Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሳዑዲ ዓረቢያ ኢትዮጵያውያንን ለይቶ የማሰር ሁኔታ መኖሩ ተነገረ

በሳዑዲ ዓረቢያ ኢትዮጵያውያንን ለይቶ የማሰር ሁኔታ መኖሩ ተነገረ

ቀን:

ከ80 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል

ከሦስት መቶ በላይ ስደተኞች ከሊባኖስ ተመልሰው ኢትዮጵያ መቋቋማቸው ተገለጸ

የሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለይቶ የማሰር ሁኔታ እንደሚታይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ገብረ ማርያም ይኼንን ያስታወቁት፣ ታኅሳስ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው ‹‹ኢትዮጵያ ቤቴ›› የተሰኘ ስደተኞችን ወደ አገር ቤት የመመለስ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ መንግሥት ከወራት በፊት በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ላይ የነበሩ 40 ሺሕ ያህል ኢትዮጵያዊ ስደተኞችን በ15 ቀናት ውስጥ ወደ አገር እንደመለሰ አስታውሰው፣ አሁንም ‹‹ሳዑዲ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ለይቶ የማሰር ሁኔታ  ይታያል፤›› ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ፣ ከአጋር ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በአሁኑ ጊዜ 80 ሺሕ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸውና የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ላይ የሚገኙ መሆናቸውን፣ መንግሥት እነዚህን ዜጎች ወደ አገር ቤት የመመለስ ሥራ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ይሁንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለተመላሾች ብሎ አገር ውስጥ የተከራያቸው ሰባት የስደተኛ መጠለያዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከዚህ ቀደም በመጡ ስደተኞች እንደተሞሉ ለሪፖርተር ያስረዱት አቶ መስፍን፣ መጠለያ ውስጥ ያሉት  አብዛኞቹ ስደተኞች የጦርነት ቀጣና ከነበረው የሰሜኑ ክፍል የመጡ በመሆናቸው ከመጠለያ እንዲወጡ ማድረግ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

አሁን በሳዑዲ በእስር ላይ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሄዱና ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወደ ቀዬአቸው መመለስ የማይችሉ በመሆናቸው፣ መጠለያዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ዜጎቹን ወደ አገር ቤት የመመለስ ሥራው የመንግሥት ውሳኔን የሚጠይቅ መሆኑን ያስረዱት አቶ መስፍን፣ ሥራው በቅርቡ ይጀመራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አክለዋል፡፡

መንግሥትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሕጋዊ ያልሆኑ መንገዶችን ተከትለው ከአገር የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ለከፋ ችግር እንደሚዳረጉ ለዓመታት ሲገልጹ ቢቆይም፣ አሁንም በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡ አቶ መስፍን በየዓመቱ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ‹‹አመቺ ባልሆኑ›› መንገዶች ወደ ተለያዩ አገሮች እንደሚሄዱ ገልጸው፣ አብዛኞቹም ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብና ከትግራይ ክልሎች የሚነሱ ስደተኞች መሆናቸውን  አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር በተደረገ ስምምነት የውጭ የሥራ ሥምሪት ሥርዓት መዘርጋቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን አሁንም አብዛኛዎቹ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት በተለያዩ አገሮች በችግር ላይ የሚገኙ ስደተኞችን የመመለስ ሥራ በተደጋጋሚ ሲያከናውን ቢስተዋልም፣ ብዙዎቹ ስደተኞች ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ የሚደረግላቸው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ ተመልሰው ወደ ስደት እንደሚያመሩ ተገልጿል፡፡ አቶ መስፍን፣ ‹‹አንዳንዴ ወደዚህ ከመለስናቸው በኋላ ምንድነው ተስፋቸው የሚለውን ማሰብ ይጨንቃል፤›› ብለዋል፡፡

ፍሪደም ፈንድ የተባለ ግበረ ሰናይ ድርጅት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከቀድሞው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባባር፣ ተመላሾችን በአገር ውስጥ በዘላቂነት በማቋቋም ወደ ስደት እንዳይመለሱ የሚያደርግ ሞዴል የሚተገብር ‹‹ኢትዮጵያ ቤቴ›› የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

በሊባኖስ በችግር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር መልሶ ለማቋቋም በሚል ዓላማ የተጀመረው ‹‹ኢትዮጵያ ቤቴ›› ፕሮጀክት፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 386 ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት በመመለስ 350 ተመላሾችን ማቋቋም መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

ፕሮጀክቱ አዲስ ዓይነት ሞዴል በመጠቀም በተገበረው አሠራር፣ ወደ አገር ካመጣቸው ተመላሾች ውስጥ በድጋሚ ወደ ስደት የተመለሰ አለመኖሩ ተገልጿል፡፡ በፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ተጨማሪ 500 ስደተኞችን የማቋቋም ዕቅድ እንደተያዘ፣ የፍሪደም ፈንድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መለሰ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አሁን የመጀመሪያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው የ‹‹ኢትዮጵያ ቤቴ›› ፕሮጀክት፣ ስደተኞችን በራሱ ወጪ ወደ አገር ቤት የሚመልስ ሲሆን፣ ከተመለሱ በኋላም ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልጋቸው የዕርዳታ መጠን ከቀናት እስከ ስድስት ወር የሚዘልቅ የአካላዊና የአዕምሮ ሕክምና ይሰጣል፡፡ አቶ ዳንኤል እንደሚናገሩት ስደተኞቹ ከመምጣታቸው በፊት ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት የሚሠራ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ስደተኞችም ከሆስፒታል፣ ከእስር ቤትና ከመንገድ ላይ እየተነሱ የሚመጡ ናቸው፡፡

ስደተኞቹ ሕክምናና ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግና ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ እንደሚገቡ አስታውቀዋል፡፡ ተመላሾቹ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላም ቢሆን ለስድስት ወራት ያህል የሚደረግላቸው ድጋፍና ክትትል የሚቀጥል በመሆኑ፣ ሞዴሉ ውጤታማ እንዲሆን እንዳስቻለ ተገልጿል፡፡

በመጀመሪያው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ 386 ያህል ዜጎችን ከሊባኖስ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የተቻለ ሲሆን፣ 350 ያህሉ ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል፡፡ ተመላሾቹ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብና ከሲዳማ ክልሎች፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተሞች የመጡ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ተመላሾቹ ለፕሮጀክቱ ተብሎ በተዘጋጁ ማገገሚያ ማዕከላት ሥልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ መጡበት አካባቢ የሚመለሱ ሲሆን፣ ከመንግሥት ጋር በተደረገው ትብብር አማካይነትም ባሉባቸው አካባቢዎች በሚገኙ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ድጋፍና ክትትሉ ይቀጥልላቸዋል፡፡

‹‹በዚህ ፕሮጀክት ያመጣናቸው ተመላሾች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ሞዴሉ ውጤታማ እንደሆነ ያሳያል፤›› ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሞዴሉን እንዲተገብሩት የማድረግ ዕቅድ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ወደ አገር ውስጥ ያመጣቸው ሁሉም ዜጎች በሊባኖስ የነበሩ ሲሆኑ፣ ሊባኖስ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አንፃር በአገሪቱ የሚገኙ ዜጎችን መመለስ ቅድሚያ እንደተሰጠው ታውቋል፡፡ በሊባኖስ ከሚገኙ ዜጎች ውስጥ ይበልጥ ለችግር የተጋለጡት ተመርጠው ወደ አገር መመለሳቸውንና ከተመለሱት ውስጥ ስምንት ሕፃናት እንዳሉበት አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...