Monday, February 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ቢዝነሱን ለማስፋት የሚያስችለውን የምዘና ውጤት አገኘ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አገልግሎትን ለመስጠት የተቋቋመውና በዘርፉ በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነው የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አ.ማ.፣ ከኢትዮጵያ ውጪ ቢዝነሱን ለማስፋት የሚያስችለውን የምዘና ውጤት ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ኩባንያው ይፋ እንዳደረገው፣ የምዘና ውጤቱን ያገኘው በዓለም አቀፍ ደረጃ የምዘና ውጤት በመስጠት ከሚታወቁ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ከሆነው የደቡብ አፍሪካው ‹‹ጂሲአር ሬቲንግስ›› ከተባለ ኩባንያ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት ወልደ አማኑኤል እንዳመለከቱት፣ ኩባንያቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርገው የሚያስችለውን የምዘና ውጤት ደረጃ (ሬቲንግ) ማግኘቱ ከኢትዮጵያ ውጪ ቢዝነሱን ለማስፋት ዕድሉን ያሰፋለታል፡፡  

ይህ የምዘና ውጤት የሚሰጠው በመመዘኛዎች መሠረት በሚገኘው ውጤት ሲሆን፣ ባለፉት ስምንት ወራትም የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያን አጠቃላይ ይዘት በራሱ መንገድና በሌሎች ገለልተኛ አካላት ሲመዝን እንደነበር ተነግሯል፡፡

በዚሁ መሠረት በተካሄደው ምዘና ተወዳዳሪ ሊያደርገው የሚችል አቅም ላይ መድረሱን የሚያረጋግጥ ውጤት እንደተሰጠው አቶ ዳዊት አክለዋል፡፡ የምዘና ውጤቱ በሁለት ተከፍሎ በዓለም አቀፍና በአገር ደረጃ ያገኘውን ውጤት በመጥቀስ ደረጃው ተሰጥቶታል፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ በዓለም አቀፍ መሥፈርቶች መሠረት አሁን ያለው የኩባንያው ቁመና ‹‹ቢ-›› (ቢ ማይነስ) እንዲሁም በኢትዮጵያ ደረጃ ‹‹ኤኤ›› ውጤት ማግኘቱም ተገልጿል፡፡  

የሬቲንጉ በሁሉም የምዘና ውጤት ሰጪ ኩባንያዎች እንደሚደረገው ከሦስት ‹‹ኤ›› (AAA) እስከ ‹‹D›› ድረስ የሚሰጥ ሲሆን፣ በዚህ የውጤት አሰጣጥ መሠረት የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠው ውጤት በማንኛውም ሁኔታ ዋስትና ለተገባላቸው የመድን ሽፋኖች ካሳ ለመክፈል የሚያስችለው አቅም ያለው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

በብሔራዊ ደረጃ የተሰጠው ‹‹ደብል ኤ›› (AA) ውጤት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ደንበኞቹ አደጋ ቢደርስ የመክፈል ከፍተኛ አቅም ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥለት እንደሆነ ከአቶ ዳዊት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ ውጤት ባሻገር የምዘና ውጤቱ ኩባያው በተጨማሪ በሚሰጠው አስተያየት መሠረት የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንወደፊት ተስፋ ካላቸው ኩባንያዎች መካከል የሚመደብ ስለመሆኑ የሚያመለክት እንደሆነ የጠቀሱት የኩባንያው ስትራቴጂና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ የምዘና ውጤት በጠለፋ መድን ሥራ ኩባንያው የበለጠ እንዲሠራ የሚያግዝ ነው፤›› ብለዋል፡፡   

እንደ ሲጂአር ያሉ ኩባንያዎች የሚሰጡት እንዲህ ያለው የምዘና ውጤት በየዓመቱ እየታየ ባለበት ደረጃ ልክ ውጤቱ የሚሰጣቸው እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡ እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ የምዘና ውጤቶች የሚሰጡት ኩባንው በገለልተኛ መንገድ በሚያካሂደው ምዘና በመሆኑ በየትኛውም የዓለም ክፍል ተቀባይነት እንዳለው ተመልክቷል፡፡

ሲጂአር ይህንን ውጤት ለኢትዮጵያ ጠለፋ መድን እንዲሰጥ ካስቻሉ ምክንያቶች መካከል በአሁኑ ወቅት ኩባንያው የደረሰበት የካፒታል አቅም ቢዝነሱን ለመቀጠል የሚያስችሉ የተመቻቹ ሁኔታዎች ያሉት በመሆኑ ጭምር እንደሆነ አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ሲቋቋም ሁሉም የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሚያገኙት እያንዳንዱ ዓረቦን አምስት በመቶ ለኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ እንዲሰጡ መደረጉ፣ እንዲሁም የኢንሹራንስ ኩባያዎች በዓመት ለጠለፋ መድን ሰጪዎች ከሚሰጡት ሥራ 25 በመቶ ለኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ በአዲሱ አዋጅ የተደነገገ መሆኑን፣ ቢዝነሱ ቀጣይነት እንዳለው የሚያመለክት በመሆኑ ጭምር ውጤቱ እንደተሰጠውም ተገልጿል፡፡

ኩባንያው በአዋጅ ከተሰጠው ሌላ 18ቱም ኩባንያዎች ለጠለፋ መድን ኩባንያው በፈቃደኝነት ቢዝነስ የሚሰጡት በመሆኑ በፋይናንስ ረገድ ጠንካራ የሚለውን ውጤት እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ የመድን ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ቢዝነስ ለመስጠት ቃል የገቡ በመሆኑም ተጨማሪ ዕድል ስለፈጠረለት በአፍሪካ ደረጃ እስከ 40 ዓመታት የሚደርስ ዕድሜ ላላቸው የጠለፋ መድን ኩባንያዎች ከያዙት የምዘና ውጤት የተቀራረበ ውጤት ሊያገኝ መቻሉም በአጭር ጊዜ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ኩባንያ እንደሚያደርገው የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና 17ቱ የመድን ኩባንያዎች የተቋቋመ መሆኑም፣ ለኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ሌላ ዕድል የፈጠረለት ስለመሆኑም የጠቆሙት የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ገቢው እየጨመረ መምጣትና ዝቅተኛ ወጪ ያለው ሆኖ መገኘቱም የተሻለ ውጤት እንዲያገኝ አስችሎታል ተብለው ከተጠቀሱ ነጥቦች መካከል የሚካተት ነው፡፡  

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ያለው ካፒታል አንድ ቢሊዮን ብር እንደሆነ የጠቆሙት የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች፣ አሁን ባለው ደረጃው ይህ ካፒታል የበለጠ ማድረግ ስላለበት በቀጣዩ ዓመት ካፒታሉን በእጥፍ ለመጨመር መታቀዱንም አመልክተዋል፡፡ ይህ የካፒታል ዕድገት በቀጣይ ለሚደረገው ምዘናም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

አሁን ባገኘው ውጤት መሠረት ከዚህ በኋላ የሚወዳደረው ከሌሎች ተመሳሳይ የአፍሪካ ኩባንያዎች ጋር በመሆኑ የካፒታሉ ዕድገት አስፈላጊ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅትም ቢሆንም ያለው 1.2 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ያለ መሆኑን ያሳያል ተብሏል፡፡  

ይህ የምዘና ውጤት ምን ያስገኛል በሚለው ዙሪያ አቶ ዳዊት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ስለኩባንያው ወቅታዊ አቋም ገለልተኛና ተዓማኒ በሆነ ኩባንያ መመዘኑና ከኩባንያው ጋር ለሚሠሩ ደንበኞች አስተማማኝ መረጃ የሚሰጥ በመሆኑ ተጠቃሚ ያደርጋል ይላሉ፡፡

በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ወጥቶ በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያ ለማምጣት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዳዊት፣ በአሁኑ ወቅት ከአንዳንድ የአፍሪካ ኩባንያዎች ጋር እየሠራ ቢሆንም፣ አሁን የተሰጠው ውጤት ከእነዚህ ኩባንያዎች ጋር የበለጠ ሥራ እንዲሠራ ያስችለዋል ብለዋል፡፡

ኩባንያው ባለፈው ዓመት ካገኘው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ሁለት በመቶው ከውጭ የተገኘ ገቢ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ፍቅሩ በበኩላቸው፣ አሁን ኩባንያው ያገኘው ውጤት ይህን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚያስችለው አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ለመሥራት በሚደረግ ሙከራ መጀመርያ የተረጋገጠ የምዘና ውጤት አምጡ ይሉ ስለነበር እንደ ልብ ለመሥራት ያላስቻሉ ሁኔታዎች ፈጥሮ እንደነበርም አስታውሰው፣ አሁን ለአገር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የሬቲንጉ መኖር ለደንበኞች መተማመን ስለሚፈጥር ኢትዮጵያ ከጠለፋ መድን ቢዝነስ የምታገኘውን ገቢ ያሳድግላታል፡፡

የፋይናንስ ዘርፍ ዝግ ቢሆንም በጠለፋ መድን ቢዝነሱ ግን ክፍት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹የተለያዩ አገሮች የጠለፋ መድን ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሠሩ የቆዩ በመሆኑ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የሚወዳደርም ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ውድድር በአሸናፊነት ለመወጣት ደግሞ ሬቲንጉ አስፈላጊ እንደነበር አመልክተዋል፡፡  

ኩባንያው እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድና እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገራዊ ራዕይ ይዞ ኢትዮጵያንም በዓለም አቀፍ መድረክ የሚወክል መሆኑንም አቶ ፍቅሩ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ከመቋቋሙ በፊት የጠለፋ መድን ሽፋን ለማግኘት ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሚያደርጉት ስምምነት እስከ 30 በመቶ የሚሆነው  በውጭ ምንዛሪ ለውጭ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያዎች ይሄድ ነበር፡፡

አሁን ይህንን በአገር ገንዘብ በሚገዛ ዓረቦን መሸፈን እየተቻለ መሆኑንም የገለጹት አቶ ፍቅሩ፣ ይህም ብዙ ለውጥ እያመጣ በመሆኑ ቀስ በቀስ ኢትዮጵያ ለጠለፋ መድን የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ እየቀነሱ ለመሄድ ብቻ ሳይሆን፣ በዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎችን በመሥራት ዘርፉን የማሳደግ ዕቅድ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 እንዲህ ያለውን ራዕይ ለማሳካት ኩባንያው ስትራቴጂ ቀርፆ እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳዊት፣ የዚህ ስትራቴጂ መተግበር በኢንዱስትሪው ብዙ ለውጥ ያመጣል ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ በየዓመቱ ያለውን ገቢ እያሳደገ የመጣ ሲሆን፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የዓረቦን ገቢውን ከ874 ሚሊዮን ብር በላይ አድርሷል፡፡ የትርፍ ምጣኔውንም ከ186 ሚሊዮን ብር በላይ አሳድጓል፡፡ 

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ አንድ ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ለኩባንያው የባለቤትነት ድርሻ 69.9 በመቶ የሚሆኑትን የያዙት 18ቱ የኢንሹራስ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ 30.76 በመቶውን ደግሞ ባንኮች፣ 2.33 በመቶ የተለያዩ ግለሰቦችና 0.01 በመቶው ደግሞ የሠራተኛ ማኅበራት ናቸው፡፡ ከባንኮቹ ትልቁ ባለድርሻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች