የኢትዮጵያን የባንክ ገበያ የተቀላቀለበትን 25ኛ ዓመት እየዘከረ ያለው ወጋገን ባንክ፣ የ2013 የሒሳብ ዓመት ትርፉ ከ880 ሚሊዮን ብር በላይ በመቀነስ ከታክስ በፊት 193.1 ሚሊዮን ብር ማትረፉ ተገለጸ፡፡
ባንኩ ቅዳሜ ታኅሳስ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው እንዳስታወቀው፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት ባጋጠሙት የተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት፣ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 193.1 ሚሊዮን ብር ብቻ ሆኗል፡፡ ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉ የሚታወስ ሲሆን፣ የ2013 የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠን ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከ880 ሚሊዮን ብር መቀነሱን የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት አመላክቷል፡፡
ባንኩ ባለፉት 20 ዓመታት ካስመዘገባቸው ትርፎች የአሁኑ ዝቅተኛ የሚባል ሲሆን፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት 18 ባንኮች ካስመዘገቡት ዓመታዊ ትርፍ አንፃር ሲታይም ዝቅተኛው ነው፡፡
በሒሳብ ዓመቱ የትርፍ መጠኑ በጣም በመቀነሱ የትርፍ ክፍፍል ድርሻንም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ በ2012 ሒሳብ ዓመት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን አስገኝቶ የነበረው 310 ብር ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን ያስገኘው 42 ብር ብቻ ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለትርፍ መቀነሱ የተለያዩ ምክንያቶች ቀርበዋል፡፡ በባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ ኢትዮጵያ ያለችበት የንግድ ሥራ በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ሆኖ መቆየቱ የባንክ ኢንዱስትሪውን በተለይም ባንኩን በመፈተን ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ችግር ባሻገር ኮቪድ-19 እና ከአንድ ከዓመት በላይ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የዘለቀው ጦርነት ተጠቁመዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ከባንኩ ቅርንጫፎች አንድ ሦስተኛ መዘጋታቸውና ከፍተኛ መጠን ባለው ሀብቱ ላይ ውድመት መድረሱ በባንኩ የሥራ አፈጻጸም ላይ ጫና ማሳደራቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ እንዲህ ያሉት ተግዳሮቶች በባንኩ ገቢ የማመንጨት ሥራ ላይ እንቅፋት በመሆናቸው፣ የትርፍ መጠኑ በእጅጉ እንዲያሽቆለቁል ማድረጋቸው ተብራርቷል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በመልካም ስሙ ላይ የደረሰበት የስም ማጥፋት ዘመቻ በሥራ እንቅስቃሴው ላይ ከባድ ጫና ማሳደሩን ሪፖረቱ ይገልጻል፡፡ በእዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቋል፡፡
የወጋገን ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብድሹ ሁሴን ባቀረቡት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደገለጹት፣ በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ቅርንጫፎች ለረዥም ጊዜ ከሥራ ውጪ ሆነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከክልሉ ሲገኝ የነበረው ከፍተኛ ተቀማጭ ገንዘብ ሳይሰበሰብ በመቅረቱ፣ በአካባቢው ተሰጥቶ የነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር በጊዜው መሰብሰብ አልተቻለም ብለው፣ የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል፡፡ ከትርፍ ተቀናሽ በማድረግ ከፍተኛ መጠባበቂያ ገንዘብ እንዲይዝ በመገደዱም የባንኩን ዓመታዊ ትርፍ መጠን እንደቀነሰው አመልክተዋል፡፡
በተሳሳተ የሚዲያ ዘገባ ምክንያት በባንኩ ላይ የደረሰው ስም ማጥፋት ዘመቻ፣ እያደገ የመጣው የዋጋ ንረት፣ ከፀጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው መቀዛቀዝና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት በሒሳብ ዓመቱ የባንኩን የሥራ እንቅስቃሴ በማስተጓጎል አፈጻጸሙ ዝቅ እንዲል አድርገዋል ብለዋል፡፡ ይሁንና ከባንኩ ዕቅድ አኳያ አንፃር የሥራ አፈጻጸሙ ዝቅ ያለ ቢሆንም፣ ያጋጠሙትን ፈታኝ ተግዳሮቶች ተቋቁሞ በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው 193.1 ሚሊዮን ብር ትርፍ አበረታች ሊባል የሚችል መሆኑን የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
በሌሎች የባንኩ አፈጻጸሞች ላይ የታየው ዓመታዊ ዕድገት ከቀደሙት ዓመታት ያነሰ መሆኑን ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበሩ ባቀረቡት ሪፖርት የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ጭማሪ ያሳየው በአምስት በመቶ ነው፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመት ባንኩ የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ 30 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2013 መጨረሻ ላይ ደግሞ በ1.4 ቢሊዮን ብር ጨምሮ 31.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን ደግሞ ዕድገት ያሳየው በ15 በመቶ ነው፡፡ ይህም አጠቃላይ የባንኩን የብድር ክምችት 27.3 ያደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በዚሁ ሪፖርታቸው፣ ‹‹በ2013 ዓ.ም. ኢኮኖሚው 4.9 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው የዓለም ገንዘብ ድርጅት ትንበያ የሚያመለክት ቢሆንም፣ በአንፃሩ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረው ግጭት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ ያስከተለው አሉታዊ ተፅዕኖ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ምልከታ ወይም ትንበያ አስቸጋሪ አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡
አያይዘውም ባንካቸው እንዲህ ያለውን አገራዊ ተግዳሮቶች በመጋፈጥ ቁርጠኝነቱን የሚያስተካክልና ያሉትን ግብዓቶች በመጠቀም፣ እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን ከባንኩ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ጋር በማዋሀድ የአፈጻጸም ውጤቱን በእጅጉ ለማሳደግ ባለው ጉልበት ሁሉ ተግቶ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡
ወጋገን ባንክ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች 399 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ ከ5,000 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ ባንኩ የባለአክሲዮኖችን ቁጥር ከ4,000 በላይ አድርሷል፡፡ ወጋገን ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሒሳብ ዓመቱ 33 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ይህንንም ለአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟያና ምገባ አንዱ ነው፡፡ ገበታ ለአገርና ለሸገር ፕሮጀክቶች ደግሞ 15 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቁሟል፡፡
በ2012 የሒሳብ ዓመት 2.9 ቢሊዮን ብር የነረው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ወደ 3.3 ቢሊዮን ብር ማድረጉን፣ ጠቅላላ ካፒታሉ አምስት ቢሊዮን ብር ማድረሱን ገልጿል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመትም 38.2 ቢሊዮን ብር የነበረው ጠቅላላ ሀብቱም በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ወደ 39.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡
ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም. በ16 ባለአክሲዮኖች በ60 ሚሊዮን ብር የተፈረመ መነሻ ካፒታልና በ30 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ወጋገን ባንክ፣ ሰኔ 2014 ዓ.ም. 25 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ይህንን ክብረ በዓል በተለያዩ ክንውኖች በማክበር ላይ እንደሚኝ ባንኩ ገልጿል፡፡