Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናተመራቂ የጤና ባለሙያዎች በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መዋጮ ደመወዝ ሊቀጠሩ ነው

ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መዋጮ ደመወዝ ሊቀጠሩ ነው

ቀን:

የጤና ሚኒስቴር፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ለጤና ባለሙያዎች የሚከፈልን የደመወዝ ወጪ እየተጋሩ፣ አዳዲስ ምሩቃን የጤና ባለሙያዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ በቅጥር ወደ ሥራ የሚያስገባበትን ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡

ሚኒስቴሩ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ይኼንን አሠራር ለመተግበር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ፣ ታኅሳስ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የተፈራረሙ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ደረጃ ወጪውን ከሚጋራው የገንዘብ ሚኒስቴርና ለፕሮጀክቱ ትግበራ የገንዘብ ድጋፍ ካደረገው ‹‹በፌት›› የተሰኘ ፋውንዴሽን ጋር ተመሳሳይ ስምምነት መደረጉ ተገልጿል፡፡

እስከ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የጤና ሚኒስቴር ተመራቂ የጤና ባለሙያዎችን በመቀበል፣ በመላ የአገሪቱ ክፍሎች ምደባ ያከናውን የነበረ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ ይኼንን አሠራር ካስቀረ በኋላ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የጤና ተቋማት ማስታወቂያ እያወጡ በራሳቸው እንዲቀጥሩ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁንና በበጀት እጥረት ምክንያት አስተዳደርና ተቋማቱ የሚፈለገውን ያህል የጤና ባለሙያ መቅጠር እንዳልቻሉ ለሪፖርተር የተናገሩት የሚኒስቴሩ የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ደምሴ፣ ይኼም ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች እንዲጉላሉና ሥራ አጥ እንዲሆኑ እንዳደረገ አስረድተዋል፡፡ ተመራቂ የጤና ባለሙያዎችም በጤና ዘርፉ ላይ የባለሙያ እጥረት እያለ ሥራ አጥ መሆናቸውን በማማረር ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡

አሁን ሚኒስቴሩ ይፋ ያደረገው የወጪ መጋራት ፕሮጀክት፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ላይ የተጣለውን የደመወዝ ክፍያ ወጪ የፌዴራል መንግሥቱ እንዲጋራው በማድረግ፣ በበጀት እጥረት ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ያለመ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፣ የጤና ሚኒስቴር ከአጋር የልማት ድርጅቶች ሀብት ሲያሰባስብ የገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ የተሰበሰበውን ገንዘብ መጠን ያህል ያዋጣል፡፡

በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዓመት ላይ ጤና ሚኒስቴር ባገኘው ዕርዳታ አማካይነት፣ የጤና ባለሙያዎችን 50 በመቶ ደመወዝ ሲከፍል፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ቀሪውን ግማሽ ይሸፍናል፡፡ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች በመጀመሪያው ዓመት ላይ ያለባቸው ግዴታ የባለሙያዎችን ጥቅማ ጥቅም መክፈል ብቻ ይሆናል፡፡

በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች በፕሮጀክቱ አማካይነት የሚቀጠሩ አዲስ የጤና ባለሙያዎች፣ ደመወዝ በየቅደም ተከተሉ 25 እና 50 በመቶ ይከፍላሉ፡፡ በአራተኛው ዓመት ላይ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ደወመዝ ወጪን በመክፈል ባለሙያዎቹን ቋሚ አድርገው ይቀጥላሉ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ይኼንን ፕሮጀክት በመተግበር የጤና ባለሙያዎችን የደመወዝ ወጪ ቀስ በቀስ ወደ ክልልና ከተማ አስተዳደሮች በማዞር፣ በአንድ ጊዜ ለመቅጠር በሚሞክሩ ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ችግር የማቃለል ዕቅድ አለው፡፡ ምንም እንኳን ይኼ ፕሮጀክት ይፋ ቢደረግም አስተዳደሮቹ ከዚህ በፊት ሲያከናውኑት የነበረው መደበኛ ቅጥር ባለበት እንደሚቀጥል አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዚህ ዓመት 2,900 ያህል ተመራቂ የጤና ባለሙያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በሚቆይባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ ከስድስት ሺሕ በላይ ባለሙያዎች ይቀጠራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሚኒስቴሩን ወክለው ከክልልና ከተማ ጤና ቢሮዎች ጋር የተፈራረሙት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የፕሮጀክቱን የዚህ ዓመት ወጪ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ለተጋራው በፌት ፋውንዴሽ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ በዚህ ዓመት 175 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከዚሁ እኩል በማዋጣት የዓመቱን በጀት ወደ 350 ሚሊዮን ብር አሳድጎታል፡፡ በፌት ፋውንዴሽ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በተመሳሳይ መልኩ የጤና ባለሙያዎቹን ደመወዝ በእኩል ለእኩል የወጪ መጋራት ስምምነት እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

አቶ ሀብታሙ እንደሚያስረዱት ፕሮጀክቱ በሚቆይባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ የሚያወጣው ወጪ የሚወሰነው የጤና ሚኒስቴር ማሰባሰብ በሚችለው ዕርዳታ ልክ ነው፡፡ ለዚሁ ዓላማ ተብሎ የተከፈተ ልዩ አካውንት መኖሩ የገለጸ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ወደ አካውንቱ ውስጥ የገባውን ገንዘብ ያህል ፈንድ ያደርጋል፡፡

‹‹በዕርዳታ መልክ የምናገኘው ገንዘብ ባደገ ቁጥር የፌዴራል መንግሥቱም መዋጮ ስለሚያድግ ወደ ሥራ የምናስገባቸው የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ይጨምራል›› ያሉት ዳይሬክተሩ የጤና ሚኒስቴር ተጨማሪ በጀት ለማግኘት ለተለያዩ አጋር የልማት ድርጅቶች ጥያቄ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሚኒስቴሩ ከዚህ በፊት በጤና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ተማሪ የጤና ባለሙያዎችን የደመወዝ ወጪ ከክልልና ከተማ አስተዳደሮች ላይ አንስቶ ወጪውን ለተጨማሪ ባለሙያዎች ቅጥር እንዲያውሉት ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ ዶ/ር ሊያ ‹‹የጤና ቢሮ ኃላፊዎች በፕሮጀክቱ ሁለተኛ ዓመት በክልላችሁ በጀት እንዲያዝለት በካቢኔ ውስጥ ይኼንን ጉዳይ አስይዛችሁ እንደምታስቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት የሚቀጠሩት የጤና ባለሙያዎች የእናቶችና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ለወደሙ ተቋማት መልሶ ማቋቋም የሚመደቡ የጤና ባለሙያዎች እንደሚኖሩም ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...