Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የቁጠባ ሒሳብ አስቀማጭ ደንበኞች ብዛት ከግል ባንኮች ቀዳሚ ሆነ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው የ2013 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.7 ቢሊዮን ብር ማትረፉን ያስታወቀው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ የቁጠባ ሒሳብ አስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር ከ7.73  ሚሊዮን በላይ በማድረስ ከግል ባንኮች ቀዳሚውን ሥፍራ መያዙን አመለከተ፡፡

ባንኩ የ2013 የሒሳብ ዓመት አፈጻሙን ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ እንዳመለከተው፣ በ2013 በገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር ከግል ባንኮች ቀዳሚውን ደረጃ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡

የደንበኞችን ቁጥር በማሳደግ በማኅበረሰብ ውስጥ በስፋት ዘልቆ መግባትን ከባንኩ ዋና ዋና ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች አንዱ በመሆኑ ይህንን ከዓመት ዓመት እያሳካ መሄዱን የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ፍቅሩ ዴክሲሳ (ዶ/ር) ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በአገሪቱ ያለው ዝቅተኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት፣ ከብሔራዊ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትና ከብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ጋር ተዳምሮ የባንክ አገልግሎትን ከፋይናንስ አቅርቦት ውጭ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማዳረስ የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰዱም ውጤት እንዳስገኘለት የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ 1.48 ሚሊዮን አዲስ አስቀማጮችን በማከል ከቀዳሚው ዓመት 24 በመቶ ዕድገት ያለው ውጤት መመዝገቡም ታውቋል፡፡

የአስቀማጮች ቁጥር እየተበራከተ መሄዱ ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ እያደገ እንዲመጣ ያደረገ ሲሆን፣ በ2013 መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ25.61 ቢሊዮን ብር ወይም በ56.3 በመቶ በማደግ 71.12 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ አስችሎታል፡፡

በ2013 የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ አፈጻጸም ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ባለአክሲዮኖችንና ደንበኞችን ጨምሮ ተጠቃሚ ማድረጉን ሲያረጋግጥ በበጀት ዓመቱ በአብዛኞቹ ቁልፍ የሥራ አፈጻጸም አመላካቾች የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው፣ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከ28.5 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ብድር ሰጥቷል ብለዋል፡፡

ይህም የባንኩን አጠቃላይ የተሰጠ የብድር መጠን 54.5 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተሰጠው ብድርም በ59.7 በመቶ ዕድገት የታየበት ስለመሆኑ የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ከተሰጠው ብድር ትልቁን ድርሻ የያዘው የአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎቶች ሲሆን፣ ይህም በባንኩ ከተሰጠ አጠቃላይ ብድር 36 በመቶ የሚሆነውን ይዟል፡፡

ዓለም አቀፍ የንግድ ፋይናንስ 28.9 በመቶ፣ የፋብሪካ ምርቶች 21.7 በመቶ በመያዝ ይከተላሉ፡፡ የተቀሩት ዘርፎች በአጠቃላይ 21.1 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው የባንኩን ዓመታዊ ክንውን በማስመልክት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጠቅሰዋል፡፡

የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን ደግሞ ከቀዳሚው ዓመት ቀንሶ 1.59 በመቶ ሳይበልጥ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 2.35 በመቶ ነበር፡፡

የባንኩን ዓመታዊ ገቢ በተመለከተ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፣ የ8.03 ቢሊዮን ብር  ገቢ አግኝቷል፡፡ ይህ የገቢ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ2.29 ቢሊዮን ብር ወይም 39.8 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው በዋነኝነት የተሰጠ ብድር መጠን መጨመር ነው፡፡ ከብድር ወለድ የተገኘ ገቢ ባንኩ በዓመቱ ማመንጨት ከቻለው አጠቃላይ ገቢ 67.5 በመቶው የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ከወለድ ገቢ ውጭ የተገኘ ገቢ ወደ 2.61 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት የ65.1 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

የባንኩ ወጪ ደግሞ በ64.6 በመቶ ጨምሮ 6.33 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ በዚህም ክንውኑ ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.7 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር 273.44 ሚሊዮን ብር ወይም የ19.2 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡

በሌላ በኩል በዲጂታል ባንኪግ ሥራዎች ላይ በስፋት ለመሰማራት በበጀት ዓመቱ የተደረገው ጥረት እንቅስቃሴያቸው እንዲሻሻልና ለደንበኞች የዲጂታል ምርቶችንና ፈጣን የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ አፈጻጸም ላይ መሻሻልን ማምጣቱ ተገልጿል፡፡

በ2013 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በኮቪድ ወረርሽኝ ተፅዕኖና አልፎ አልፎ በሚፈጠሩ የውጭ ጫናዎች ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል የተለያዩ የኢኮኖሚ ትንበያ ዘገባዎች አመልክተው እንደነበር የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ እነዚህ ውጫዊ ሁኔታዎች በጥቅሉ በባንክ ኢንዱስትሪው የሥራ አፈጻጸም ላይ በተናጠል በባንኩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ቢሆንም፣ ባንኩ ወሳኝና አበረታች አፈጻጸም ያስመዘገበበት ዓመት ነው ተብሏል፡፡

 ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ባንኩ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን፣ ከሰሞኑ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ የሚውል 70 ሚሊዮን ብር ስጦታ አበርክቷል፡፡ ይህንንም የስጦታ ቼክ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው ተረክበዋል፡፡

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 49 አዳዲስ ቅርንጫፎች ከፍቶ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 469 ያደረሰው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ፣ በተለይም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ቅርንጫፎችን በመክፈት ቀዳሚ ከሚባሉ ባንኮች አንዱ  ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ አጠቃላይ ካፒታሉን ስምንት ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ 4.65 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ተጨማሪ 1.65 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉንም የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች