Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች የመጡና የተመረቁ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ...

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች የመጡና የተመረቁ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበ

ቀን:

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች የመጡና ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የቀድሞ ተማሪዎቹ በተያዘው ወር መጨረሻ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበ፡፡

እነዚህ 41 የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች፣ ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ፣ ከቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞንና ከትግራይ ክልል የመጡ ሲሆኑ፣ የመጡበት አካባቢ ላይ የፀጥታ ችግር በመኖሩ ቢመረቁም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እንዲቆዩ ማመልከቻ አስገብተው ነበር፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ማቲዮስ ኤርሳሞ (ዶ/ር) ተማሪዎቹ ከተመረቁ በኋላ በግቢው ውስጥ ቆይተው የመኝታና የምግብ አገልግሎት ሲያገኙ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ ከተመረቁ በኋላ በግቢው ውስጥ እንዲቆዩ የፈቀደው፣ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ አሁን ላይ ግን ተማሪዎቹ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ማቲዮስ (ዶ/ር) ‹‹እንደ ሕጉ ከሄድን አንድ ተማሪ የምግብ፣ መኝታና ሕክምና አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችለው እስከ ምረቃ ቀኑ ድረስ ብቻ ነው›› ያሉ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው አሁን ያለው ሁኔታ ‹‹ተለዋዋጭነት ያለው›› ውሳኔ የሚያስፈልገው መሆኑን በመረዳት ተማሪዎቹን እስካሁን እንዳቆየ አስረድተዋል፡፡

ማቲዮስ (ዶ/ር) እንደገለጹት ከሆነ፣ በዩኒቨርሲቲው እንዲቆዩ የተፈቀደላቸው ተማሪዎች ላይ ‹‹ችግሮች›› የታዩ ሲሆን፣ አንዳንድ ተመራቂዎች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሥራ ካገኙም በኋላ በግቢው መኖር ቀጥለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎቹ የመጡበት አካባቢ በትክክል የፀጥታ ሥጋት ያለበት መሆንና አለመሆኑ ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጸው፣ ተመራቂዎቹም በትክክል የሚኖሩበትን ቦታ ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትግራይ ክልል ጦርነት ከተነሳበት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎችን ከተመረቁም በኋላ እያስተናገደ መቆየቱን ያስታወሱት ማቲዎስ (ዶ/ር)፣ ከክልሉ የመጡት ተመራቂዎች በጊዜ ሒደት ሥራ በማግኘታቸውና ወደ መኖሪያቸው በመመለሳቸው አሁን ላይ በግቢ ውስጥ ያሉ ከትግራይ የመጡ ተማሪዎች ቁጥር ‹‹ጥቂት›› ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከተመረቁ በኋላ አገልግሎቶችን እያገኙ ያሉ ተማሪዎች ላይ በጀትን የተመለከተ ጥያቄ ያነሳ ሲሆን፣ የተመደበለት በጀት የተገደበ በመሆኑ ለእነዚህ ተማሪዎች አገልግሎት እያቀረበ ያለው ከሌሎች በጀቶች ‹‹እየቀነሰ›› መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ማቲዎስ (ዶ/ር) ‹‹ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያላቸው ሕጋዊ ውል ይቋረጣል›› ብለው ዩኒቨርሲቲው ለተመረቁ ተማሪዎች ወጪ ማውጣት ሥልጣን እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

በኮቪድ-19 የተነሳ ትምህርት በመቋረጡ የመማር ማስተማር መርሐ ግብሩ የተዛባበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ተማሪዎቹን ያስመረቀው መስከረም 30 ቀን  2014 ዓ.ም. ላይ ሲሆን፣ አሁን በግቢው ውስጥ እየተሰጠ ያለውን የመጀመርያ መንፈቅ ዓመት ትምህርት በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ አገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና መሰጠቱን ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ምደባን በቅርቡ እንደሚያደርግ በማሰብ፣ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከተመረቁ በኋላ በግቢው ውስጥ አገልግሎት እያገኙ ያሉት ተማሪዎች ‹‹ለአዲስ ተማሪዎች ቦታ መልቀቅ›› እንዳለባቸው የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ማቲዮስ ኤርሳሞ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...