ኅብረተሰቡ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚመከሩ መከላከያ መንገዶችን ችላ በማለቱና ከፍተኛ መዘናጋት ውስጥ በመግባቱ በአሁኑ ጊዜ ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረና ዋጋ እያስከፈለ እንደሚገኝ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትና የመደበኛ ክትባት አፈጻጻም ግምገማ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጄ ዱጉማ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታትና ለመቆጣጠር ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ግብዓት በመመደብ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሠራ መቆየቱን፣ የመከላከያ ክትባቱንም አሥር ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ማዳረስ መቻሉን ያስታወቁት ዶ/ር ዱጉማ፣ መዘናጋት ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ኅብረተሰቡ በኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዙሪያ ግንዛቤውን እንዲያሳድግ፣ ክትባቱን እንዲወስድና ሌሎች የጥንቃቄ መንገዶችን እንዲያከብር ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መሠረት ዘለዓለም (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ከጤና ተቋም በተገኘ መረጃ ብቻ 6,800 የሚሆኑ ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉንና በርካታ ዜጎችም ለጤና፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
የኮቪድ-19 በሽታ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትንና ሌሎች መከላከያ ምክሮችን ዜጎች ካለመዘናጋት እንዲጠቀሙና ሁሉም ባለድርሻ አካላት እስካሁን ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያስገነዘቡት ዶ/ር መሠረት፣ ሌሎች የመደበኛ ክትባቶችም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም ጥሩ አፈጻጸም እንዳለ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የግጭት አካባቢ በነበሩ ሥፍራዎች ትልቅ ሥራ እንደሚጠይቅና በዚህ ዙሪያም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎች፣ ከአጋር አካላትና በኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት ዙሪያ እየሠሩ ያሉ ባለሙያዎች በተገኙበት ታኅሳስ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ የተጀመረው ግምገማ ለአራት ቀናት እንደሚቆይ ጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡