Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትቀድሞ ካሜሮን የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና መሰናዶው

ቀድሞ ካሜሮን የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና መሰናዶው

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በካሜሮን አስተናጋጅነት በሚከናወነው 33ኛው አፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ቀድሞ ወደ ሥፍራው ያመራ የመጀመርያው ቡድን ሆኗል፡፡ እሑድ ታኅሣሥ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. 28 ተጫዋቾችንና የመጀመርያውን ልዑክ ይዞ ካሜሮን የደረሰው ብሔራዊ ቡድኑ በአገሪቱ የስፖርትና የሚዲያ አካላት አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በዘንድሮ አፍሪካ ዋንጫ ከሚካፈሉ 24 ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ የሆነው  የዋሊያዎቹ ስብስብ ልምምድ መጀመሩም ተገልጿል፡፡ ዋሊያዎቹ በካሜሮን ቀድመው መገኘታቸውን በጎ አንድምታ እንዳለው ያብራራው የአትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ውድድሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ በሳዑዲ ዓረቢያ ዝግጅት ለማድረግ አቅዶ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እንዳልተሳካለት ጠቅሷል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ ሊያደርገው የነበረው ዝግጅት ባይሳካም፣ የፓን አፍሪካኒዝምን መንፈስ ከማጠናከር አንፃር የተሻለ ምርጫ ተደርጎ በተወሰነው መሠረት በአዘጋጇ አገር ካሜሮን ዝግጅት እንዲደረግ መወሰኑን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በተለይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀድሞ ወደ ካሜሮን ማቅናቱ፣ የአፍሪካ ዋንጫ  የመካሄዱ ነገር ጥያቄዎች እየተነሱበት የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለካፍና ለካሜሮን የውድድሩ መስተንግዶ ዝግጅት ዕውቅና፣ እንዲሁም ለመካሄዱ ጥያቄ ምላሽ እንደሰጠ አስረድቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር ብሔራዊ ቡድኑ በተለይ በምዕራባውያን ሚዲያ ውድድሩ ለሌላ ጊዜ መዘዋወር፣ እንዲሁም መሰረዝ እንዳለበት በአጽንኦት እየሞገቱ ባሉበት ወቅት፣ ሥፍራው ላይ መገኘቱ፣ ለሌሎች አፍሪካ አገሮች ፈር ቀዳጅ መሆን እንደተቻለ ፌዴሬሽኑ በማኅበራዊ ገጹ ላይ አብራርቷል፡፡

ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአዘጋጇ ካሜሮን፣ ቡርኪና ፋሶና ኬፕ ቨርዴ ጋር ተደልድሏል፡፡ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ከመክፈቻው ጨዋታ በኋላ ኬፕ ቨርዴን ይገጥማል፡፡ በዚህም ዋሊያዎቹ ከምድብ ጨዋታቸው ማለፍ ከቻሉ የዘጠኝ ሚሊዮን ብር ጉርሻ እንደተዘጋጀላቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

ዋሊያዎቹ ወደ ካሜሮን ካቀኑበት ዕለት ጀምሮ ዝግጅታቸውን መቀጠላቸው ተነግሯል፡፡ በግብፅ ሊግ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለና በቅርቡ ለአልጄሪያ ሊግ የፈረመው ሙጂብ ቃሲም ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ሊጀምር ቀናት በቀሩት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ቀናት በቀሩት የ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በካሜሮን በደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን ተከትሎ በተለይ በተለያዩ አውሮፓ አገሮች እየተጫወቱ የሚገኙት አፍሪካውያን ተጫዋቾች በውድድሩ እንዳይካፈሉ ጫና እየተደረገ ይገኛል፡፡

የእንግሊዞች ‹‹ደይሊ ሜል›› ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ፣ በተለይ ጨዋታውን ከሚያስተናግዱ ስታዲየሞች መካከል፣ ሦስቱ ለዚህ እርስ በርስ ጦርነት የፀናባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው በተለይ ታዋቂ ተጫዋቾች ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል ያትታል፡፡ ጋዜጣው ከሰብዓዊ መብት ተቋማት አገኘሁት ባለው መሠረት፣ ‹‹አካባቢው በጣም አደጋ ነው፤›› ሲል ያትታል፡፡

በካሜሮን ለአራት ዓመታት የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት የተከሰተ ሲሆን፣ ይኼም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችና ፈረንሣይኛ ተናጋሪ በሆኑት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተከሰተ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህም እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች በፈረንሣይኛ ቋንቋ ጭቆና ደርሶብናል በሚል በደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች ጦርነት ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል፡፡

ምንም እንኳን ጦርነቱ ለውድድሩ ሥጋት ተደርጎ ቢጠቀስም፣ ከሳምንት በፊት በካሜሮን ጉብኝት ያደረጉት የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞቴሴፔ፣ አዘጋጇ አገር በቂ ዝግጅት ማድረጓንና ውድድሩም በታቀደለት ቀን እንደሚከናውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...