Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የተቀናጀ የጭነት አገልግሎት ማስተዳደሪያ የትራንስፖርት ሥርዓት ወደ ዲጂታል ተቀየረ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተቀናጀ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ማስተዳደሪያ ሥርዓትን ወደ ዲጂታል ቀየረ፡፡

  ከዚህ ቀደም በነበረው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣንና በሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ሲሰጡ የነበሩ አምስት የማስተዳደሪያ ሥርዓት አገልግሎቶች፣ ከዓርብ ታኅሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹የተቀናጀ የጭነት ማስተዳደሪያ ትራንስፖርት ሥርዓት›› የሚል ስያሜ በተሰጠው የዲጂታል አገልግሎት ተለውጠዋል፡፡

   የቀረበው አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከዚህ ቀደም ተጠሪ ተቋሙ በነበረው የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች አማካይነት ተቀርፆ፣ የተቀናጀ የጭነት ትራንስፖርት ማስተዳደሪያ ሥርዓት እንደሆነ ተገልጿል።

  በትራንስፖርት ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ግለሰቦችና ባለሀብቶች አዲስ የትራንስፖርት ብቃት ማረጋገጫ፣ ዓመታዊ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ዕድሳት፣ የአዲስ ተሽከርካሪዎች ምዝገባ፣ የተሽከርካሪ ዝውውር፣ ወደ ጎረቤት አገር የንግድ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች የድንበር ተሻጋሪ መታወቂያ ማውጣት፣ ማደስና ምትክ መስጠት አገልግሎቶች በበይነ መረብ ሥርዓቱ መሰጠት ጀምረዋል፡፡

  ተገልጋዮች ያላቸውን አስፈላጊ ሰነዶች ስካን በማድረግ አገልግሎቱን በቀላሉ መጠቀም የሚችሉ ሲሆን፣ የተቀናጀ አገልግሎቱን ለማበልፀግ አንድ ዓመት ተኩል የፈጀ ጊዜ ጠይቋል፡፡

  በ2013 ዓ.ም. ብቻ 72,000 ለሚሆኑ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ወደ ጎረቤት አገር እንዲገቡ የሚያስችላቸውን መታወቂያ ዕድሳትና ፈቃድ ማግኘታቸውን፣ ይህ አገልግሎት ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል እንደሚቀየር ተገልጿል፡፡

  አገልግሎቱ ታኅሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል ይፋ በተደረገበት መድረክ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር / ዳግማዊት ሞገስ፣ የተቀናጀ የጭነት ትራንስፖርት ማስተዳደሪያ ሥርዓቱ በደረቅና ፍሳሽ ማመላለሻ ትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ትርጉም ባለው መንገድ የሚቀይር እንደሆነ አስታውቀዋል።

  ‹‹የትራንስፖርት ዘርፉ ዘመናዊ፣ ብቁና ቀልጣፋ እንዲሆን እየሠራን ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ይፋ የተደረገው ሥርዓት ቀልጣፋና ዘመናዊ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ኦፕሬተሮችን ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።

  / ዳግማዊት እንደገለጹት የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ የገቢና ወጪ ጭነቶችን በማጓጓዝ ረገድ የተሽከርካሪዎች ድርሻ 90 በመቶ በላይ ሲሆን ቀሪው የባቡርና ሌሎች የሎጂስቲክስ አማራጮች ናቸው፡፡

  በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ችግሮች በአሠራር፣ በብቁ የሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በቴክኖሎጂ መቅረፍ ከተቻለ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማድረግ ይቻላል ያሉት በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

  የብራይት ድንበር ተሻጋሪ ደረጃ አንድ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ንጉሴ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ይፋ የተደረገው የተቀናጀ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ የትራንስፖርቱ ዘርፍ አገልግሎቶች ዘመናዊ በሆነ መንገድ እንዲሰጡ የሚያስችል ነው፡፡

  ከዚህ ቀደም የተቀናጀ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለማግኘት ውጣ ውረዶች እንደነበሩ፣ ይህም ዘርፉ ላይ ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ሥራዎች በስፋት ባለመስረፃቸው የተነሳ መሆኑን፣ ከአደረጃጀት የተነሳ አገልግሎቱን በሚያገኙ አካላት ዘንድ ቅሬታዎች እንደነበሩ ያስታወቁት አቶ ሲሳይ፣ ነገር ግን ይፋ የተደረገው አዲስ ሥርዓት ከመተግበሩ በፊት ከዚህ ቀደም የተለያዩ ውይይቶችና አስተያየቶች እንደተደረጉ አስረድተዋል፡፡

  የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ከሚያገኟቸው ወሳኝ አገልግሎቶች መካከል የጂቡቲ መግቢያና፣ የጂቡቲ መግቢያ የተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎች ፈቃድ ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም በዚህ ወቅት በፈረሰው የትራንስፖርት ባለሥልጣን መሥርያ ቤት በኩል ሲሰጡ የነበሩ የዕድሳት ፈቃድ ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ አገልግሎት በአካል በመቅረብ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንደ መሆናቸው መጠን፣ ቢሮክራሲውን ሰብሮ ገብቶ ለ24 ሰዓታት የሚሰጠውን አገልግሎት ማስተዳደር የራሱ የሆኑ ፈተናዎች ነበሩት፡፡ በተለይም በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ለዓብነትም ዓርብ ከቀትር በኋላ ወደ ውጭ የሚሄድ ጭነት ቢኖር፣ እስከ ሰኞ ድረስ አገልግሎቱን ለማግኘት መጠበቅ ግድ ይል ነበር፡፡ ሆኖም በኦንላይን ለ24 ሰዓታት የሚሰጥ አገልግሎት መቅረቡ ከሰው ንክኪ ነፃ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል እንደሆነ ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

   በዚህ ወቅት 98 የድንበር ተሻጋሪ የንግድ ጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ኦፕሬተሮች፣ እንዲሁም 12,700 በላይ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በማኅበርና በድርጅት ዘርፍ ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ፣ እንዲሁም የፈሳሽ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ከ200 በላይ ትራንስፖርተሮችና 3,500 የሚጠጉ የፍሳሽ ማመላለሻ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችም መኖራቸው ታውቋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች