Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹ዕቅዳችን ከምድባችን ማለፍ ነው››የዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ

‹‹ዕቅዳችን ከምድባችን ማለፍ ነው››የዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ

ቀን:

ከሁለት ሳምንት በኋላ በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ዝግጅቱን በዚያው በካሜሩን ያውንዴ ለማድረግ እሑድ ታኅሳስ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ሥፍራው አቅንቷል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዝግጅቱን ወጪ በሚመለከት ለመንግሥት 51 ሚሊዮን ብር በጀት አቅርቦ፣ 35 ሚሊዮን ብር የተፈቀደለት መሆኑ ታውቋል፡፡ ቀሪው 16 ሚሊዮን ብሩን በሚመለከት ከስፖንሰሮችና መሰል ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ለመሙላት ዕቅድ ስለመያዙ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡ 28 ተጫዋቾችን ጨምሮ በአጠቃላይ 40 አባላት የያዘው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን፣ ከምድቡ ውጪ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ቢያንስ ሁለት አሊያም ሦስት የአቋም መፈተሻ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ዋና አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡ አዘጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶና ኬቨርዴ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ቡድን እንደ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሆነ፣ ቡድኑ የምድብ ጨዋታውን ማለፍ የመጀመርያ ዕቅዱ ነው፡፡ ከዝግጅቱ ጋር ተያይዞ ከዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባልተለመደ መልኩ ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚያደርገውን የሁለት ሳምንት ዝግጅት በካሜሩን እንዲያደርግ ወስኗል፡፡ ጠቀሜታውን በተመለከተ የሚሉት ይኖርዎታል?

አሠልጣኝ ውበቱ፡- የፌዴሬሽኑ ውሳኔ አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡ አንደኛውና መሠረታዊ ብለን ማንሳት የሚገባን ቡድናችን ከካሜሩን አየር ፀባይ ጋር የሚለማመድበት በቂ ጊዜ እንዲኖረው ያደርጋል፣ የወዳጅነት ጨዋታ ለማግኘት ያመቻቻል፣ ሌላው በቦታው ሆኖ ዝግጅት ማድረግና ሐሳብ በመሰብሰብ አንድ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት የሚኖረው ጠቀሜታ በራሱ ትልቅ ሲሆን፣ ሌላው ውድድሩ ሲቃረብ የሚኖረውን መተረማመስ ይቀንሳል፣ በአጠቃላይ በብዙ መልኩ ጥቅሙ የጎላ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ጨዋታ የምታደርገው ከኬቬርዴ ጋር ነው፡፡ ምድቡ ጠንካራ ከመሆኑ አኳያ ኬቬርዴንን በመክፈቻው ጨዋታ በማግኘታችሁ ምን ማለት ይቻላል?

አሠልጣኝ ውበቱ፡- እንደተባለው የኢትዮጵያ ምድብ የሞት ምድብ ተብለው ከተቀመጡት አንደኛው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኬቬርዴም ሆነ ሌሎቹ ቢገጥሙን ለእኛ ልዩነት የለውም፡፡ ዝግጅታችንም ለኬቨርዴና ለካሜሩን አሊያም ለቡርኪናፋሶ የሚል አይደለም፡፡ እንደተባለው ምድባችን በአብዛኛው ጉልበት ላይ መሠረት አድርገው የሚጫወቱ ቡድኖች እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ለዚያም አስፈላጊውን ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያን ጨምሮ ያደርግናቸው ጨዋታዎች ብዙዎቹ ምን ዓይነት የአጨዋወት ሥልት መከተል እንደሚገባን በሚገባ ተምረንበታል፡፡ ቀደም ብለን መጓዛችን እነዚህንና መሰል ክፍተቶቻችን ለማረም እንጠቀምበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ያለፉ ጨዋታዎችን ሙሉ ቪዲዮ ለሁሉም ተጫዋቾቻችን እንዲመለከቱት አድርገናል፡፡ ምክንያቱም የዓለም ዋንጫ ማጣሪያን ጨምሮ የተደረጉ ሁሉንም ጨዋታዎች ተጫዋቾችን በግላቸው እንዲመለከቱ ሙሉ ቪዲዮው እንዲደርሳቸው በማድረግ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲገመግሙ፣ እርስ በርሳቸው ሐሳብ እንዲለዋወጡ በማድረግ ክፍተቶቻቸውን መልሰው መላልሰው እንዲመለከቱና ስለሚሻሻሉበት እንዲያስቡ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ ይህ ዝም ተብሎ ሳይሆን ተጫዋቾቻችን ከተጋጣሚዎቻቸው እንቅስቃሴ በመነሳት ራሳቸውን በሥነ ልቦናው ረገድም ዝግጁ እንዲያደርጉ ለማድረግም ጭምር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚደመጡ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ከቅሬታው ጋር ተያይዞ የሚሉት ይኖርዎታል?

አሠልጣኝ ውበቱ፡- ምርጫው ተጫዋቾች በውድድር ዓመቱ የነበራቸውን ወቅታዊ ብቃት መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ሁሉም ሰው እኔ ባሰብኩት መንገድና አስተሳሰብ መሄድ ይኖርባቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ቅሬታ የሚገባቸው ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ 28 ተጫዋቾችን ምርጫ ስናደርግ ዓመቱን ሙሉ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የተጓዙትን ጨምሮ እንቅስቃሴያቸውን  ለመለካት ደረታቸው ላይ ዘመናዊ የእንቅስቃሴ መለኪያ (ጂፒኤስ) ጭምር በመግጠም ከነበራቸው ወቅታዊ ብቃት በመነሳት ነው፡፡ እንደተባለው በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ያልተካተቱ ልጆች እንደሚኖሩ አልክድም፡፡ የዕይታ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርነው ቡድኑ ዝግጅት የሚያደርገው ውድድሩ በሚከናወንበት አገርና ከተማ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት እርሶዎን ጨምሮ ቴክኒካል ቡድን ወደ ሥፍራው አምርቶ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን የመገምገም ዕድል ነበር?

አሠልጣኝ ውበቱ፡- ራሱን የቻለ የጥናት ቡድን የሄደበትና ግምገማ ያደረገበት አጋጣሚ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ወደ ሥፍራው በማቅናት ከካሜሩን አቻቸው ጋር በጉዳዩ በሚገባው ልክ ማለትም ከአየር ፀባይ አኳያ፣ ከሆቴልና ለዝግጅት ከሚሆኑ የተመቻቹ ሜዳዎችን ጭምር ምንም ዓይነት ችግር እንደማይገጥመን መግባባት ላይ ስለመድረሳቸው ግን መረጃው አለኝ፣ አውቃለሁም፡፡

ሪፖርተር፡- ከወዳጅነት ጨዋታ ጋር ተያይዞ አብዛኛዎቹ የወዳጅነት ጨዋታዎች እንደሚገኙ የሚነገረው ዋናው ውድድሩ ሊጀመር ከሳምንት ያነሰ ጊዜ ሲቀር እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ የመጀመርያ ጨዋታዋን የምታደርገው ጥር 9 ከመሆኑ አኳያ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ ከተጫዋቾች ጉዳት አኳያ የሚኖረው ተፅዕኖ ምን ያህል ታስቦበታል?

አሠልጣኝ ውበቱ፡- እንደተባለው የወዳጅነት ጨዋታዎቹ ሊገኙ የሚችሉት ቡድኖች ለውድድር ወደ ካሜሩን በሚገቡበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ችግር ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ካሜሩን በምታስተናደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከእኛ ውጪ 23 ብሔራዊ ቡድኖች ይኖራሉ፡፡ የወዳጅነት ጨዋታዎችን የምናደርገው ከእኛ ምድብ ውጪ ካሉ ቡድኖች ጋር እንደመሆኑ ሥጋቶቹ የሚጠበቁ ናቸው፡፡ በተቻለ መጠን ችግሮቹ እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ጥንቃቄ ማድረግ ካልሆነ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች የስብስብዎ አካል እንዲሆኑ ተጠይቀው አልቀበልም ማለትዎ ይነገራል፡፡ ምክንያት ይኖርዎታል?

አሠልጣኝ ውበቱ፡- አቅም ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች አልቀበልም የሚል ነገር ተናግሬ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ከትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች ጋር ተያይዞ የእርሶዎ አስተያየትም ሆነ ሐሳብ ምንድነው? ደግሞስ ጥያቄው አልቀረበልኝም እያሉ ነው? ምክንያቱም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እነዚህንና መሰል ሥራዎችን እንዲሠራ መልማይ ባለሙያ እንዳለው የሚታወቅ ነው፡፡

አሠልጣኝ ውበቱ፡- ፌዴሬሽኑ መልማይ ባለሙያ አለው የለውም? የሚለው በራሱ ጥርት ብሎ እንዲቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ እንደተባለው መልማይ ተብሎ በፌዴሬሽኑ ዕውቅና የተሰጠው ዴቪድ በሻህ የተባለ ሰው በዚህ ረገድ ከፌዴሬሽኑ ጋር ለመሥራት ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ጥያቄ ሲያርብ የቆየ መሆኑ፣ ግለሰቡ ይዞት የመጣው ሐሳብ ጥሩ እንደሆነ በማመን፣ እኔ ራሴ ፌዴሬሽኑ እንዲቀበለውና እንዲሠራ ፈቃድ የተሰጠው ነው፡፡ እስከዚህ ድረስ ፈቃደኛ የሆነ አሠልጣኝ ታዲያ እንዴት ነው በውጭ የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎች ሲመጡለት አልፈልግም ብሏል ተብሎ ድምዳሜ ላይ የሚደረሰው? እውነታው ምንድነው ለተባለው፣ እንደተባለው ዴቪድ በሻህ ባለፈው ሳምንት ማለት ወደ አራት የሚጠጉ በውጭ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ ሳይሆን፣ አጫጭር እንቅስቃሴዎችን የሚያሳይ ቪዲዮ አቅርቦልኛል፡፡ በመሠረቱ ቪዲዮዎቹ መቅረብ የነበረባቸው ለእኔ ሳይሆን ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ዴቪድ በሻህ ያቀረበልኝን ቪዲዮ ከተመለከትኩ በኋላ ተጫዋቾቹ ሙሉ ጨዋታ ያደረጉበት ቪዲዮ በዋናነትም በጀርመን ሦስተኛ ሊግ ላይ የሚጫወት ቪዲዮ የሌለውና በረኛ ተብሎ የቀረበው ቪዲዮ ሙሉ ጨዋታ ያደረጉበትን እንቅስቃሴ እንደገና ላክልኝ ባልኩት ጊዜ፣ እንዴት እንዲህ ትላለህ በሚል ተቆጥቶ ግንኙነቱን አቋረጠ፡፡ ይህንኑ አግባብ ባልሆነ መንገድ ማኅበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን ላይ ሲቀርብ ነው የሰማሁት፡፡ የሚገርመው ግለሰቡ ሥራውን ሕጋዊ ሆኖ ከፌዴሬሽኑ ጋር እንዲሠራ ከፍተኛ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ ሥራውንም መሥራት የጀመረው ባለፈው መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡ ከእኔ ጋር በውጭ ስለሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች ጉዳይ ማውራት የጀመርነው ደግሞ ከአንድ ወር በፊት ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ተዓማኒነት ያለው ቪዲዮ እንዲልክልኝ ከመጠየቅ ውጪ ከጊዜው መቃረብ ጋር ተያይዞ ሊኖር የሚችለውን ችግር ምክንያት አላደረኩም፡፡ አጫጭር ቪዲዮዎችን ተመልክቶ ውሳኔ ላይ መድረስ የከፋ ጉዳት ስለሚኖረው፣ በተቻለ መጠን የሁለቱን ተጫዋቾች ሙሉ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቪዲዮ እንዲልክ ነው የጠየኩት፡፡ ይህንን መጠየቅ ወንጀሉ የቱ ጋር ነው? በመጨረሻም ውድድሩ ከቀረው ጊዜ አንፃር ተመልክተን ልጆቹን የቡድናችን አካል ማድረግ እንደማይቻል ተስማምተን ሳናካትታቸው ቀርተናል፡፡ ለቡድኔ  ውጤት የሚመጥን ተጫዋች ቢመጣና ውጤት ቢመዘገብ የመጀመርያው ተመሥጋኝ እኔ ነኝ፡፡ ከዚህ አኳያ ከተጫዋቾቹ ጋር ተያይዞ የሚቀርበው ትችት ውኃ የማይቋጥር ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡

ሪፖርተር፡- ከትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት መፍትሔውና አሠራሩ ምን ሊሆን ይገባል ብለው ያምናሉ?

አሠልጣኝ ውበቱ፡- አንዱና መሠረታዊው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከዜግነት ጋር ተያይዞ የምትከተለው የሕግ አግብባ እንዴት ነው የሚለውን ተመልክቶ ጥርት ያለውን አሠራር መስቀመጥ ይገባል፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ ዜግነትን በተመለከተ ጥምር ዜግነት እንደማትፈቅድ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን በአግባቡ ማየትና መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ብሔራዊ ቡድኑን ጨምሮ ክለቦችን መልማይ ባለሙያ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ዴቪድ በሻህ ጥሩ ነገር ጀምሯል፡፡ ይህ ግን አበው ‹‹ሠርገኛ መጣ…›› እንደሚባለው ሳይሆን፣ ጊዜ ተሰጥቶት ቢሠራበት በእግር ኳሱ የተሻለ ነገር ማምጣት እንደሚቻል አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከካሜሩን ምን እንጠብቅ?

አሠልጣኝ ውበቱ፡- ቀደም ሲል እንደተገለጸው ምድባችን ከባድ ነው፡፡ ያም ሆኖ ምድቡ የቱንም ያህል ከባድ ቢሆንም ዕቅዳችን ከምድባችን ማለፍ ነው፡፡ እንደ ቡድን ለዚያ የሚሆን አቅሙም ሆነ ዝግጁነቱ አለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...