Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዳያስፖራዎች ይጠቀሙባቸዋል በተባሉ ተቋማት ላይ ቁጥጥር  መጀመሩ ተገለጸ

ዳያስፖራዎች ይጠቀሙባቸዋል በተባሉ ተቋማት ላይ ቁጥጥር  መጀመሩ ተገለጸ

ቀን:

የአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዳያስፖራዎች የሚያርፉባቸው ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ቁጥጥር መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ማክሰኞ ታኅሳስ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከዚህ በፊት ያደርግ ከነበረው መደበኛ ቁጥጥር በተጨማሪ፣ ከታኅሳስ 13 እስከ ታኅሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚቆይ ዘመቻ እያካሄደ ነው፡፡ እየተደረገ ባለው ዘመቻ ከውጭ የሚመጡ እንግዶች ሊያርፉባቸውና ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ባለኮኮብ ሆቴሎች፣ ማረፊያ ቤቶች፣ ባሮች፣ ሬስቶራንቶችና የባህል ምግብ  ቤቶች የመሳሰሉ ተቋማት ላይ ትኩረት መደረጉ ተገልጿል፡፡

ዘመቻው እንደ ማሳጅ ቤቶች፣ ፀጉር ቤቶችና የኮስሞቲክስ መሸጫዎችን የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንም እንደሚያካትት የባለሥልጣኑ የምግብና መጠጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት በዳዳ ተናግረዋል፡፡

በዘመቻ እየተደረገ ባለው ቁጥጥር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የውኃ አቅርቦት፣ የፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ የሠራተኞች የጤና ምርመራና የምግብ ማብሰያ ንፅህናን የተመለከተ ግምገማ እየተካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በሆቴሎች ላይ በተካሄደው ምልከታም የምግብ ማብሰያ ክፍል ሠራተኞች ንፅህና፣ግብዓት ማስቀመጫ ክፍሎችናመጋዘኖች ያሉ ምግቦች አቀማመጥ ሁኔታ፣ የደረቅ ቆሻሻ አቀማመጥና የመሳሰሉት ላይ ጉድለቶች እንደተገኙ ተጠቁሟል፡፡

እስካሁን በተደረገው ዘመቻ 380 ያህል የምግብና መጠጥ ተቋማት ላይ ቁጥጥር መደረጉን የተናገሩት ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ችግር በታየባቸው 35 ተቋማት ላይ ዕርምጃ እንደተወሰደም አስታውቀዋል፡፡ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት ውስጥ 20 ያህሉ የተገኘባቸው ችግር በቀላሉ የሚስተካከል በመሆኑ በማስጠንቀቂያ መታለፋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በየኅብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርስ ችግር የተገኘባቸው 15 ተቋማት ደግሞ ጉድለቱ እስኪቀረፍ ድረስ መታሸጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የባለሥልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ዳይሬክተር ብሪሳ ሚደቅሳ በበኩላቸው፣ ወደ አገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎችን የሚያሳርፉ ተቋማት የኮቪድ-19 መመርያ አተገባበራቸው ላይም ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ባለሥልጣኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ አንስቶ የኮቪድ-19 መመርያ አጠባበቅን በተመለከተ፣ በ16 ሺሕ ተቋማት ላይ ከሦስት ግዜ በላይ ምልከታ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በመጪዎቹ የበዓል ቀናት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ዳያስፖራዎች አቀባበልና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በጋራ ለመሥራት ከአዲስ አበባ ሆቴሎች ድርጅት፣ ከቱሪስት ታክሲ ማኅበራት፣ ከአዲስ አበባ የግል አስጎብኚና ከኢትዮጵያ የአስጎብኚ ማኅበራት ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ይታወሳል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎችም እስከ 30 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እያደረጉ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

የከተማዋ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የዳያስፖራዎችን መምጣት ተከትሎ የሆቴሎች የመኝታ አቅርቦት አለመመጣጠን ሊከሰት እንደሚችል በማስታወቅ፣ የእንግዳ ማረፊያና አፓርትመንት ያላቸው ግለሰቦች በሚኖሩበት ክፍለ ከተማ የባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በመገኘት ‹‹ተገቢና ተመጣጣኝ” የሆነ ዋጋ በመተመን እንዲያሳውቁ ጠይቆ ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን  የብቃት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሆቴሎችና ሌሎች ተቋማት ባለሀብቶችን በአካል አግኝቶ ማወያየቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ይኼ ወቅት እንግዶች “በመልካም ሁኔታ” የሚስተናገዱበት በመሆኑ የአልግሎት ጥራት ጉድለትና የዋጋ ጭማሪ መታየት እንደሌለበት ከተቋማቱ ባለቤቶች ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በመጪው የበዓል ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በምግቦች ውስጥ ባዕድ ነገሮችን መቀላቀል፣ ሕገወጥ ዕርድና በአያያዝና በአጠቃቀም የተበላሹ ምግቦችን መልሶ የማቅረብ ድርጊት የተለመደ በመሆኑ ነዋሪዎች ጥቆማ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ ገበያተኞችም በባለሥልጣኑ የብቃት ማረጋገጫ ከወሰዱ ተቋማት ብቻ ምርትና አገልግሎቶችን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...