Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሽብርተኝነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሕንፃዎችን የተከራዩ ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ውል እየፈጸሙ መሆኑ ታወቀ

በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሕንፃዎችን የተከራዩ ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ውል እየፈጸሙ መሆኑ ታወቀ

ቀን:

በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሕንፃዎች ውስጥ ተከራይተው በንግድና በሌሎች ተግባራት የተሰማሩ ሕጋዊ ተከራዮች፣ ቤቶቹን በጊዜያዊነት ከሚያስተዳድረው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ውል እንዲያስሩ እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር ከኮርፖሬሽኑ ያገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የእነ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ የብርጋዴር ጄኔራል ተክላይ አሸብር፣ የሜጀር ጄኔራል ምግበ ኃይለ፣ የኮሎኔል ፀሐዬ ኪዳኑ፣ የአቶ ዓባይ ፀሐዬና ቤተሰቦቻቸው፣ እንዲሁም በበርካታ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ስም የሚገኙ 25 ሕንፃዎችና የንግድ ተቋማት በጊዜያዊነት በኮርፖሬሽኑ ሥር እንዲተዳደሩ የተደረገ ሲሆን፣ የንብረቶቹ ዕጣ ፈንታ በፍርድ ቤት እስከሚወሰን ድረስ የቤቶቹ ተከራዮች ባሉበት ይዞታና የኪራይ መጠን አዲስ ውል ከኮርፖሬሽኑ ጋር እንዲፈጽሙ ተደርጓል፡፡

በፍርድ ቤት ውሳኔ በኮርፖሬሽኑ ሥር እንዲተዳደሩ አዳዲስ ንብረቶች እንደሚጨመሩ ለሪፖርተር ያስረዱት የኮርፖሬሽኑ ባለሙያ፣ ሕግና ምህንድስናን ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩ አምስት አባላትን ያቀፈ ኮሚቴ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ኮሚቴ አማካይነት ንብረቶቹ እንደሚተዳደሩና የኪራይ ገንዘቡም በፍርድ ቤት በሚወሰን መጠን የአስተዳደር ወጪ ተቀንሶ ለእዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ የባንክ የሒሳብ እንደሚጠራቀም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ እነዚህ አምስት አባላት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (አሁን ፍትሕ ሚኒስቴር) አቅራቢነት በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. በፍርድ ቤት የዚህ መሰል ሥራ ልምድ ያላቸው መሆናቸው ተመስክሮላቸው የተሾሙ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኮርፖሬሽኔ ቅርንጫፍ ሦስት ሥር ብቻ በእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ 142 ቤቶች እንደሚገኙ፣ ምንጩ ባልታወቀ ገንዘብ የተገነቡ፣ አልያም የሚያስገኙት ጥቅምና ሕንፃዎቹ ለሽብር ተግባር እንዳይውሉ ታስቦ ይኼ ውሳኔ መተላለፉ የታወቀ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ጥፋት ያለባቸው አካላት ንብረቶች ወደ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ባለቤትነት እንደሚተላለፉና ጥፋት የሌለባቸው ደግሞ ለባለንብረቶቹ እንደሚመለሱ በሙያው ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ለማስወሰንም በችሎት ቀርበው ክርክር በማድረግ ላይ የሚገኙ እንዳሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ክርክር ላይ የማይገኙ መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

አንዳንዶቹ ባለንብረቶች በተወካዮቻቸው አማካይነት ያከራዩ እንደነበርና የቤት ኪራይም የሚከፈላቸው በእነርሱ ስም በማይገኝ የሒሳብ ቁጥር እንደሆነ በመግለጽ፣ አንዱ የሒሳብ ቁጥር ሲዘጋ እስከ አምስት ድረስ የሒሳብ ቁጥር ያላቸው በመሆኑ በተለያዩ ሐሳቦች የኪራይ ገንዘቦቻቸውን ይሰበስቡ እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ ከሽብር ወንጀል ጋር ግንኙነት ያላቸው ውል ሳይዋዋሉ እንዲወጡና የተከራዩት እንዲታሸጉ፣ እንዲሁም በአስተዳደርና እንደ ጥበቃ ባሉ የሕንፃ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ተነስተው በአዳዲስ ሰዎችና አስተዳዳሪዎች እንዲተኩም ተደርጓል፡፡

ቤቶቹን በጊዜያዊነት ተረክቦ የማስተዳደር ውሳኔ የተላለፈው ገንዘቡ ለእኩይ ዓላማ እንዳይውልና በንብረቶቹ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ታስቦ እንደሆነ የገለጹት ባለሙያው፣ የቤቶቹ ርክክብ ከመደረጉ በፊት ከፀጥታ አካላት ጋር በመጣመር ምርመራና ፍተሻ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡ በእነዚህ ፍተሻዎችም በርካታ የጦር መሣሪያዎች ተይዘዋል ብለዋል፡፡

በዚህ አግባብ የሚተዳደሩ ቤቶችን የማጣራት ሥራ አስቀድሞ ተሠርቶ ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከኮርፖሬሽኑ አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጎ ፍርድ ቤት ሲወስን፣ ለየቅርንጫፎች እንደሚተላለፉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም እዚህን ቤቶች በተመለከተ በየሦስት ወሩ ለአራዳ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሪፖርት እንደሚደረግ፣ በየሁለት ሳምንቱ ደግሞ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ግምገማ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

ከቤቶቹ ኪራዮች ከአንድ ሕንፃ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በወር እንደሚገኝ የተናገሩት ባለሙያው፣ አስቀድሞ ዝግጅት ሲደረግ ስለነበረም በሕንፃዎቹ መያዣነት ከፍተኛ የሆነ ብድር ከባንክ ስለተወሰደ በኪራይ የሚገኘው ገንዘብ ወደ ዕዳ መክፈያነት እንዲዘዋወርም ጥያቄ እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም አንዳንድ ተከራዮች ከአከራዮቻቸው ጋር በመመሳጠር የኪራይ ዋጋ ቀንሰው በመናገር፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በእዚህ ዋጋ ውል በመግባት የተቀረውን ገንዘብ ከአከራዮቻቸው ጋር ለመከፋፈል ሲሠሩ የተደረሰባቸውም እንዳሉ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም ሁለት ካርታ ያላቸው ንብረቶችም በመኖራቸው የማጣራት ሥራውን አዳጋች አድርጎታል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ አንዱ አስቸጋሪ ጉዳይ ሕንፃዎቹንና ቤቶቹን የተከራዩት የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ስለሚገኙበት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገርና የአሜሪካ ኤምባሲን በመቅረብ እየተሠራ መሆኑን፣ ለአብነትም ለዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር በወር በ21 ሺሕ ዶላር የተከራየውን የኮሎኔል ፀሐዬ ኪዳኑን ቤት በምሳሌነት በማንሳት ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

የኪራይ ውላቸው በዚህ አሠራር መሠረት ያልተራዘመላቸው ተከራዮች የለቀቋቸውን ይዞታዎች ለማከራየት ጨረታ እንደሚወጣ፣ ተጨማሪ ማጣራት ለማድረግም ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...