በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቡድኖችና አገረ መንግሥቱ ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ የሚችሉት ‹‹አንዳቸው ሲጠፉ ነው›› በሚል አመለካከት የተነሳ የሚታየው ፍትጊያ፣ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ብሔራዊ ምክክር አካል መሆን እንዳለበት ተጠቆመ፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ‹‹ሰላም፣ ደኅንነት፣ ዲፕሎማሲና ልማት በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይደረግ?›› በሚል ርዕስ ታኅሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሁራንን ያካተተ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ ዴሞክራሲና ልማት፣ ደኅንነት፣ ዲፕሎማሲና ሰላም በሚሉ ርዕሶች ተጋባዥ ምሁራን ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም መምህርና ‹‹ብሔራዊ ደኅንነት በኢትዮጵያ›› በሚል የጥናት ርዕስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉት አቶ ዮናስ ታሪኩ ‹‹ደኅንነት›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ‹‹የማንን ደኅንነት እናስጠብቅ›› የሚለው ላይ አለመግባባት መኖሩንና በዚህም ምንክያት የአገሪቱ ደኅንነት ፍትጊያ ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል፡፡
ቋንቋና ባህላቸውን ከመዋጥ ለመጠበቅ የሚፈልጉ ቡድኖች የአገረ መንግሥቱ ደኅንነት መጠበቅ እንቅፋት ይሆንብናል የሚል ሐሳብ እንዳላቸው ሁሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ የአገረ መንግሥቱን ደህንነት ማስጠበቅ የሚሹ አካላት የቡድኖች መብት መጠበቅ እንደሚያሰጋቸው ገልጸዋል፡፡ የዚህም አንዱ ምክንያት ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ማለት ማንን ያካትታል የሚለው ግልጽ አለመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የቡድን መብቶችን ማስጠበቅ የሚፈልጉ አካላት አገረ መንግሥቱ ላይ የቅቡልነት ጥያቄ እንደሚያነሱ አስረድተዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች አገረ መንግሥቱንና መንግሥትን ነጣጥሎ ማየት አስቸጋሪ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዮናስ፣ አገዛዙም የራሱን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲል በአገረ መንግሥቱ ስም ቡድኖች ላይ ሥጋት ሊፈጥር የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡
‹‹በሁለቱ መካከል ያለው መሳሳብ ነው እዚህ ያደረሰን›› ያሉት መምህሩ፣ የሁለቱም አካላት ደኅንነት እርስ በርስ የሚጋጭ መስሎ መቅረቡ ለበዙ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሁለቱን አመለካከቶች ባነገቡ ኃይሎች መካከል የሚደረጉት ተደጋጋሚ ግጭቶችም በምላሻቸው የቡድኖችንና የአገረ መንግሥቱን ደኅንነት በሌሎች ለሚቃጣ ጥቃት እንዳጋለጡት ገልጸዋል፡፡
አቶ ዮናስ እንደሚናገሩት ኢትዮጵያ የምትገኘው የበዙ አገሮች ፍላጎት በሚንሸራሸርበት የቀይ ባህር ቀጣና ውስጥ እንደመሆኑ ከውጪ የሚመጡ ጥቃቶች ቀላል የሚባል ጫና ያላቸው አይደሉም፡፡ ከውጭ የሚመጡት ሥጋቶች መነሻቸው የአገር ውስጥ ግጭት በመሆኑም ከውጭና ከውስጥ የሚመጣን ሥጋት ነጣጥሎ ማየት አስቸጋሪ እንደሆነ አክለዋል፡፡
እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የመንግሥት ሥርዓቶች የተለያዩ ጥያቄዎችን መመለስ ቢችሉም በአገረ መንግሥቱና በቡድኖች መካከል ያለውን መሳሳብ ማስወገድ አልቻሉም፡፡ ‹‹የመሬት ላራሹ ትግል የመደብ ጥያቄን ሲመልስ የብሔር ጥያቄን ዘሎታል›› ብለው ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ሲቆጣጠር የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን በመዘርጋት የብሔር ጥያቄን ቢመልስም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 39 ላይ ‹‹የራስን ዕድል መወሰን እስከመገንጠል›› በማለቱ አገረ መንግሥቱ የፀና መሠረት እንዳይኖረው እንዳደረገ አስረድተዋል፡፡
የአገረ መንግሥቱ ደኅንነት ለቡድኖች ሥጋት፣ የቡድኖች ደኅንነትም ለአገረ መንግሥቱ ሥጋት መሆኑ መቆም እንዳለበት ያስረዱት አቶ ዮናስ፣ ይኼንን መፍታት የሚቻለው በንግግር በመሆኑ በቀጣይ ሊካሄድ በታሰበው ብሔራዊ ምክክር ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በተለያዩ አካላት መካከል በሚደረጉ ምክክሮች ‹‹የቡድኖች ደኅንነትን ማሳካት የሚቻለው በአገረ መንግሥቱ መፍረስ ላይ ነው›› የሚል አስተሳሰብን መቅረፍ እንደሚገባ፣ የአገረ መንግሥት ደኅንነት ውስጥ የቡድን ደኅንነት የማይካተትና የቡድኖች ደኅንነት በራሱ አደጋ እንደሆነ ማሰብም መታረም እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
ማኅበራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የሰጠ የደኅነት ፖሊሲና ተቋም እንደሚያስፈልግ ያሰመሩት አቶ ዮናስ ‹‹ይሄ ሊመጣ የሚችለው መሠረተ ሰፊና ጥልቅ ውይይት ሲደረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሌላኛው ጽሑፍ አቅራቢ አስናቀ ከፍአለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ወደ ዕርቅና ብሔራዊ መግባባት እንዴት ነው የምንገባው የሚለው ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከጦርነቱ ዳፋ ለመውጣት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፣ ለዚህም ‹‹ከውጪ ተሞክሮ ይልቅ ወደ ውስጥ መመልከት ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አንድ ፓርቲ በተደጋጋሚ ሥልጣኑን እንዲቆናጠጥ ዕድል የሰጠውን የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት በድጋሚ መፈተሸ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሰላም›› በሚል ርዕስ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው የጦርነቱ መነሻ ምክንያቶችን በሳይንሳዊ መንገድ ዘርዝሮ በማስቀመጥ እንዳይደገም መሠራት አለበት የሚል ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡