Monday, December 4, 2023

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ውሳኔ አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአውሮፓ ኅብረት ጠያቂነት ዓርብ ታኅሳስ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከናወነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ፣ ኢትዮጵያን ያሳዘነና ያስቆጣ ‹‹በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለ አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት›› የሚል ርዕስ የተሰጠው የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ለተመድ አካል ያቀረበው ጥያቄ በ17 የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላትና በ35 የምክር ቤቱ አባል ባልሆኑ አገሮች ተፈርሟል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ጥያቄውን ማቅረቡን ተከትሎ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ እንደማትቀበለው ያስታወቀች ሲሆን፣ መንግሥትና የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ስብሰባው እንዲከናወን ከፈረሙ ጠያቂዎች መካከል አንድም አፍሪካዊ አገር አለመኖሩን በማንሳት ሒደቱን ተችተዋል፡፡ ይሁንና በመንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በታኅሳስ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫው፣ ‹‹ቢዘገይም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የትግራይ ጉዳይ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ አንድምታ ያለው መሆኑን ዕውቅና በመስጠት ልክ ሠርቷል፤›› ሲል አሞካሽቶታል፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ኅብረት ጥያቄውን ባቀረበ በማግሥቱ ታኅሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በተጠራው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ አባላቱ ለስብሰባው መካሄድ ድጋፋቸውን እንዲነፍጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

‹‹በሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ውስጥ ያሉ አንዳንዶች በኢትዮጵያ መንግሥት እየተሠራ ላለው ሥራና ለጥረቶቹ ሁሉ ፍፁም ቸልተኝነት በማሳየት፣ ፖለቲካዊ ተነሳሽነት ያለውን ዓላማ ለማሳካት ሲባል የሆነ ዓይነት ውጤት ለማስገኘት በማለም ልዩ ስብሰባ ለመጥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፤›› ሲል ያወሳል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና የዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም፣ መንግሥት የውሳኔ ሐሳቡን የማፅደቅ መላ ሒደቱን ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ያደረገው ፖለቲካዊ መነሻ ስላለው መሆኑን፣ በቅርቡ የተደረገ ምርመራ ሳለ ተመሳሳይ ጊዜን የሚሸፍን አዲስ ምርመራን መደገፍ ስሜት ሊሰጥ የማይችልና አንዳንዶች የጠበቁትን ውጤት ባለማግኘታቸው የተነሳ ያስጀመሩት ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

‹‹መንግሥት ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. የወጣውን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና (ኢሰመኮ) የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በጥምረት የተደረገው ምርመራ ሪፖርት ምክረ ሐሳቦችን ተቀብሎ ዕርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት አዲስ ምርመራ ለማድረግ መነሳት፣ ዓለም አቀፍ ልምዶችን መበዝበዝና የተደረተ ተግባር በማከናወን ሀብት ማባከን ነው፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡

በሌላ ወገን በኢሰመኮና በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ያደረጉትን የምርመራ ሥራ ገለልተኝነትና ግልፅነት በማድነቅ፣ አዲስ የሚከናወነውን ምርመራ በተመለከተ የተላለፈው ምክረ ሐሳብ ለአንድ ዓመት የሚዘልቀው ምርመራ በጥምር መርማሪዎቹ የተገኙ ግኝቶች ላይ ተጨማሪ እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ በዚህም መሠረት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልጋል በማለት፣ የጋራ ምርመራው ያስቀመጠውን ምክረ ሐሳብ ተከትሎ የሚከናወን ነው ይላል፡፡

ኢሰመኮና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በጋራ ባወጡት የምርመራ ሪፖርት የሰላማዊ ዜጎችን የጥቃት ዒላማ መሆን፣ አስገድዶ መደፈር፣ የዜጎች መፈናቀል፣ የሕፃናት ለጉዳት መጋለጥ፣ ብሎም ሌሎች በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በትግራይ ክልል ጦርነት መፈጸማቸውን ለመመርመር ስምምነት አድርገው በኋላም ከምርመራው ባወጡት ሪፖርት ሁሉም በጦርነቱ የተሳተፉ ወገኖች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ፈጽመዋል በማለት አረጋግጠዋል፡፡ ሪፖርቱ አክሎም ግኝቱ ተጨማሪ ግምገማና ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሰብዓዊ መብት ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ አስተማማኝ የሆነ የመረጃ ግብዓት መሆን እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

ይሁንና ሕወሓት ሪፖርቱ ከመውጣቱ አስቀድሞ የምርመራውን ሒደትና ውጤት እንደማይቀበል ያስታወቀ ሲሆን፣ ኢሰመኮ በምርመራው መሳተፉ ተዓማኒ ምርመራ እንዳይሆን አድርጎታል በማለትና ምርመራው ሁሉንም የትግራይ አካባቢዎች የሸፈነ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል ማለቱ ይታወሳል፡፡

ኢሰመኮ ለምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ነዣት ከሃን ኅዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈውና ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽለት ግልባጭ ባደረገው ደብዳቤ፣ ከተባሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ጋር ጋራ ያደረገው ምርመራ ምክረ ሐሳቦች ይተገበሩ ዘንድ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአሁን ቀደም የተናገሩ አካላት በድጋሚ የተጠቂነትና ከጥቃት ተራፊነት ውይይት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል በማለት፣ አሁን መሆን የነበረበትን የመልሶ ማቋቋምና ካሳ እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም አጥፊዎችን ወደ ተጠያቂነት ማምጣት ነው ሲል ተከራክሯል፡፡

ሦስት ሚሊዮን ዶላር የፀደቀለት የምክር ቤቱ ፕሮጀክት ሦስት የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች የሚኖሩት ሲሆን፣ በምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የሚሾሙ ይሆናሉ፡፡ መቀመጫቸውም ኡጋንዳ ኢንቴቤ ይሆናል፡፡

መጀመሪያ የውሳኔ ሐሳቡ ከመፅደቁ አስቀድሞ የተነሱ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሥጋቶች መጨረሻ ላይ በፀደቀው የውሳኔ ሐሳብ መሻሻላቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት የኢሰመኮ ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ፣ የውሳኔ ሐሳቡን ተከትሎ የሚመሠረተው የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ገለልተኛ ኮሚሽን ተጨማሪ እንጂ ካሁን ቀደም በጥምረት ከተመድ ጋር የተሠራውን ሥራ የሚተካ አይደለም ብለዋል፡፡

ሆኖም ተመሳሳይ ሥራ መሥራት የሚችል ብቁ አገራዊ ተቋም ሳለ ይኼንን መሰል ምርመራ የማድረግን ጥቅም ያጠይቃሉ፡፡

‹‹የጋራ ምርመራው፣ ሪፖርቱ፣ እንዲሁም ምክረ ሐሳቦቹ ከትግራይ ክልል ጦርነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደ ተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት አነስተኛ ድጋፍ ተደርጎለት መርመራ ሊያከናውን የሚችል ገለልተኛ፣ ብቁና ችሎታ ያለው አገር በቀል ተቋም እንዳለ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህም አገር በቀሉን የሰብዓዊ መብቶች ተቋም አቅም መገንባት መቻል እንጂ፣ ሌላ የጎንዮሽ ተቋም መሥርቶ ምርመራ ማድረግ ስሜት የሚሰጥ አይደለም፤›› ሲሉ የሚከራከሩት ራኬብ፣ ይኼ ዘላቂ የአገር በቀል ተቋማትን አቅም ከመገንባት ጋር የሚሄድ አይደለም በማለት፣ ‹‹በኢሰመኮ እምነት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ትኩረት ሊሆን ይገባ የነበረው የጋራ ምርመራ ምክረ ሐሳቦች በሁሉም ወገኖች እንዲተገበሩ ማገዝ፣ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥና ለተጎጂዎች ካሳ ማስገኘት፣ ኢሰመኮንና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤትን ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርጉና በጥምር ምርመራው ያልተሸፈኑ ሥፍራዎችን እንዲሸፍኑ ማገዝ፣ እንዲሁም ሕወሓትና ሌሎች በግጭቱ የተሳተፉ አካላት ለኢሰመኮና ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ሥራዎች ዕውቅና ሰጥተው እንዲተባበሩ ማድረግ ነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ሆኖም የውሳኔ ሐሳቡ ረቂቅ ሲፀድቅ የተደረገበት ማሻሻያ፣ እንዲሁም የሚሾሙት የገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ባሙያዎች የጥምር ምርመራውን ሊያግዙ ይችሉ ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡ ይሁንና የዚህ የገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባሙያዎች የሥራ መዘርዝር የሚወስነው ይሆናል ባይ ናቸው፡፡

‹‹ኢሰመኮ ጥቅምት 2014 ድረስ ሲከናወን የነበረው ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ግጭቱ ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመስፋፋቱ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመመርመር ላይ ስለሆነ፣ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የፈቀደው ምርመራ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ይሁን አይሁን ግልጽ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

በመቱ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ዕጩ ሙሉቀን ካሳሁን፣ እንዲህ ያለው ምርመራ የሚያወጣው ማናቸውም ሪፖርት ውጤት የሚወሰነው በግኝቶቹ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፍላጎቶች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ፣ እንዲሁም በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የፖለቲካ ፍላጎቶች ላይ ይመሠረታል ይላሉ፡፡ ነገር ግን ታሪካዊ ዳራ እንደሚያሳየው ይኼንን ተከትሎ የሚመጣ ተመሳሳይ አሠራር እንደሌለ፣ በምዕራቡ ዓለምና በተቀረው የዓለም ክፍል መካከል ያለው የኃይል አሠላለፍ የምርመራው ውጤት ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

እንዲህ ያሉ ሪፖርቶች ሊያገኙ የሚችሉት በአሰቃቂ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ የሚኖሩ ግኝቶች፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ዓይነቶችና የጥሰት ደረጃ ይሆኑና የሚመለከታቸውን አገሮች ለመከላከል አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስዱ ሊጠይቁ ይችላሉ የሚሉት ካሳሁን፣ የሚመለከተው አገር በጥሰቶቹ ተሳትፎ አለው ከተባለና አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ ካልቻለ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ እንዲጥል፣ አልያም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲፈቅድ ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ደግሞ ምርመራው የአገሪቱን መልካም ስም ከማጉደፍ አልፎ እንደ ጦር መሣሪያ ዕቀባ፣ የጉዞ ክልከላ፣ የነዳጅና ነዳጅ ነክ ያልሆኑ ቁሶች ገቢ ንግድ ክልከላ፣ የገንዘብ ዝውውር ገደብ፣ ጠቅላላ የንግድና መሠረታዊ ያልሆኑና የቅንጡ ሸቀጦች ንግድ ገደብ፣ እንዲሁም የዲፕሎማሲያዊ ገደብ ሊያስከትል ይችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚህ በተጨማሪም የዳርፉርን ጉዳይ የመረመረው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ላይ እንዳደረገው፣ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ግለሰባዊ ተጠያቂነቶች እንዲኖሩ ሊያደርግም ይችላል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ለምርመራው ምንም ትብብር እንደማያደርግ ያስታወቀ መሆኑን ተከትሎ፣ ለእንዲህ ያለ ምርመራ የአገሮች ትብብር ወሳኝ ቢሆንም ቅሉ፣ ምርመራው ከማከናወን ግን የሚያስቆም ውሳኔ ላይሆን እንደሚችል ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በሶሪያ እ.ኤ.አ. በ2011፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑክ በጋዛ ግጭት እ.ኤ.አ. በ2009 እና በተለያዩ ተከታታይ ኮሚቴዎች እንደታየው እነዚህ አካላት የጎረቤት አገሮችን በመጎብኘት በሚመረመሩ ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ መረጃ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት፣ ተጠቂዎችና ምስክሮች ከአገር ውጭ ምስክርነት እንዲሰጡ ለማድረግ፣ ይፋዊ መግለጫዎችንና በማንም ሊገኙ የሚችሉ መረጃዎች ላይ ሊመረኮዙ፣ እንዲሁም የመንግሥትን አቋም ሊያፀባርቁ ከሚችሉ አካላት ጋር መደበኛ ያልሆነ ግንኙነት ለመፍጠር ይጥራሉ ሲሉ ሊጠቀሙ የሚችሏቸውን የምርመራ መንገዶች ያስረዳሉ፡፡

‹‹ወደ እኛ ስንመለስ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ መረጃዎች በሱዳንና በኬንያ ከሚገኙ ስደተኞች ይሰበሰባሉ፡፡ ሆኖም ከኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ትብብር አለማግኘት በሽግግር ጊዜ ፍትሕ ላይ ድጋፍ ለማድረግና ለመተግበር፣ ዕርቅና መሻርን ለማምጣት፣ እንዲሁም እንዳስፈላጊነቱ ምክረ ሐሳቦቹን ለመተግበርና ተጠያቂነትን ለማምጣት፣ ዕርቅና መሻርን ዕውን ለማድረግ የቴክኒክ ዕገዛ ማድረግ እንዳይችል ያደርጋል፤›› ይላሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የተመድ አካል የሆነው ምክር ቤት ምርመራውን ለማከናወን ሲወስን ትብብር መንፈጉ፣ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ሰላም እንዲያወርዱና በተጨማሪ የውሳኔ ሐሳቦች እንዲሳተፉ፣ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የምክር ቤቱን ጥያቄዎች ማሟላታቸውን የሚከታተል የክትትል መንገድ መቅረፅ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማበረታቻዎችን፣ ማስፈራሪያዎችንና ማዕቀቦችን ማኖር፣ በተጨማሪም እንደ መጨረሻ አማራጭ የሰላም ማስከበር ኃይል እንዲያሰማራ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት እ.ኤ.አ. በ2015 ያወጣው እንዲህ ያለውን የምርመራ አሠራር የሚገዛ “Commissions of Inquiry and Fact-finding Missions on International Human Rights and Humanitarian Law: Guidance and Practice” የተባለ ሰነድ እንዲህ ያሉ ችግሮች መሰል ምርመራዎችን በማድረግ ረገድ ፈተና እንደሚሆን በማመን፣ ካሳሁን ከላይ የዘረዘሯቸውን አማራጭ የምርመራ መንገዶች በተለያየ መንገድ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ያስረሉል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -