የሰሜን ሸዋ ዞን በ22 ወረዳዎችና አምስት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ነው፡፡ 436 የገጠርና የከተማ ቀበሌዎችም አሉት፡፡ ዞኑ 1,500 ሜትር እስከ 4,012 ሜትር ከመሬት ወለል በላይም ይገኛል˸˸
በስተደቡብና ምዕራብ ከኦሮሚያ፣ በስተሰሜን ከደብብ ወሎ ዞን፣ በስተሰሜን ምሥራቅ ከአማራ ክልል ኦሮሚያ ዞን እንዲሁም በስተምሥራቅ ከአፋር ክልል ጋር የሚዋሰነው ዞኑ፣ ከ15,954.92 ኪሎ ሜትር በላይ የቆዳ ስፋት እንዳለውና ከክልሉ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት መካከል 11 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን በመመዝገብ ሥራ ላይ የተሳተፉት የሥነ ሕንፃ ባለሙያ አቶ ሚኪያስ ቴዎድሮስ ከዓመት በፊት ያጠናቀሩት መረጃ ያሳያል፡፡
35.9 በመቶ ሜዳማ፣ 26.11 በመቶ ከፍታ ቦታዎች፣ 25.9 በመቶ ተራሮች፣ 11.7 በመቶ ሸለቆዎች፣ 0.3 በመቶ ረግረጋማና 0.02 በመቶ በውኃ የተሸፈኑ ሥፍራዎችም በዞኑ ይገኛሉ፡፡
የዞኑ አየር ንብረት 33.71 በመቶ ቆላ፣ 35 በመቶ ወይናደጋ፣ 30.65 በመቶ ደጋ እንዲሁም 0.6 በመቶ ውርጭ ሲሆን፣ ትልቁ ተራራም አብየ ሜዳ ነው፡፡
ሥነ ምኅዳሩ በተለይም ደጋውና የውርጩ አየር ንብረት የአፍሮ አልፓይን ባህሪ የተላበሰ በመሆኑ ከአውሮፓ ለሚመጡ ቱሪስቶች እጅግ ምቹ እንደሚያደርገው የአቶ ሚኪያስ መረጃ ያሳያል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የተቆረቆረችውና ስያሜዋን ያገኘችው ደግሞ ከ566 ዓመት በፊት በ1446 ዓ.ም. በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1426 እስከ 1460) ነበር፡፡
ዞኑ በመካከለኛው ክፍለ ዘመንም ሆነ በዘመናዊቷ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው የነገሥታት፣ መኳንንቶች፣ ጀግኖች አርበኞች፣ የጥበብ ሰዎችና ሌሎችም መፍለቂያ ነበር፡፡
አጼ ዘርዓ ያዕቆብ፣ አፄ ሕዝብናኝ፣ መርዕድ አዝማች አመሐ የሱስ፣ መርዕድ አዝማች ወሰን ሰገድ፣ ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ፣ አፄ ምንሊክ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ፣ ሜትር አርቲስት አፍወርቅ ተክሌና ሌሎችም ከዚሁ ሥፍራ እንደተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የሸዋ ነገሥታት መቀመጫ፣ የይፋት ሡልጣንና የጀጎል ግንብ ጽንሰ ሐሳብ ባለቤት የሆነው ይህ ዞን ብዙ ጥንታዊ ገዳማት፣ መስኪዶችና አድባራት ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህም የፃድቃኔ ማሪያም፣ ጎዜ መስጂድ፣ አቡነዜና ማርቆስ፣ ባልጪ አማኑኤል፣ ፍርኩታ ኪዳነ ምሕረትና አንኮበር ሚካኤል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በዞኑ የአርኪዎሎጂ ሥፍራዎች ከሆኑት ትክል ድንጋዮች ያሉባቸው ሥፍራዎች፣ የቀብር ቦታዎች፣ ጉሮች (ጥንታዊ ቀብር ቦታዎች)፣ መደበኛ ዓይነት ቀብር ሥፍራዎች፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች ተገንብተው የነበሩ የሕንፃ ቅሬቶች የቤተ መንግሥትና የመኖሪያ፣ የሃይማኖት ተቋማት ታሪካዊ ሥፍራዎች (አምባዎች) እና መካነ ቅርሶቻቸው፣ የከተማና ጥንታዊ መንደር ፍርስራሽ ሥፍራዎች፣ ገበያዎች (አልዩ አምባ)፣ የመከላከያ ምሽጎችና የጦር ካምፖች የሚገኙባቸው ቦታዎች፣ የመገልገያ መሣሪያዎች ማምረቻ (ሸክላ፣ ብረታ ብረትና ባሩድ…) ሥፍራዎች፣ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በንጉሥ ሳህለ ሥላሴ (1805 እስከ 1840) እንደተሠራ የሚነገርለት በአንኮበር ወረዳ የሚገኘው ጥንታዊ የንጉሥ ሳህለ ሥላሴ የባሩድ መውቀጫ ዞኑ በመካከለኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሥልጣኔዎችና የእጅ ጥበብ ማዕከል መሆኑን የሚያመላክት ነው ይላሉ አቶ ኤርሚያስ፡፡
እንደ አቶ ኤርሚያስ፣ በዞኑ የተለያዩ ፓሊዮንቶሎጂ ሥፍራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም የጀማ ወንዝ ሸለቆ የፓሊዮንቶሎጅ ሥፍራ፣ በመርሐ ቤቴ ወረዳ ውስጥ የተገኘ የጁራሲክ ዘመን የዳይኖሰር ጥርስ እንዲሁም በሙሽ ወንዝ ሸለቆ ባሶና ወራና ወረዳ የፓሊዮንቶሎጂ ሥፍራዎችን ዕድሜ ጠገብ የሆኑ የእንስሳትና የዕፅዋት ቅሬቶች ይገኙበታል፡፡
በኢትዮጵያ በተፈጥሮ መስህቦች ከታደሉ ሥፍራዎች አንዱ በሆነው ሰሜን ሸዋ የወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ደን በመንግሥት ጥበቃ የተደረገለት ሲሆን፣ ሥፍራውም በስምጥ ሸለቆ የተራራ ሰንሰለቶች አናት ላይ ተዘርግቶ የብዙ ብርቅዬ አዕዋፋትና እንስሳት መገኛ ነው፡፡
ሥፍራው የአንኮበር ሶረኔ ወፍ ብቸኛ መገኛና የመንዝ ጓሳ ማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ፣ የበርካታ አዕዋፋት፣ እንሰሳት እንዲሁም ዕፅዋት መገኛ ነው፡፡ በጥብቅ ሥፍራው ቀይ ቀበሮ፣ ወርቃማው ንስር ወፍ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እንዲሁም በርካታ የድመት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡
ሰሜን ሸዋ የተለያዩ ባህላዊ ትውፊቶች፣ የቤት አሠራር፣ አለባበስና ጌጣጌጥ፣ አመጋገብ እንዲሁም ባህላዊ ውዝዋዜዎችና የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ነው፡፡
በሸዋሮቢት ወረዳ የሚገኙት የአቡነ አረጋዊና እብዱ ፍል ውኃዎች፣ ሚዳ ወረሞ ወረዳ የሚገኘው የልብቃ የሱስ ፍል ውኃ፣ መንዝ ቀያ ወረዳ የሚገኘው የአመፀኛ ዋሻ፣ በጣሊያን ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያውያን አርበኞች ምሽግ የነበረ የመገዘዝ ተራራ፣ የቁንዲ ተራራ፣ የጀማና ከሰም ወንዝ ሸለቆዎች ይገኛሉ፡፡
በዞኑ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶና መስህቦች ቢኖሩም የውጭ አገር ቱሪስቶች ፍሰት እምብዛም ነው፡፡ የአገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰት የተሻለ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በሃይማኖታዊ ቱሪስት ፍሰት ከሌሎቹ ዘርፎች አንፃር የተሻለ ነው፡፡ በመሆኑም ሀብቱን ለውጭ ቱሪስቶች ማስተዋወቅና በስፋት የቱሪት መረጃ እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል፡፡