ያራ ዳሎልና ሰርከም ሚነራልስ የተባሉ ሁለት የውጭ ኩባንያዎች፣ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማምረት ካልጀመሩ፣ በኢትዮጵያ ያላቸውን የማዕድን ፈቃድ ለመመለስ መስማማታቸውን ለመንግሥት አስታወቁ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሁለቱ ኩባንያዎች ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ እ.ኤ.አ. በ2017 ፈቃድ እንዲሰጣቸው የወሰነ ሲሆን፣ የማዕድን ሚኒስቴርም በዚያው ዓመት ለሁለቱም ኩባንያዎች በአፋር የሚገኘውን የፖታሽየም ማዕድን እንዲያለሙ ፈቃድ መስጠቱን ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ነገር ግን ኩባንያዎቹ ፈቃድ ካገኙበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ዓራት ዓመታት ያካሄዱት የፕሮጀክት ልማት ባለመኖሩ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቢሆንም የተለወጠ ነገር ባለመኖሩ፣ የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከኩባንያዎቹ አመራሮች ጋር በቀጥታ በመወያየት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ምንጮች ገልጸዋል።
ሁለቱ ኩባንያዎች በሚኒስትሩ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያና ምክረ ሐሳብ መሠረት አድርገው በተናጠል በጻፉት ደብዳቤ፣ በተቀመጠላቸው አዲስ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ወደ ምርት ሒደት ካልገቡ የተሰጣቸውን ፈቃድ ለመመለስ ስምምነት ማድረጋቸውን ሪፖርተር የተመለከተው የኩባንያዎቹ ደብዳቤ ያመለክታል።
‹‹እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 4 እና 5 ቀን 2021፣ እንዲሁም ዲሴምበር 17 ቀን 2021 ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በተደረጉት ስብሰባዎች በተሰጡን መመርያዎች መሠረት የፖታሽ ማዕድኑን እ.ኤ.አ. እስከ ኤፕሪል 7 ቀን 2026 ድረስ ማምረት መጀመር ካልቻልን፣ የፈቃድ መብታችንን አሳልፈን የምንሰጥ መሆናችንን በሰርከም ሚኒራልስ ሊሚትድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስም አረጋግጣለሁ፤›› በማለት የሰርከም ሚኒራልስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢያን ስታከር ረቡዕ ታኅሳስ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ለማዕድን ሚኒስቴር በላኩት ደብዳቤ ገልጸዋል።
በአፋር ክልል ደናኪል አካባቢ በሚገኘው በደናኪል የፖታሽ ክምችት ከፍተኛ የማዕድን ማውጣት ፈቃድ የወሰደው ሰርከም ሚኒራልስ ሊሚትድ፣ በ365 ካሬ ኪሎ ሜትር የፈቃድ ቦታ ውስጥ የተከማቸ 4.9 ቢሊዮን ቶን ፖታሽየም ለማምረት የ20 ዓመት ፈቃድ እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ያራ ዳሎል ኩባንያም ተመሳሳይ ደብዳቤ ለማዕድን ሚኒስቴር መላኩን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
‹‹በመጀመሪያ እ.ኤ.አ. በኖቤምበር 12 ቀን 2021 በፕሮጀክታችንና በሥራ ፕሮግራማችን ላይ ጊዜ ወስደን እንድንወያይ ስላደረጋችሁ እናመሠግናለን። ሚኒስትሩ በስብሰባው በሰጡት መመርያ መሠረት የፖታሽ ማዕድኑን እስከ ዲሴምበር 2025 ድረስ ማምረት ካልጀመርን የፈቃድ መብታችንን ለማስረከብ መስማማታችንን እንገልጻለን፤›› ሲሉ የኩባንያው ቦርድ ሰብሳቢ ጆርጅ ማግነስ ስቴንቮልድ፣ ከሦስት ሳምንት በፊት ለማዕድን ሚኒስቴር በተላከው ደብዳቤ አስታውቀዋል።
ያራ ዳሎል ላለፉት በርካታ ዓመታት ለኢትዮጵያ ማዳበሪያ በማቅረብ የሚታወቀው፣ የኖርዌይ ግዙፍ ማዳበሪያ አምራች ያራ ኢንተርናሽናል እህት ድርጅት ነው።
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ታከለ (ኢንጂነር) ሁለቱ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎች ኩባንያዎችንም የማጥራት ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
‹‹የማዕድን ሀብታችን ሳይለማ መቅረት የለበትም። በመሆኑም የልማት ፕሮጀክቶችን ባዘገዩ ኩባንያዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ጀምረናል ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።