Wednesday, February 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ከሚያስቀምጡት መጠባበቂያ ገንዘብ ላይ ብድር መስጠት ጀመሩ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚያስቀምጡት መጠባበቂያ ገንዘብ ላይ ለቡና ላኪዎችና አቅራቢዎች ብድር እንዲሰጡ በብሔራዊ ባንክ የተላለፈው መመርያ ከታኅሳስ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ መተግበር ጀመረ፡፡

በኢንዱስትሪው ውስጥ እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ከብሔራዊ ባንክ በተላለፈው መመርያ መሠረት፣ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ከሚያስቀምጡት የአሥር በመቶ መጠባበቂያ ገንዘብ ላይ ሁለት በመቶውን ወጪ በማድረግ ለዚሁ ዘርፍ ብድር እንደተጠቀሙበት አስታውቋል፡፡

በተለይ የቡና የወጪ ንግድ እንዳይስተጓጎል ባንኮችም የጥሬ ገንዘብ  ችግር እንዳይገጥማቸው ታሳቢ ተደርጎ ተግባራዊ እንዲሆን በተላለፈው መመርያ መሠረት፣ ለቡና ላኪዎችና አቅራቢዎች ብድር ማቅረብ ይችላሉ፡፡

ባንኮቹ ለነዚህ ዘርፎች የሚሰጡት ብድር እያንዳንዱ ባንክ ባለው መጠባበቂያ ገንዘብ ልክ መጠን የሚወሰን ነው፡፡ የተሰጠው ብድር የመመለሻ ጊዜ ገደብ የተቀመጠለት ሲሆን፣ ባንኮቹ ለነዚህ ዘርፎች የሰጡትን ብድር እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. መልሰው ወደ ብሔራዊ ባንክ  ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህ በብሔራዊ ባንክ ሰሞናዊ ውሳኔ ላይ ካነጋገርናቸው መካከል አንዱ የሆኑት የኦሮሚያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን፣ ውሳኔው ኃላፊነት የተሞላበትና ወቅቱን የጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ካለንበት አገራዊ ችግር አኳያ የወጪ ንግዱን ማሳደግ የግድ ነው ያሉት አቶ ተፈሪ፣ የወጪ ንግድ ደግሞ ቡና ላይ ማረፉን፣ አገራችን የተሻለ የንግድ ሚዛን እንዲኖራት ለማድረግ እንዲሁም ወቅቱ ቡና የሚገዛበትና ለውጭ ገበያ የሚዘጋጅበት እንደመሆኑ መጠን ይህንን ሊያግዝ የሚችል ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እየተወሰደ ካለው ዕርምጃ አኳያ ለዘርፉ ይሰጥ የነበረው የብድር አቅርቦት በጣም የመነመነ በመሆኑ በዚህ መልክ ብድር መመቻቸቱ ተገቢ መሆኑን የሚያምኑት አቶ ተፈሪ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ባንኮች ሊገጥማቸው የሚችለውን የገንዘብ እጥረት ለመሙላትም ይረዳል ብለዋል፡፡

በተለይ በባንኮች ላይ የተጨመረው የመጠባበቂያ መጠን መጨመር፣ በአጠቃላይ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር በሒሳብ አከፋፈት ላይ የተወሰዱ የጥንቃቄ ዕርምጃዎች ባንኮች በቂ የብድር አቅርቦት እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡

በውሳኔው መሠረት ባንኮች ካላቸው መጠበቂያ ገንዘብ ለቡና ላኪዎችና አቅራቢዎች መልቀቅ መጀመራቸውንም ከአቶ ተፈሪ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የሰሞኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕርምጃ አወንታዊ ሲሆን፣ ይህም ዘንድሮ ብራዚል በውርጭ ምክንያት የቡና ምርቷ ጥሩ ባለመሆኑ ለኢትዮጵያ ቡና ጥሩ ዕድል የሚከፍትና ተወዳዳሪ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይህም እስከ መጋቢት ወር ድረስ እንደሚቀጥል የሚጠበቅ በመሆኑ ከዚህ ምርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሰሞኑ ውሳኔ አግባብ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

ውሳኔው፣ ኢኮኖሚውን በማነቃቃቱ ረገድም ትልቅ ጥቅም አለው ያሉት አቶ ተፈሪ፣ ለዘርፉ የሚሰጠው ብድር ለአገር፣ ለባንክ ደንበኞች፣ ለባንኮች፣ ለገበሬውና በአጠቃላይ በቡና ግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላትን በሙሉ የሚጠቅም መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ለአቅራቢው ብድር ቀርቦ ቡናው የማይሰበሰብ ከሆነ ከገበሬው ጀምሮ በአገር ደረጃ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበርም የጠቆሙት አቶ ተፈሪ፣ ይህንን ብድር በጥንቃቄ በመስጠትና በመበደር የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

 ብዙ ጊዜ  ለቡና የሚሰጥ ብድር አመላለስ ላይ ችግር የሚገጥመው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዲህ ባለው መንገድ የተሰጠ ብድር በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ላይመለስ ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው ወገኖች ቢኖሩም፣ ወቅቱ ከቡና ሥራ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ባንኮች በገንዘብ እጥረት ለዘርፉ የሚሰጡት ገንዘብ ካጠራቸው እንኳን በዚህ እንዲሸፍኑ መደረጉ አግባብ ነው፡፡

እንደ አንዳንድ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ፣ ለቡና ተብሎ የተሰጠው ብድር ለሌላ ዓላማ እንዳይውል ለማድረግ ጥንቃቄ የሚደረግ ሲሆን፣ በተለይ ለላኪዎች ብድሩ ሲፈቀድ  የቡና ንግድ ፈቃድ ያላቸው መሆኑ እንዲሁም ሌላ በተለይ ቡና ላኪዎቹ ቡና ለመላክ የተዋዋሉት ኮንትራት እየታየ ብድሩን በመልቀቅ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡

ብዙ ጊዜ ግን ለቡና እየተጠሰ ያለው ብድር ለተለያዩ አገልግሎቶች ሊውል ስለሚችል አሁን አመላለሱ ላይ ችግር እንዳይገጥም ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቡና አብቃዮች አቅራቢዎችና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት  ሁሴን አሞቦ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ቡና መሰብሰብ ያልተቻለ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ጉዳት ሊከሰት ችሏል፡፡ ይህንን ለማስቀረት የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ወሳኝ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በአፋጣኝ ባንኮች ብድሩን ሊለቁ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡትን የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን ማሳደጉ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ለነዚህ ዘርፎች የሚሰጠው ብድርም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ካላቸው የአሥር በመቶ መጠባበቂያ ሁለት በመቶ ያህሉን ነው፡፡

ባንኮች በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ባንክ አዲሱ መመርያ መሠረት ከአምስት ወደ አሥር ያደገውን የመጠባበቂያ ገንዘብ መጠን ሙሉ በሙሉ አስገብተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች