Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በስምምነት መፍታት የሚያስችል መመርያ ወጣ

የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በስምምነት መፍታት የሚያስችል መመርያ ወጣ

ቀን:

በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በተከራካሪ ወገኖች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በስምምነት ለመፍታት፣ በፍርድ ቤቶች ላይ በሚኖር የመዝገቦች መደራረብ ምክንያት ዕልባት ሳያገኙ የሚቆዩ ጉዳዮችን ጊዜ ለመቀነስና ፈጣን የፍትሕ ሥርዓት ለማስፈን ያስችላል የተባለና ‹‹የፌዴራል ፍርድ ቤት መር አስማሚነት›› የሚል ስያሜ የተሰው መመርያ ወጣ፡፡

መመርያው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስተባባሪነት በፌዴራል የመጀመርያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሥራ ላይ የሚውል ሲሆን፣ በፍትሕ ሥርዓቱ መጎልበትና በተከራካሪ ወገኖች መካከል ቀጣይነት ያለው ግንኙነትና መቻቻል እንዲኖር፣ ጊዜ የሚወስዱ የክርክር ሒደቶችን የተቀላጠፉ ከማድረግ ባለፈ ጉዳዩን በስምምነት ከመፍታት ባለፈ ለባለ ጉዳዮች አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓትን ተደራሽ እንደሚያደርግ ይገልጻል፡፡

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ፊርማ ፀድቆ በሥራ ላይ እንዲውል የተደረገው፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 45/8/ እና 48/45 ድንጋጌ መሠረት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መሆኑን መመርያው ያብራራል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መመርያው 53 አንቀጾችን የያዘ ሲሆን፣ ከታኅሳስ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ መዋሉም ታውቋል፡፡

የአገሪቱ የንግድና ሌሎች የፍትሐ ብሔር ክርክር ጉድለት እንደሆነ የሚነሳው የፍርድ ቤት መርህ አስማሚነት ሥርዓት አለመኖር፣ በተለይ በተከራካሪ ወገኖች መካከል ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲበላሽና በፍርድ ቤት ሒደቶች የገንዘብና የጊዜ ብክነት እንዲፈጠር አድርጓል ሲሉ የተለያዩ ጥናቶችና የፕሮጀክት ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

የሙግት ውሳኔ የራስ እንደሆነ፣ መነሻው ከእያንዳንዱ ሰው እንደሚመነጭና ተመሳሳይ ጉዳይ ገጥሟቸው ፍርድ ቤትን የሚመርጡና ከፍርድ ቤት ውጪ ጉዳያቸውን የሚጨርሱ ተከራካሪዎች እንዳሉ የሚጠቁሙት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ አማካሪና በማናቸውም ፍርድ ቤቶች ጠበቃ አቶ ታምራት ኪዳነ ማርያም፣ ያላግባብ የከሰሱ ወይም ያላግባብ የተከሰሱ ሰዎች በክርክር ከመግፋታቸው በፊት እዲያስቡና በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለ መልካም ግንኙነት እንዳይበላሽ ሊያግዝ የሚችል አሠራር ነው ይላሉ የፍድር ቤት መርህ አስማሚነት፡፡

በፍርድ ቤት ሒደት አሸናፊና ተሸናፊ እንደሚኖር፣ ነገር ግን ይኼ አሠራር ማኅበራዊ ሰላምን የሚፈጥር፣ የኅብረተሰቡን መልካም ግንኙነት ሳይበላሽ እንዲቀጥል የሚረዳ፣ የፍርድ ቤቶችን ሥራ እንዲቀንስ ዕድል የሚሰጥ፣ የፍርድ ቤት ጊዜ እንዳይባክን የሚያግዝ፣ አገር ለሙግት የምታባክነውን ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ የሚቀንስ፣ እንዲሁም ፍትሕ በቶሎ እንዲሰፍን ዕድል የሚሰጥ እንደሆነም ያምናሉ፡፡

ፍርድ ቤት ቀርበው የክስ ሒደት መሰማት ባልጀመረባቸው ጉዳዮች ላይና በየትኛውም ሒደት ላይ ቢሆንም፣ ተከራካሪ ወገኖች ጉዳዩን በስምምነት ለማየት ፍላጎት ካላቸው በእነሱ ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው መመርያ፣ በነፃ ፈቃዳቸው ላይ የተመረኮዘ ማስማማት ይደረጋል ይላል፡፡

በዚህ ሒደት አስማሚ ሆነው የሚመደቡ ሰዎች የማመቻቸት ኃላፊነት ብቻ ተሰጥቷቸው እንደሚሠሩና ውሳኔ ሰጪ እንዳልሆኑ ለተከራካሪ ወገኖች ማሳወቅ እንደሚገባቸው የሚጠቅሰው መመርያው፣ የውሳኔ ሰጪነት ኃላፊነት ያለው በተሟጋች ወገኖች ዘንድ መሆኑን ያብራራል፡፡

አስማሚዎቹ በዚህ ሒደት ገለልተኛና ሁለቱንም ባለጉዳዮች እኩል ማየት አለባቸው በማለት በማስማማቱ የሚገኙ የቃልም ሆነ የጽሑፍ ማስረጃዎችና ኤግዚቢቶች መጠበቅ እንዳለባቸው፣ በሒደቱ ላልተሳተፈ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው የማይሰጡ እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡

በዚህ ሒደት የሚገኙ መረጃዎችም ምናልባት የማስማማት ሒደቱ ባይሳካ ለፍርድ ቤት እንደ ማስረጃ ሊቀርቡ እንደማይችሉና ቢቀርቡም ዳኞች ሊቀበሏቸው እንደማይችሉ የሚናገሩት አቶ ታምራት፣ ከዚህ ባለፈ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን ወደ አስማሚዎች እንዲሄዱ ከማድረጋቸው በፊት የሕግና የማስረጃ ድጋፍ ያላቸው ክርክሮች መሆናቸውን እንደሚያጣሩና የቃል ክርክር ከመደረጉ በፊት ለማስማማት እንደሚሞከር ያስረዳሉ፡፡ በአስማሚዎች ጥረት ሊስማሙ ያልቻሉ ተከራካሪዎች ተመልሰው ወደ ፍርድ ቤት ሊመጡና ጉዳያቸውን ሊቀጥሉ የሚችሉ መሆናቸው፣ ከፍርድ ቤቱ ሥርዓት ጋር የሚጣጣም ነው ይላሉ፡፡

ፍርድ ቤቱ ለአስማሚነት የሚመረጡ ሰዎችን በቅጥር፣ በአስማሚዎች ዝርዝር መዝገብ (ሮስተር) አልያም በተከራካሪዎች ምርጫ ሊሰይም እንደሚችል የተደነገገ ሲሆን፣ እነዚህ አስማሚዎች የገንዘብ ተመን ለሌለው ክርክር በመጀመር ቀጠሮ 2‚000 ብር፣ ከዚያ በኋላ ላሉ ቀጠሮዎች 1‚000 ብር ከተተመነለት የቤተሰብ ክርክር በስተቀር 1‚500 ብር ይከፈላቸዋል ይላል፡፡

በገንዘብ ለሚተመኑ ክርክሮች ደግሞ እንደ ገንዘቡ መጠን ከ500‚000 ብር እስከ መቶ ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ ላሉ ክርክሮች ከአንድ በመቶ እስከ 0.005 በመቶ ድረስ ክፍያ ይሰጣቸዋል፡፡ ሆኖም ከመቶ ሚሊዮን አንድ ብር በላይ ካሉ ክፍያዎች በስተቀር፣ ለሌሎች ክፍያዎች ከ26‚000 ብር እስከ 62‚375 ብር ድረስ ያሉ የክፍያ ጣሪያዎች ተቀምጠዋል፡፡ ክፍያውም ተስማሚዎቹ በተለየ መንገድ ካልወሰኑ በስተቀር በሁለቱ ወገኖች የሚሸፈን ይሆናል፡፡ በፍርድ ቤት የሚሾሙ አስማሚዎች ግን በደመወዝ የሚሠሩ ናቸው፡፡

የአስማሚነት ሥራ ባለጉዳዮች ጉዳዮቻቸውን ራሳቸው ለመፍታት እንዲችሉ እስካሁን ያልነበረን ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ፣ ካሁን ቀደም ይተገበር የነበረው ፍርድ ቤት ሳይመጡ አልያም ፍርድ ቤት ከመጡ በኋላ ደህና ሽማግሌ ከተገኘ ብቻ ይሆን የነበረ ነው በማለት፣ ብዙዎች ራሳቸው የሚፈቱበትን ዕድል በማጣት ለዓመታት ፍርድ ቤት ሲንከራተቱ ይታያሉ ይላሉ አቶ ታምራት፡፡ ይኼም ንግድ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዳይካሄድ፣ ክርክሮች በቶሎ እንዳይቋጩ፣ ፍትሕ እንዲጓተት፣ እንዲሁም የፍርድ ቤት ሥራ እንዲወዘፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

የንግድ ክርክሮችን በተመለከተ በግልግል ዳኝነት የሚታይበት አሠራር መኖሩ ዕሙን ቢሆንም ይኼኛው ግን እንደ ግልግል አስገዳጅ ውሳኔ የሚኖርበት እንዳልሆነ፣ በተከራካሪዎች ስምምነት በራሳቸው የሚወስኑት ውሳኔ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ታምራት፣ በሙግት የሚጠፋ ገንዘብና ጊዜ ለሥራ እንዲውል ያግዛል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ይኼ አሠራር መኖሩ ተሟጋቾች ችግሮቻቸውን በባህላዊ መንገድ ለመፍታት ሊያበረታታቸው እንደሚችል በመጠቆም፣ ሕጉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓትን ማካተት ቢችልና ይኼ ማሻሻያ ቢታከልበት የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...