Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ፆታዊ ጥቃትን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር የቋማት ተሳትፎ

በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት እንዲቆም መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት መሥራት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም ሥር የሰደደውን በሴቶች ላይ የሚደርስ በደል ማስቆም አልተቻለም፡፡ ሴቶች ዛሬም ፈተና ላይ ናቸው፡፡ ይደፈራሉ፣ ይደበደባሉ፣ ቃላዊና ስሜታዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፡፡ በተለይ ግጭትና ጦርነት ባሉባቸው ሥፍራዎች ሴቶች የእልህ መወጣጫ እስኪመስሉ ድረስ የፆታዊ ጥቃት ሰለባ ናቸው፡፡ ከወንዶች ያልተናነሰ እንዲያውም የላቀ ቁጥር ቢኖራቸውም የመማር ዕድላቸው አናሳ ነው፡፡ በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ በብዛት አይገኙም፡፡ ይህን የዓለም እውነታ ኢትዮጵያውያት ሴቶችም ይጋሩታል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በትምህርት፣ በሥራ ቦታና በከፍተኛ የኃላፊነት እርከን ያለው የሴቶች ተሳትፎ እያደገ ቢመጣም፣ ሴቶች ከወንዶች በላቀ የፆታዊም ሆነ የአካላዊ ጥቃት ሰለባ ናቸው፡፡ በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረውና ዛሬ ላይ ረገብ ባለው ጦርነት ይበልጡኑ ለጥቃት የተጋለጡት ሴቶችና ሕፃናት ናቸው፡፡ በዓለም አቀፉ ደረጃም ሲታይ በተለይ ግጭትና ጦርነት ባለባቸው ሥፍራዎች በአብዛኛው ለጥቃት የሚጋለጡት ሴቶች ናቸው፡፡ ግጭት ያለባቸውን ጨምሮ በሁሉም ሥፍራዎች ከሚኖሩ የዓለም ሴቶች አንድ ሦስተኛ ያህሉ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፡፡ ይህ ይቆም ዘንድ በየዓመቱ ፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡ ይህንን አስመልክቶም የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ16 ቀናት የዘለቀ ዘመቻ ባለፈው ወር አካሂዶ አጠናቋል፡፡ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የተለያዩ ተቋማትም ፆታዊ ጥቃትን ለማስቆም እያከናወኑ ስላሏቸው ተግባራት አብራርተው ነበር፡፡ በፓናል ውይይቱ መሪ ፓካርድ ፋውንዴሽን በኩል ለቀረቡ ጥያቄዎችም የተለያዩ ተቋማት መልስ ሰጥተዋል፡፡ ምሕረት ሞገስ አጠናክራዋለች፡፡

ጥያቄ፡- ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ምን እየሠራ ነው? ምን ችግርስ ገጥሞታል?

የሴቶችና ማኅበራዊ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፡- በዋነኛነት ኢትዮጵያ ተቀብላ በሕግ ያካተተቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ የሴቶች ፖሊሲ ከወጣ ረዥም ጊዜው ነው፡፡ ለዚህ የሕግ ማዕቀፍ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ካልወጣና መሠረት ካልያዘ ምንም መሥራት አንችልም፡፡ በ1986 ዓ.ም. የወጣው የሴቶች ፖሊሲ ብዙ ርቀት አስኪዶናል፡፡ ነገር ግን አሁን ካለንበት አንፃር መከለስ አለበት፡፡ አሁን በተለየ የምናያቸው ፆታዊ ጥቃቶች፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ የፖሊሲ ማዕቀፉ ሁሉን አቀፍ ሆኖ ባለመውጣቱ ይህን ለማስተካከል ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ ከባህል ጋር ተያይዞ ልንቀርፍ ያልቻልናቸው ችግሮች አሉ፡፡ ይህንን ለመቅረፍ እንሠራለን፡፡ ለዚህ ተቋማዊ አደረጃጀት መዘርጋት ግድ ይላል፡፡ ቅንጅታዊ ሥራም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ለአንድ ጊዜ ተሠርቶ እንዳይቆምና በተቋም መልክ ምላሽ እንዲያገኝ ይረዳናል፡፡ የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የወንዶችም ኃላፊነት አለ፡፡ ወንዶች ጥቃት አድራሽ ብቻ ሳይሆኑ መከላከል እንዲችሉ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን ዘርግተን እየሠራን ነው፡፡ ‹ሂ ፎር ሺ› የሚለው ፕሮግራማችንም የዚህ አካል ነው፡፡ ጥቃት ከመድረሱና ከደረሰ በኋላ ጥቆማ የሚሰጥበትና መፍትሄ እዛው የሚገኝበት የአንድ መስኮት አገልግሎት ለማጠናከር እየሠራን እንገኛለን፡፡

ጥያቄ፡–  ስለ ሴቶች ሲነሳ የጤና ጉዳይ ዋናው ነው፡፡ በተለይ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የሕክምና ተደራሽነቱ ምን ይመስላል? የአንድ መስኮት አገልግሎት ዝግጅትስ ምን ያህል ነው?

የጤና ሚኒስርት ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፡- የሴቶችን ጥቃት መከላከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ በስትራቴጂያችንና በጤና ፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡ ቀድሞ በመከላከል ሥራው በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በኩል ኅብረተሰቡን ቀርበን ግንዛቤ በማስጨበጥ እንሠራለን፡፡ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጉዳታቸው የአካል ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቦናም ነው፡፡ ለኤች አይቪ፣ ለሄፒታይተስና ለእርግዝና ሊጋለጡ ስለሚችሉ ምርመራ ይደረጋል፡፡ የአዕምሮ ሕከምናና የሥነ ልቦና ሕክምናም በጤና ተቋም ደረጃ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ክስተቱ ቶሎ ሪፖርት የማይደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎት በሆስፒታል ነው የሚሰጠው፡፡ የጤና፣ የሕግ፣ የፖሊሲ ድጋፍ የሚያገኙበት ላይ እየተሠራ ቢሆንም፣ ይቀረዋል፡፡ አሁን ላይ አገልግሎቱ በ36 ቦታ ይሰጣል፡፡ ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ አሁን በገጠመን ፈተና ሴቶች በጣም እየተጎዱ ስለሆነ አገልግሎቱን ማስፋፋት ይጠበቅብናል፡፡ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ይህ አገልግሎት እንዲስፋፋ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ለገጠመን ችግር የተለያዩ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡ የሕግ፣ የጤና፣ የሥነ ልቦና ሌሎች የተለያዩ ባለሙያዎችን ማቀናጀት ይጠበቅብናል፡፡ የመከላከል ሥራው ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ግንባታው ላይ መሥራት ግድ ይላል፡፡ ፆታዊ ጥቃትን የሚፀየፍ ትውልድ መፍጠር አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉም ቅንጅት ያስፈልጋል፡፡  

ጥያቄ፡- ሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ልዩ ባህሪ አላቸውና የፍርድ ቤት አደረጃጀትና አሠራር ምን ይመስላል? የባለሙያዎች ግንዛቤስ እንዴት ነው?

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፡- ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን ከመሠረቱት አንዷ ስለነበርኩ የሴቶችን ጥቃት መቆም አለበት የሚለውን ወደፊት ለማምጣት ጥረናል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሲቪል ማኅበረሰብና ሌሎች ሲቪል ማኅበራት አብረው መሥራት አለባቸው፡፡ በሰሜኑ ክፍል ያለው ጦርነት በርካታ ገጽታዎች ያሉት፣ ሕይወትን የነጠቀና በሚሊዮን ያፈናቀለ ነው፡፡ የተለያዩ ሪፖርቶች በሴቶች ላይ ዓለም አቀፍ መርሆችን የሚጥስና ሰብዓዊነትን ከግምት ያላስገቡ ጥሰቶች በሴቶች ላይ እየተፈጸሙ ስለመሆኑ እያሳዩ ነው፡፡ ይህንን ዝም ልንል አንችልም፡፡ መጋፈጥ አለብን፡፡ ይህ ጦርነት ማለቁ አይቀርም፡፡ በቀጣይ ምን መሥራት አለብን የሚለውን ካሁኑ ተባብረን መሥራት አለብን፡፡ ችግሩን የሚያጠና ኮሚሽን ቢቋቋም ጥሩ ነው፡፡ አሁንም የሴቶች ጉዳይ በቂ ትኩረት ያገኛል የሚለው ያሳስበኛል፡፡  ሙሉ ጥናቶች ሲመጡ ብዙ ነገሮች እንሰማለን፡፡ በመሥሪያ ቤታችን ሥርዓተ ፆታን አካተን እየሠራን ነው፡፡ የሴቶችና ሕፃናት ልዩ ችሎቶች በስምንት ክፍላተ ከተሞች አሉ፡፡ ከፆታዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ይመጣሉ፣ ውሳኔ ያገኙም አሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ አይደሉም፡፡ ያልበዛበትም ሰዎች ወደ ፖሊስ ስለማይሄዱ ነው፡፡ በዓለም ከአሥር አንድ ሴት ናት ፍትሕ ፍለጋ የምትሄደው ምክንያቱም የባህል፣ የፍትሕ ሥርዓት ላይ ሥጋት መኖርና ሌሎችም ላለመምጣታቸው ምክንያት ናቸው፡፡ የሕፃናት ፍትሕ ማዕከል አለ፡፡ ከ38 በላይ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ አሉ፡፡ ሕፃናት ጥቃት ደርሶባቸው ፍርድ ቤት ሲመጡ ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ የሚከናወንበት ነው፡፡ ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልሎች ቢስፋፉ ጥሩ ነው፡፡ አማራና ኦሮሚያ ላይ ዩኒሴፍ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ ‹ትኩረታችን ሌላ ነው› ብለው ትተውታል፡፡ ይህ ቢሠራበት ጥሩ ነው፡፡  ስለ ሥርዓተ ፆታ፣ ማስረጃ ማቅረብ፣ ሕፃናትና ሴቶች ላይ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ የሚገኝበትን መመርያ የሚይዝ ቤንች ቡክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋርም እየሠራን ነው፡፡

ጥያቄ፡- ፍትሕ ሚኒስቴር ያደረጋቸው የሕግ ማሻሻያዎች አሉ? ብሔራዊ ጥምረቱ ያለውን አስተዋጽኦ?

የፍትሕ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ፡- በፍትሕ ሚኒስቴር ደረጃ ከሕግ አንፃር በ1996 ዓ.ም. ወጥቶ በ1997 ዓ.ም. ተግባር ላይ የዋለው የወንጀል ሕግ ላይ ምን ክፍተት አለበት በሚለው ዙሪያ ዓምና ጥናት ተሠርቷል፡፡ ጥናቱ ክፍተቱን አሳይቷል፡፡ ለምሳሌ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት አንድ ዓመት ያስቀጣ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕይወት ሊነጥቅ የሚችል ነው፡፡ በወቅቱ ማስተማር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የወጣ ሕግ ነው፡፡ ሆኖም ላለፉት 18 ዓመታት ግንዛቤ ተገኝቷል፡፡ አስገድዶ መድፈር በአብዛኛው ማስረጃ በሌለበት የሚፈጸም ነው፡፡ ይህ ውይይት ተደርጎበት ተሻሽሎ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ ሕፃናትን የፍትሕ አገልግሎት ለማስተባበር ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የፍትሕና የክብካቤ ማዕከል አለ፡፡ ነገር ግን አመራሮች በተቀያየሩ ቁጥር ሥራው በአግባቡ አልተሠራም፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዴት መሥራት አለበት የሚለውን እየሠራንበት ነው፡፡ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች ምላሽ ምን መሆን አለበት የሚለውና ወንጀልን ከመከላከልና ሲፈጠር ከመክሰሱ አንፃር እየተሠራ ነው፡፡ 

ጥያቄ፡- የሴቶችና ሕፃናትን መብት ከማስከበር አኳያ ኮሚሽኑ የሚሠራው ሥራና ያጋጠመው ችግር?

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ መስከረም ገስጥበኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ትልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ናቸው፡፡ ኮሚሽናችን በይዘቱ መንግሥታዊ ቢሆንም ነፃነትና ገለልተኛነት ያለው ነው፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲሠሩ እንሠራለን፡፡ የመብት ጥሰት የገጠማቸው አካላት ድምፃቸው እንዲደመጥ እናደርጋለን፡፡ ሴቶችና ሕፃናት ከፍተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ናቸው፡፡ እኔ በኮሚሽነርነት የምመራው የሴቶችና ሕፃናትን ዘርፍ ነው፡፡ ከሰሜኑ ግጭት ጋር ተያይዞ ብዙ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እንሰማለን እናያለን፡፡ የጥቃቶች ግዝፈትና ዓይነትን ለማየት የምርመራ ሥራ አለን፡፡ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር እንዲሁም በሌሎች የሰብዓዊ መብት፣ ጥሰቶችን ይፋ አድርገናል፡፡ የደረሱ ጥሰቶች ላይ ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ ሰነድ የመሰነድ፣ ዘገባ የማጠናከርና የተጎጂዎችን ድምፅ የማሰማት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ መንግሥታዊ አካላት ተጠያቂነት ላይ ጥቆማ እንሰጣለን አሠራርና ድርጊቶችን እንኮንናለን፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው እንዲያገግሙ፣ ተገቢ ፍትሕ፣ የመልሶ ማቋቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ከሌሎች ጋር ተባብረን እንሠራለን፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ፆታዊ ጥቃቶች በትምህርት ቤት፣ በቤትና በተለያዩ ቦታዎች ስለሚፈጸሙ ክትትል በማድረግ ምክረ ሐሳብ እንሰጣለን፡፡ በዚህ ውጤት ዓይተናል፡፡ በማረሚያ ቤትና በሌሎችም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንጠቁማለን፡፡ ተያያዥ ሕጎችን እንገመግማለን፣ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ሕጎቹ ምን ያህል ጠንካራ መሆን አለባቸው የሚለው ላይ እንሠራለን፡፡ የሴቶችን መብት የሚያከብር ልምድ እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ የሰብዓዊ መብትን የሚያከብርም እንዲፈጠር የግንዛቤ ሥራ እንሠራለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...