Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተደራሽነትን የሚፈታተነው የጤና ተቋማት ውድመት

ተደራሽነትን የሚፈታተነው የጤና ተቋማት ውድመት

ቀን:

ጥራቱን የጠበቀ፣ ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገ፣ የፆታ  እኩልነትን ያማከለና የመክፈል አቅምን ያገናዘበ የጤና አገልግሎት ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በዚህም በመላ ኢትዮጵያ የእናቶችና ሕፃናት ሞትን መቀነስ ተችሏል፡፡ የጤና አሰጣጡ፣ ተደራሽነቱና ሥርዓቱ ክፍተት ቢኖርበትም በርካታ መሻሻሎች ተመዝግበዋል፡፡ የሆስፒታሎች፣ የጤና ጣቢያዎች፣ የጤና ኬላዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችንም ማጠናከር ተችሏል፡፡ መንግሥት ከሚሠራው በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በጤናውም በመሰማራቱ አጋዥ ሆኗል፡፡ ተደራሽነቱን ለማሻሻልም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡

ነገር ግን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ የተባለው የሕወሓት ቡድን ዓምና በጀመረው ጦርነት የጤናው ዘርፍ እክል ገጥሞታል፡፡ በተለይ በመንግሥት የተናጠል ተኩስ ካደረገበት ከሰኔ 2013 ዓ.ም. በኋላ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የዘለቀው የሕወሓት ቡድን የሕዝብና የግል መገልገያ ተቋማትንና ንብረትን አውድሟል፡፡ የከፋ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት ደግሞ የጤና ዘርፉ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ሥራ ወደኋላ የሚጎትት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ለሕፃናት፣ ለእናቶችም ሆነ የጤና ተቋማት በወደሙባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሳንካ ነው፡፡ ሞትና መንገላታትንም የሚጨምር ነው፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ታኅሣሥ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ቡድኑ በአማራ ክልል ብቻ በስምንት ዞኖች በ82 ወረዳዎች በቆየባቸው ጊዜያት 2,350 የመንግሥት ጤና ድርጅቶችን፣ 466 የግል ክሊኒኮችንና 55 አምንቡላንሶችን እንዳወደመ አስታውቋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 40 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያዎችን፣ 1,850 ጤና ኬላዎችን፣ 4 የደም ባንኮችን፣ 1 የኦክሲጅን ማምረቻ ድርጅት፣ 1 ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ 1 የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅት፣ 466 የግል ጤና ድርጅቶችንና 55 አምቡላንሶች እንደሚገኙበትም ጠቁሟል፡፡

ይህም በተለይ በክልሉ ያለውን የጤና አጠባበቅና ተደሯሽነት አደጋ ላይ የሚጥል ሲሆን፣ ከዚህ ባለፈ የአካባቢው ነዋሪዎች ሕክምና ፍለጋ በሌሎች አካባቢዎች እንዲንገላቱና ለተጨማሪ ወጪ እንዲዳረጉ ያደርጋል፡፡

ይህንን ችግር ተጋግዞ ለመቀልበስ ጤና ሚኒስቴር ሁሉን አቀፍ ጥሪ ያደረገውም ባሳለፍነው ሳምንት ነው፡፡ ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ካደረሰው ሰብዓዊና ሞራላዊ ጥፋት በተጨማሪ  ህዝብ የሚገለገልባቸውን የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የህክምና ግብዓት ማከማቻ ተቋማትንና ሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት አውድሟል ያለው ሚኒስቴሩ፣ የሕክምና መሣሪያዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን ጭኖ በመውሰዱና በመዝረፉ በዘረፋ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡

በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ወድመት በተለይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎችና መሠረታዊና ድንገተኛ ሕክምና አግልግሎት አሰጣጥ ላይ በእጅጉ መስተጓጎል እንደፈጠረና ባልተጠቃለለው መረጃ መሠረትም ከ2700 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንደማይሰጡና አሁን ላይ በመንግሥት ተደራሽ ያልሆኑ አከባቢዎች ሲካተቱ ውድመት የደረሰባቸው ቁጥር እንደሚያሻቅብ ጠቁሟል፡፡

በጤና ተቋማቱ ላይ በተከሰተው መጠነ ሰፊ ወድመት ምክንያት በርካታ ዜጎች የጤና አግልግሎት የሚያገኙባቸው ተቋማት በከፊልና ሙሉ ለሙሉ መስተጓጎላቸውን በሌላም በኩል ግጭቱ በተከሰተባችው አካባቢዎች አቅራቢያ አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች እንዲጨናነቁና መደበኛ ከሆነው አቅማቸው በላይ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስገደዱንም አክሏል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለዚህ  አደጋ ምላሽ ለመስጠት እንዲያግዝ ሁሉን አቀፍ ከግጭት ጋር የተያያዘ ድንገተኛ አደጋ የጤና ምላሽ ሥርዓት አቋቁሞ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ፣ ይህን ፈታኝ የሆነ ተግዳሮት ለመግታት ዝርዝር ተግባር ያለው ስትራቴጂ በመንድፍ ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ፣ ከእነዚህም የመጀመሪያውና በአሁኑ ወቅት እየተሰራበት ያለው የተዘረፉ እና ውድመት የደረሰባቸውን ጤና ተቋማት ከተለያዩ በሃገር አቀፍ ደረጃ ካሉ  የመንግስት ተቋማት ጋር በማጣመር  ተቋማቱን መልሶ ማቋቋም እንደሆነ አሳውቋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር በግጭቱ አካባቢ ፈጣን ዳሰሳ በማካሄድ አሁን ላይ  የወደሙ የጤና  ተቋማትን መልሶ ለማቋቋምና ሥራ ለማስጀመር እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚስፈልግ እነደሆነ የዳሰሳው ግኝት ማመላከቱን ጠቅሶ፣ ይህንን የሀብት ማሰባብሰብና ድጋፍ ሥራን ለማስተባበር የጤና ሚኒስቴር የባለሙያ ቡድን ማቋቋሙን፣ በግለሰብም ሆነ በቡድን ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ሚኒስቴሩ አስፈላጊ መረጃና ትብብር ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡

የጤና ዘርፉ ከገጠመው የመውደም ፈተና በተጨማሪ እንደ አገር ተደራሽነቱም ክፍተት አለበት፡፡ የጤና ተደራሽነትን አስመልክቶ ማክሰኞ ታኅሣሥ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ላይ የተገኙት የሚኒስቴሩ አጋርነትና ትብብር ዳይሬክተር ፌቨን ግርማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት በሚጠይቅበት ጊዜ የፋይናንስ አቅርቦቱን በታማሚው መሸፈን አንዱ ክፍተት ነው፡፡ በመሆኑም ታማሚ ከኪሱ እንዳያወጣ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀይሰዋል፡፡ በተቀየሰው አቅጣጫ መሠረትም መንግሥት የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የማቋቋምና የማስፋፋት ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሽፋን ውስጥ የሚሳተፉት አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና የራሳቸውን ልዩ ልዩ ዓይነት ሥራ የሚያከናውኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን አመልክተው፣ ኅብረተሰቡም በዓመት አንድ ጊዜ በቤተሰብ ደረጃ የዓረቦን/ፕሪሚየም ክፍያ እየፈጸመ በማንኛውም የመንግሥት ጤና ተቋማት ያለምንም ተጨማሪ ወጪ የሚያስፈልገውን ሕክምና እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እጅግ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይህንኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ካቀረቡ፣ የሕክምና አገልግሎት በነፃ እንደሚያገኙ፣ ለተሰጠውም አገልግሎት የሚያስፈልገው ወጪ በመንግሥት እንደሚሸፈን ገልጸዋል፡፡

ማኅበራዊ የጤና መድን በማስጀመርና በማስፋፋት ላይ ያለመ የሥራ አቅጣጫ መኖሩንም ጠቁመው፣ በዚህ ዓይነቱ የጤና መድን የሚታቀፉት በመንግሥትና መደበኛ ዘርፍ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ፌቨን (ዶ/ር)፣ አብዛኛው ኅብረተሰብ አርሶ አደር ሲሆን፣ የሚኖረውም በገጠር ነው፡፡ ስለሆነም ጤና ኬላዎችንና ጤና ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በተለይ ጤና ተቋማት ላይ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ቤት ለቤት እየተንቀሳቀሱ ከክትባት ጀምሮ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ለሕፃናትና ለእናቶች ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

አገልግሎቱ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል ለጤና ባለሙያዎች በየወቅቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት የሙያ ብቃታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ 

ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ በማስገባት የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑም ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡

ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲቻል ስድስት ዋና ዋና ፒላሮች እንደተዘጋጁ፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የሠለጠነ ወይም ብቁ የሰው ኃይልና የጤና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወደ ሥራ ማስገባት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የጤና ፋይናንስ መረጃ ሥርዓትን ማዘመንና ለጤናው ሴክተር የተመደበው በጀት መጨመር ከስድስቱ ፒላሮች መካከል ተጠቃሽም ነው፡፡

ኢትዮጵያ ይህ ዓይነቱን የጤና አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረጓ የተነሳ ከመጀመርያው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ውስጥ በወሊድ ሳቢያ የሚያጋጥመውን የእናቶች ሕመምና ሞት እንዲሁም የሕፃናትን ሞት እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ለመቀነስ የወጣውን መለኪያ ከሁሉም አገሮች በቀዳሚነት ስኬታማ ለማድረግ እንደበቃች ተናግረዋል፡፡

ከዚህ የተረፉ መለኪያዎችን ደግሞ አሁን በወጣውና እየተተገበረ ባለው የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት ተግታ እየሠራች መሆኑን ፌቨን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ፈተና ገጥሞታል፡፡ የሕወሓት  ቡድን በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ያወደማቸው የጤና ተቋማት መልሰው እስኪገነቡ፣ የተዘረፉ የሕክምና መገልያዎች እስኪተኩ ለኅብረተሰቡ አገልግሎቱን በማዳረስም ሆነ በመካሄድ ላይ ባለው ፕሮግራም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያደርስበትም ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፌቨን (ዶ/ር) ሲመልሱ፣ ‹‹በወረራው ጉዳት ከደረሰባቸው ዘርፎች መካከል የበለጠና የከፋ ጉዳት የደረሰው ጤና ሴክተሩ ላይ ነው፡፡ ከተቀመጡትም ዕቅዶችና ግቦች አንፃር ችግር እንደሚያመጣ ምንም ጥያቄ የለውም፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን ይህንን ችግር ለመወጣት ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ ከእነዚህም ከተለያዩ ምንጮች ሀብት ማሰባሰብ፣ መንግሥት ለአደጋው ምላሽ ራሱን የቻለ በጀትና የሰው ኃይል መመደብ እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት ወደ አገልግሎት የሚገቡበት ሁኔታ እየተመቻቸ ሲሆን፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በሌሎችም አገሮች የሚገኙና የገናን በዓል በማስመልከት ወደ አገር ቤት ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የወደሙ ሆስፒታሎችን ወደ ሥራ በማስገባት እንቅስቃሴ ላይ የየራሳቸውን አሻራ ያኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን ጤና ሚኒስቴር የማስተባበር ሥራዎችንና ሌሎች ዕገዛዎችን የሚያደርግ ግብረ ኃይል አቋቁሟል፡፡ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃም የጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎቱን ደረጃ በደረጃ መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ዕቅድ ነድፏል፡፡

ዕቅዱም ከክሎሎች፣ ከፌዴራልና ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር ከተጎዱ ተቋማት ጋር ጥምረት በመፍጠር መደገፍና አገልግሎት ማስጀመር ነው፡፡ ዕቅዱንም በመከተል የአዲስ አበባ ጤና ቢሮና በፌዴራል ሥር ያሉ ሆስፒታሎች ከወደሙ ሆስፒታሎች ጋር በማስተሳሰር ድጋፍ እንዲያደርጉ ሥራ ተጀምሯል፡፡

በዚህ ዓይነቱ አካሄድ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከደሴ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከከልዋንና ቦሩ ሜዳ፣ አቤት ሆስፒታል ከባቲ፣ የካቲት 12 ሆስፒታል ከወረኢሉ፣ ምኒልክ ሆስፒታል ከመሀል ሜዳ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ከከሚሴ፣ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከሐይቅ፣ ራስ ደስታ ሆስፒታል ከደብረሲና፣ አለርት ሆስፒታል ከኮምቦልቻ፣ ዘውዲቱ ሆስፒታል ከደጐሎ፣ ጋንዲ ሆስፒታል ከሞላሌ ሆስፒታሎች ጋር እንዲሁም አማኑኤል ሆስፒታል ከሁሉም ሆስፒታሎች ጋር ትስስር በመፍጠር ወደ ድጋፍ ሥራው ገብተዋል፡፡

አማኑኤል ሆስፒታል ከሁሉም ሆስፒታሎች ጋር ትስስር ሊፈጥር የቻለው የአዕምሮ ጤናና የሥነ ልቦና ማኅበራዊ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ለማቋቋም የተጣመረው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከ7.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስና የመድኃኒት ድጋፍ በማድረግ የሐይቅ ሆስፒታልን ሥራ አስጀምሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...