Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ አስተዳደሩ የኮቪድ-19 ክትባት በትምህርት ቤቶች በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲሰጥ ማለቱ ቅሬታ ፈጠረ

 አስተዳደሩ የኮቪድ-19 ክትባት በትምህርት ቤቶች በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲሰጥ ማለቱ ቅሬታ ፈጠረ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ የኮቪድ-19 ክትባት በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲሰጥ ትዕዛዝ መተላለፉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ሪፖርተር ያነጋራቸው የተማሪ ወላጆች አስታወቁ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ሥር ለሚገኙ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች የተላከ ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ በወረርሽኝ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ 1112/2011 አንቀፅ 72/2 መሠረት መመርያ እንደወጣ አስታውቋል፡፡ መመርያ የማክበርና ማስከበር ግዴታ መሆኑን በደብዳቤው የተገለጸ ሲሆን፣ ክትባቱን ያልተከተቡ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎችና ተማሪዎች በሁለት ቀናት ውስጥ የኮቪድ-19 ክትባት እንዲከተቡ ያዛል፡፡

በሌላ በኩል በተለያየ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤት ለተማሪ ወላጆች በላኩት ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው ከወረዳ ጤና ጣቢያዎች የተላከላቸውን ደብዳቤ መሠረት በማድረግ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ለሆኑ ተማሪዎች የመጀመሪያው ዙር የኮቪድ-19 ክትባት እንዲያስከትቡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፣ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ሆኗቸው ያልተከተቡ ተማሪዎችን መንግሥት ያወጣውን መመርያ መሠረት በማድረግ ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይልኩ ትምህርት ቤቶቹን አስጠንቅቋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ አነጋግሯቸው ቅሬታቸውን የገለጹ የተማሪ ወላጆች እንዳስታወቁት፣ በዚህ ወቅት በትምህርት ቤቶች ውስጥ በጉንፋን ተህዋስ ያልተያዘ ተማሪ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ተማሪዎች እንዲከተቡ መገደዳቸው ተገቢና ልክ አይደለም ብለዋል፡፡ ከዚህ በሻገርም ተማሪዎች ካልተከተቡ ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ ማለት ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡

ከዚህ በሻገር ወላጆች ልጆቻቸው እንዲከተቡ ምን ያህል ግንዛቤ  ተሰጥቷቸዋል? የሚለው ሲታይ ልጆቻቸውን ድንገት አስከትቡ በማለት የቀረበላቸው መመርያ እንደ ዱብዕዳ የወረደ ጉዳይ ሆኖብናል ያሉት ወላጆች፣ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ወላጆች ልጆቻቸው ክትምህርት ሊባረሩ ነው የሚል ሥጋት እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ወላጆች ልጆቻቸውን ቢያስከትቡና ከክትባቱ ምልክቶች ጋር ተያይዞ ያልተጠበቀ ነገር ቢከሰት የሚመጣው ችግር አስጊ እንደሆነም ወላጆቹ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ነገር በድብዳቤ ከመገለጹ በፊት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና ጤና ቢሮ እንዲሁም በስሮቻቸው የሚገኙት አካላት ወላጅንና የትምህርት ቤት ማኅበረሰብን አስቀድመው ማወያየት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎችና የትምህርት ቤት ማኅበረሰቦች በአንደኛ ዙርም ሆነ በሁለተኛ ዙር ለመስጠት በቂ የሆነ ክትባት ዶዝ ስለመኖሩ ሥጋት እንዳላቸው የገለጹት ወላጆች፣ ለክትባቱ ማስቀመጫ የሚሆን ማቀዝቀዣ በየትምህርት ቤቱ ሊኖርና ሊሟላ ይችላል የሚለው በራሱ በትክክል የማይታወቅ እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ አበበ ቸርነት በጉዳዩ ላይ ለማናገር ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ኃላፊው በጉዳዩ ላይ ሙሉ ዝርዝር መረጃ የሚገኘው ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ እንደሆነ አስታውቀው፣ በትምህርት ቢሮ በኩል ክትባቱ ለምን እንዴት ይሰጣል የሚለውን መመለስ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

የክትባቱ አተገባበር በተለላፈ ሰርኩላር መሠረት እንደሆነ ያስታወቁት አቶ አበበ፣ ስለ ሰርኩላሩ ምንነት፣ ክትባቱ በምን መልኩ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ቢገልጹም በተደጋጋሚ ላደረግንላቸው የስልክ ጥሪ ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የእናቶችና ሕፃናት ዳይሬክተር ቤተልሔም ታዬ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ አስገዳጅነቱን በተመለከተ መረጃ ማቅረብ ያለበት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እንደሆነ ተናግረው፣ ጤና ቢሮው መስጠት የሚችለው መረጃ ክትባቱ ትምህርት ቤቶች ላይ እንዴት ነው እየተሰጠ ያለው? ምን ያህል ተማሪዎች ተከተቡ? በሚለው ዙሪያ ላይ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ክትባቱ በትምህርት ተቋማት ላይ በአስገዳጅ ሁኔታ ይሰጣል አሊያም አይሰጥም የሚለው መመለስ ያለበት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ እንዳስታወቀው 321,771 የሚደርሱ ተማሪዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 103,890 የሚሆኑት የኮቪድ-19 ክትባት ወስደዋል፡፡ በተጨማሪም 46,908 የሚደርሱ መምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ሲኖሩ፣ ከዚህ ውስጥ 19,848 የሚሆኑት እንደተከተቡ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...