Monday, December 4, 2023

የተለያዩ ሐሳቦች የተደመጡበት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ሕዝባዊ ውይይት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምልዓተ ሕዝቡ ተቀራራቢና በአገራዊ አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙና አካታች አገራዊ ምክክር ተግባራዊ ለማድረግ፣ ይህንኑ ምክክር በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ቅቡልነት ያለው ተቋም ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመራው ታኅሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ነበር፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ሊቋቋም የታሰበው ኮሚሽን 11 ያለ መከሰስ መብት የሚሰጣቸው ኮሚሽነሮች ይኖሩታል፡፡ በዋነኝነት በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ፣ የሐሳብ መሪዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ፣ ይህንን ልዩነትና አለመግባባት ለማርገብና ለመፍታት ሰፋፊ አገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚሠራ ስለመሆኑ በረቂቅ አዋጁ ተጠቅሷል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አገራዊ የምክክር መድረክ እንዲመራና እንዲያሳልጥ ለመጀመርያ ጊዜ በመቋቋም ላይ የሚገኘውን ኮሚሽን በሚያቋቁመው ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ ሰኞ ታኅሳስ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በረቂቅ አዋጁ ላይ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የፍትሕ ሚኒስትርና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በርካታ ተሳታፊዎች የኮሚሽነሮች አሰያየም፣ አወቃቀርና የኮሚሽኑ አደረጃጀት ላይ ያላቸውን ሥጋትና የገለልተኝነት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የኮሚሽነሮች አሰያየም ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና በግልጽ እንዳልተቀመጠ ጠቁመው፣ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጅምሩ አስፈላጊነታቸው ታምኖበት ተመሥርተው መንግሥት በገንዘብም ሳይቀር እየደገፋቸውና የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ በመሆናቸው፣ በአገራዊ ውይይቱ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሚና በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

አቶ ክቡር ገና፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ሰብሳቢዋ አክለውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተፈጥቸውና ከአደረጃጀታቸው ልዩነቶችን አጉልተው ከማሳየት፣ የኅብረተሰቡን ፍላቶችንና ጥያቄዎች መልክ ሰጥተው ከማምጣት አኳያ የማይተካ ሚና ስላላቸው፣ እነሱ ሊኖራቸው ስለሚገባ ኃላፊነት በግልጽ ሊቀመጥና ከፍ ያለ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ስለሆነም ፓርቲዎች በውይይትና በክርክር ይዘውት የመጡትን ልምድ በግብዓትነት ማቅረብ ስለሚችሉ፣ ይህ ልምድ የአገራዊ ውይይቱ ገባር ወንዝ ሊሆን እንደሚገባ በረቂቁ አዋጅ ላይ መሥፈር እንዳለበት ወ/ሪት ብርቱካን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 14 የሠፈረው የኮሚሽነሮች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ለመንግሥት ከፍተኛ ተሿሚዎች በተፈቀደው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም አግባብ በመባሉ፣ አንድ ተሿሚ ሕዝብን ለማገልገል የዕለት ተዕለት ኑሮውን ማሰብ ያለበት አይመስለኝም፤›› ያሉት ወ/ሪት ብርቱካን፣ እንዲሾሙ የሚታሰቡትን ኮሚሽነሮች የማይጋብዝና ከልካይ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋቸውን አስረድተዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ መስከረም ገስጥ በበኩላቸው፣ የኮሚሽነሮች ዕጩ ጥቆማ አሰጣጥ ላይ የሌሎችን አገሮች ልምድ በመውሰድ  በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ተብሎ የቀረበው አማራጭ ቀርቶ ራሱን የቻለ ገለልተኛና ከአስፈጻሚው አካል ውጪ የሆነ ሌላ አካል የጥቆማውንም ሆነ የአሰያየሙን፣ ወይም የአስተያየት አቀባበሉን ሒደት የሚመራ ገለልተኛ ተቋም ወይም ቡድን እንዲይዘው ቢደረግ የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ወቅት በተደጋጋሚ ለብልፅግና ጽሕፈት ቤት ጭምር ጥያቄቸውን በተደጋሚ አቅርበው እንደነበር፣ ነገር ግን መልስ ያላገኘና ያልታረመ አሁንም ተመልሶ ሳይስተካከል በረቂቁ አንቀጽ 12.1 ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዕጩ የኮሚሽነር አባላትን ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ከፓርቲዎችና ከሲቪል ማኅበራት ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች ጥቆማ ይቀበላል ተብሎ ስለቀረበው ጉዳይ ሐሳባቸውን የሰጡት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

‹‹መንግሥትም ሆነ ምርጫ ሊፈታው ያልቻለውንና ሲንከባለል የመጣውን ችግር ለመፍታት እየሄድን፣ አሁንም በአስፈጻሚው አካል በኩል ከተለመደው አሠራር ለምን መውጣት አልተቻለም፤›› በማለት በሚል ሐሳባቸውን የሰጡት ሰብሳቢዋ በመንግሥትና በሕዝብ፣ በሕዝብ በራሱ ውስጥና በታሪክ ሲንከባለል የመጣውን ችግር ለመፍታት እንዴት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያልፍ እንደተደረገ ማብራርያ ጠይቀዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈትና ቤት የብልፅግና ፓርቲን አንዱ ከአንዱ ተለይቶ በማይታይበት በዚህ ጊዜ፣ ረቂቅ አዋጁ ሲዘጋጅ የጋራ ምክር ቤቱና የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሲሠሩበት የቆየውን ሥራ በአንድ ጊዜ ገልብጦ በብልፅግና ፓርቲ ከተወሰደ በኋላ፣ ብልፅግና ፓርቲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረቡ እንደ ፖለቲካ ፓርቲም እንደ ሕዝብም የገልተኝነቱን ጉዳይ ለማመን እንደሚቸገሩ ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው አሁናዊ የመንግሥት ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲው የመንግሥት መሪ በመሆኑ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በአንድ ፓርቲ የበላይነት የተያዘ ስለሆነ፣ እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በአንድ ፓርቲ ጋር የተያዘ ስለሚሆን፣ ከዚህ ወጣ ብሎ ገለልተኛ አካል እንዲይዘው በተለይም የጋራ ምክር ቤቱ ጉዳዩን የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንዲይዘው፣ የፍትሕ ሚኒስቴርንና የብልፅግና ጽሕፈት ቤትን ጠይቆ እንደነበር ነገር ግን ምንም ዓይነት ማስተካከያ እንዳልተደረገበት ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አሁንም ጉዳዩ በድጋሚ ታይቶ ማስተካከያ እንዲያደርግበት ጠይቀዋል፡፡

የኢዜማ ሊቀመንበርና የፖለቲካ ፓርቲዊች የጋራ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው፣ የገለልተኝነትን ጉዳይ አስመልክተው በረቂቅ አዋጁ መግቢያ ላይ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ ተብሎ የቀረበው ሐሳብ ከብልፅግና ፓርቲም ሆነ ከእሱ በፊት በነበሩ ፓርቲዎችና ገዥ ሥርዓቶችም የሚዘል ችግር እንዳለ በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን ችግር በሕግና በሕገ መንግሥቱ ወይም ባለው መንግሥታዊ መዋቅር ብቻ እያዩ ለመፍታት መሞከር ትክክል አለመሆኑን፣ ለዚህ ዘለግ ያለ ችግር ዘለግ ያለ ዕይታ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የግብር አዋጅ እንደሚወጣበት አሠራር ብቻ እንወስደዋለን የሚለው አካሄድ ትክክል ባለመሆኑ፣ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ወይም ሌላ ገለልተኛ ምክር ቤት ተቋቁሞ ኮሚሽኑን ማቋቋም እንደሚያስፈልግና እያንዳንዱ ዕርምጃ ላይ ገለልተኝነቱን ማረጋገጥና ከጅምሩ እየተማመኑ መሄድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

‹‹የአገራዊ መግባባት ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ተስፋ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በጣም ብዙ የተጠላለፉ ነገሮችን የምንፈታበትና በየደረጃው እየፈታን የምንሄድበት በመሆኑ፣ ከዚህ መድረክ ጀምሮ እየተማመንን ብንሄድ ጥሩ ይመስኛል፤›› ብለዋል፡፡

አክለውም የሚቋቋመው ኮሚሽን ምክረ ሐሳብ ያቀርባል ተብሎ የቀረበው ሐሳብ ተቀይሮ ተግባራዊነቱንም ያስፈጽማል የሚል ሐረግ መጨመር እንዳለበት የጠቆሙት አቶ የሽዋስ፣ ወደ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ የሚሰበሰበው ነገር ቀርቶ ለሁሉም  ክፍት የሆነ ተቋም እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

‹‹የኮሚሽኑ መቋቋም ብዙ ችግሮቻችን ሊፈታ ይችላል፡፡ ለበርካታ ቁስሎቻችን ማከሚያ መንገድ ይሆናል ብለን እናስባለን፤›› ያሉት ደግሞ፣ አቶ ጋሻው ሽባባው የተባሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

በመሆኑም የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ በጥንቃቄና በጣም በሰከነ መንገድ ገለልተኛነቱን  አብዛኞቹ ብዙዎች ተስማምተውበት ስምምነት ላይ መድረስ እንዲቻል ተደገርጎ መቀረፅ እንዳለበት፣ ለዚህም የኮሚሽኑ አሰያየምና አወቃቀር በፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ወይም በአፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት አማካይነት እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የቀረበው ሐሳብ  አጀንዳው ትልቅና ጥንቃቄ የሚፈልግ አገራዊ ፕሮጀክት በመሆኑ፣ በውጭ ደርጅቶች አጀንዳው እንዳይጠለፍ ተሳታፊዎቹ ድርጅቶች መለየት እንዳለባቸው አቶ ጋሻው አሳስበዋል፡፡

 ከመድረኩ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራርያ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ሊቋቋም የታሰበው ኮሚሽን ከዚህ በፊት ሲከናወኑ በነበሩ ውይይቶች፣ በተለይም እንደ ማይንድ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ስብስቦች የተከናወኑ ሥራዎችን እንደ ግብዓት ወስዶ ኮሚሽኑ ራሱ መሠረታዊ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮችን እንደሚወስን አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ አካላት በተለይም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በማይንድ ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በሌሎች ስብስቦች በአንድም በሌላ መንገድ ምክክሮች ሲያደርጉ የቆዩ እንዳሉ፣ አጀንዳና ተሳታፊ የለዩ ስለመኖራቸውና ሒደቱ ምን መምሰል እንዳለበት ያዘጋጁትን ሰነድ የሚቋቋመው ኮሚሽን እንደ መነሻና ግብዓት እንደሚያደርጋቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የአሰያየም ሐደቱን በተመለከተ በተለይም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የዕንባ ጠባቂ ተቋም ኮሚሽነሮችን አሰያየም መከተል ለምን እንዳልተቻለ ሲያስረዱ፣ እነዚህ ተቋማት ከሌሎቹ የዴሞክራሲ ተቋማት ለየት ባለ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቋቁማቸው በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ ከሕገ መንግሥታዊ ባህሪያቸውና ከአፈጣጠራቸው አንፃር ሕገ መንግሥቱ የሚሰጣቸው የራሱ የሆነ ባህሪ ስላለቸው እንደሆነ አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት በሚል የቀረበው ጉዳይ ከሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች በተጨማሪ፣ ለአገሪቱ ርዕሰ መንግሥት ዕጩዎችን እንዲያሰባስብ መደረጉ የፕሮቶኮልና የሥልጣን ጉዳዮችን ሊያስነሳ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተብሎ የቀረበው ሐሳብ ሊያስኬድ የሚችል በመሆኑ ይታሰብበታል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -