Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ የተወሳሰበ ዲፕሎማሲ ካካሄደችባቸው ዘመቻዎች ይኼኛው አንዱ ነው›› ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣...

‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ የተወሳሰበ ዲፕሎማሲ ካካሄደችባቸው ዘመቻዎች ይኼኛው አንዱ ነው›› ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ

ቀን:

በአገሪቱ የሰሜኑ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት አስታኮ አገሮችና የተለያዩ ተቋማት ያሏቸውን ፍላጎቶች ለማስፈጸም በማሰብ፣ የተለያዩ ጫናዎችን እያደረጉ እንደሚገኙ በመጠቆም፣ የዚህ ዘመን ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ ከአሁን ቀደም ካስተናገደቻቸው የተወሳሰቡ ዲፕሎማሲዎች ጋር ሊስተካከል የሚችል ነው፤›› ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ተናገሩ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት የአዲስ ወግ መድረክ ላይ፣ ‹‹ህልውናን መጠበቅ፣ ዕድገትን ማዝለቅ›› በሚል ርዕስ ንግግር ያደረጉት አምባሳደሩ፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተሠራው ዲፕሎማሲ፣ ‹‹ምናልባትም ኢትዮጵያ በታሪኳ የተወሳሰቡ ዲፕሎማሲዎችን ካካሄደችባቸው ዘመኖች አንዱ ይኼኛው ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የሰብዓዊ ዕርዳታ ያደርሳሉ የሚባሉ ድርጅቶቹ ማንነት የተገለጠበት፣ እንዲሁም የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቶቻቸው አንድ በመቶ ብቻ እንደሆነና ሌላ ፍላጎቶች ያላቸው መሆኑን በማውሳት ያብራሩት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ‹‹በሌላ ቦታ ሲባል ስንሰማው በከፊል የምንጠረጥረው ቢሆንም፣ እኛ ላይ ሲደርስ ግን እውነታውን ያየንበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ለፖለቲካ ፍላጎቶች ሲሉ መረጃ የሚያጣምሙ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትገኝበት አካባቢ ሚና እንደነበረው የጠቆሙት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ጉዳዩን የከበቡት የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚና የተፅዕኖ ፈጣሪነት ፍላጎቶች ዲፕሎማሲውን ከባድ አድርገውታል ብለዋል፡፡

በእነዚህ የተዛቡ ፍላጎቶች ሳቢያ በርካታ ልዑካን ወደ ቀጣናው ሲመደቡ እንደነበር፣ ከአገሮች መሪዎችና ከተለያዩ የአካባቢ/ቀጣናዊ ተቋማት መሪዎች ጋር ከአሁን ቀደም በዓመት አንዴ ለማግኘት አዳጋች የነበረውን፣ አሁን በሳምንት ሁለቴ እስከ ማግኘት የደረሰ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን የጠየቀ ዘመን እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ‹‹ገንዘብ ስለሰጡ ብቻ የፈለጉት እንዲሆን መፈለግ፣ እንዲሁም አዘቅዝቆ የመመልከት ፍላጎት ታይቷል›› ያሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያውያን በተለይም ዳያስፖራው ባሳየው አንድነት ሳቢያ፣ ‹‹እስካሁን ከመጣንበት የምንሄድበት አቅም በእጃችን ነው፤›› ብለዋል፡፡ የአንዳንድ አገሮች ጥቂት ግለሰቦች ካላቸው የፖለቲካና ሌላ ፍላጎት የተነሳ ሲያስቸግሩ እንደነበርና ትዕዛዝ ለመስጠት መፈለጋቸውን፣ ወዳጅና የንግድ አጋር ለመምረጥ የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለም አክለዋል፡፡

ሆኖም በተለያዩ ተፅዕኖዎች ሳቢያ የአገሪቱ የመደመጥ አቅም ማደጉን በማንሳት፣ ለወደፊት የውስጥ ጥንካሬን በማሳደግ በሁለት እግር መቆምና የዳያስፖራውን ተሳትፎ ተቋማዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ኢኮኖሚውን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ በበኩላቸው፣ የጦርነቱ ተፅዕኖ ከባድ ቢሆንም እስካሁን መቋቋም ተችሏል ብለዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ጥሩ እንደነበረና ጦርነቱ በጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ላይ የነበረው ተፅዕኖ አነስተኛ እንደሆነ በመግለጽ፣ ዘንድሮ ግን ከሁለት ሚሊዮን ዜጎች በላይ መፈናቀላቸውንና በርካታ ንብረት መውደሙን በማስረዳት፣ ከፍተኛ ጫና እየደረሰ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውሉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን ለመግዛት አሥር ቢሊዮን ብር መውጣቱን ተናግረው፣ የፀጥታ ኃይሎችን ማደራጀት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ከልማት ሥራዎች የሀብት ማሸጋሸግ በመደረጉ ኢኮኖሚውን ፈትኗል ብለዋል፡፡

ሆኖም የወጪ ንግድ በመጠንም በዋጋም በማደጉ፣ እንዲሁም የግብርና አፈጻጸም በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች መልካም ስለነበር የኢኮኖሚውን አይበገሬነት አግዟል ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የመንግሥት ቀጣይ የኢኮኖሚ ትኩረት የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የተቋረጡ የመሠረተ ልማትና አገልግሎቶችን ማስቀጠል፣ እንዲሁም አጠቃላይ የጉዳትና የጥፋት መጠንን ጥናት መሥራት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጥናት የሚከናወነውም በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ፣ እንዲሁም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ አማካይነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ የመልሶ ግንባታ ሥራውን ለማገዝ የተጨማሪ በጀት አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደቀረበና ወደ ፓርላማ ተልኮ ሲፀድቅ መጠኑ እንደሚገለጽ አስረድተዋል፡፡  

አቶ አህመድ አክለውም ኢትዮጵያ ካለችበት ቀጣና አንፃር ትልቅ ኃላፊነት ስላለባት፣ ያለባትን ችግር ፈትታ የሰላም ማዕከል መሆኗን ማሳየት ይኖርባታል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...