የሚንሳፈፈውን ዓረም 80 በመቶ መሰብሰቡ ቢነገርም፣ ዘላቂው መፍትሔ የሐይቁን ዳርቻን ማልማት፣ መጠበቅና ከብክለት መከላከል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በረቂቅ ላይ ያለው የውኃ ዳርቻ አዋጅ ችግር ከተፈጠረ በኋላ መፍትሔ ከመፈለግ ባለፈ መንስዔውን ማድረቅ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ የተዘጋጀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አዋጁ ሲፀድቅ የውኃ አካል ዳርቻ ክልልንም እንደሚወስን ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት የውኃ አካል ዳርቻ ክልል ላይ የአፈር ደለልና ሌሎች ብክለትን የሚፈጥሩ ንጥረ ነገሮች ወደ ውኃ ውስጥ እንዳይገቡ ለማስቻል፣ ሦስት ደረጃዎች ያሉት የዕፅዋት ተከላ እንደሚከናወን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

ይኼ ተግባራዊ ሲደረግ በተለይ በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮችን እርሻ ቦታ ሊነካ እንደሚችል የጠቆሙት አስተባባሪው፣ ከአርሶ አደሮች ጋር ንግግር እንደሚደረግና ዳርቻው ላይ የሚተከሉ ዕፅዋትን ለአርሶ አደሮቹና እንስሳቶቻቸው ምግብነት የሚውሉ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የውኃ አካላትን የዳርቻ ርቀትን ለመወሰን ያለመ በመሆኑ፣ የበዛ ብክለት የሚታይባቸውን የከተማ ወንዞችንም ይመለከታል፡፡ ‹‹በከተማዋ በሚገኙ ወንዞች ዳርቻ ላይ ያሉ ነዋሪዎች ጉዳይ እንዴት ይሁን፤›› የሚለው ከአዋጁ በኋላ በሚወጣ መመርያ የሚመለስ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ነዋሪዎቹ ባሉበት ሆነው ወንዞቹን የሚንከባከቡበትን መንገድ መፍጠር አንዱ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ይህንን የተመለከተ ኮሜቴ ተዋቅሮ ምልከታ በማድረግ ላይ መሆኑንም አክለዋል፡፡

‹‹እንደኛ ዕቅድ ቢሆን ኖሮ አዋጁ እስካሁን መፅደቅ ነበረበት፤›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ የሚቀሩት ማስተካከያዎች ተደርገው ረቂቁ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ዓቃቤ ሕግ ተመልሶ እንደሚላክ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...