Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየካፍ አዲሱ አሠራርና አሠልጣኞች ሊኖራቸው የሚገባው የብቃት ማረጋገጫ

የካፍ አዲሱ አሠራርና አሠልጣኞች ሊኖራቸው የሚገባው የብቃት ማረጋገጫ

ቀን:

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለስድስት ዓመታት ያህል አቋርጦት የቆየውን የአሠልጣኞች ብቃት ማረጋገጫ (ላይሰንስ) ሥልጠና እንደገና ሊጀምር መሆኑ ታወቀ፡፡ በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያን ጨምሮ የካፍ አባል አገሮች ሥልጠናውን ማግኘት ይችሉ ዘንድ፣ በተለይም ከሥልጠናው ይዘት ጋር ተያይዞ የካፍን ቅርፅ (ፎርማት) እንዲከተል ቅድመ ጥናት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯል፡፡

ካፍ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረውን ሥልጠና ለማቆም የተገደደበት ዋናው ምክንያት፣ ከጥራት ጋር ተያይዞ እንደሆነና በነበረው የሥልጠና ሒደት ብቃት ያላቸው አፍሪካዊ አሠልጣኞች ለማፍራት፣ እንዲሁም የአፍሪካን እግር ኳስ ከተቀረው ዓለም ጋር ተፎካካሪ ለማድረግ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡

 በኢትዮጵያ ቀደም ሲል በነበረው የሥልጠና አካሄድ ወደ ሦስት ሺሕ ለሚጠጉ አሠልጣኞች ከ‹‹ሲ›› እስከ ‹‹ኤ›› ደረጃ የብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና እንደተሰጠ ከብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ በአሁኑ ወቅት ሥልጠናውን ወስደው ካፍ የሚያውቀው የብቃት ማረጋገጫ (ላይሰንስ) ያላቸው ሙያተኞች ቁጥር ከ60 አይበልጥም፡፡

ከሥልጠና ጋር ተያይዞ የነበረው ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም የአፍሪካ አገሮች በመሆኑ፣ ሲሰጥ የቆየው የሥልጠና አካሄድ ዳግም እንዲታይ ያደረገውም ለዚህ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል፡፡

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ እንደሚገልጹት፣ ካፍ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሁሉም አባል አገሮች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና የመቋረጡ መሠረታዊ ምክንያት ከጥራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ከሥልጠናው ዓይነትና ይዘት፣ ጥራቱን ጭምር በመጠበቅ መስጠት እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡ እንዲሁም የአሠለጣጠኑ ቅደም ተከተልን ጭምር በማሻሻል ይህንኑ ለእያንዳንዱ አባል አገሮች በመላክ ሥልጠናው እንደገና እንዲጀመር ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተሻሻለውን የካፍ ቅድመ ሁኔታዎች ካሟሉ  የአፍሪካ አገሮች አንዷ መሆኗን የሚናገሩት የቴክኒክ ዳይሬክተሩ፣ የካፍ ቅድመ ሁኔታን መነሻ በማድረግ፣ አሁን ላይ የ‹‹ዲ›› ላይሰንስ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከ‹‹ሲ›› እስከ ‹‹ኤ›› ያለውን ሥልጠናን በተመለከተም ፌዴሬሽኑ የሚሠለጥኑትንና ኢንስትራክተሮቹን የመለየት፣ እንዲሁም የኮርስ ዓይነቱን  የካፍን የሥልጠና ማንዋል መነሻ በማድረግ ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡  

ኮርሱ የሚወስደውን የጊዜ ሁኔታ በተመለከተ ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፣ ቀደም ሲል የ‹‹ሲ›› ብቃት ማረጋገጫ ለመውሰድ ከ15 እስከ 20 ቀን የነበረው በአዲሱ አሠራር ዝቅተኛው 21 ቀን ሆኖ፣ ነገር ግን ሥልጠናው በፕሮጀክት መልክ ስለሚሰጥ እያንዳንዱ ሠልጣኝ የሚወስደውን የኮርስ ዓይነት ለማጠናቀቅ እስከ 63 ቀናትን ሊወስድም ይችላል፡፡ በዚያ ላይ እያንዳንዱ ሥልጠና ሲጀመርም ሆነ ሲጠናቀቅ ፊፋና ካፍ ይከታተሉታል፡፡  ሥልጠናው ከመጀመሩ ከሦስት ወራት በፊት ፌዴሬሽኑ ለዓለም አቀፉና ለአኅጉር አቀፉ ተቋም የሥልጠናውን ዓይነትና ሁኔታ የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

የራሳቸው የሆነ መለያ (አይዲ) የሚኖራቸው ሠልጣኞች የኮርሱ ዓይነትና ይዘት የሚሰጣቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ካፍ ሥልጠናው በሚጀመርበት ወቅት በአግባቡ የሚካሄድ መሆኑን ድንገተኛ የሆነ ገምጋሚ ቡድን በመላክ የሚከታተል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሥልጠናውን የሚሰጡ ስምንት ኢንስትራክተሮች እንዳሉ ቢነገርም፣ ካፍ አዲስ ለሚከተለው ሥልጠና ብቁ የሆኑት ሁለት ብቻ እንደሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ቢያንስ በአሁኑ ወቅት 15 ያህል ኢንስትራክተሮች ሊኖሯት እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፣ የኢንስትራክተሮችን ውስንነት አስመልክቶ ችግሩ እንዳለ አምነው፣ ነገር ግን ካፍ ችግሩን ከግምት አስገብቶ ያሉት ኢንስትራክተሮች ብቁ ሆነው ሥልጠና እንዲሰጡ ለማድረግ ፌዴሬሽኑ እየጣረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ቀደም ሲል ሥልጠና ለመውሰድ የተሳታፊ ቁጥር ገደብ እንዳልነበረ የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፣ በአዲሱና በተሻሻለው አሠራር ግን ለእያንዳንዱ ሥልጠና ማለትም የ‹‹ዲ›› ብቃት ማረጋገጫ  መውሰድ የሚችሉት ሠልጣኞች ቁጥር 30 ሲሆን፣ ለ‹‹ሲ›› በተመሳሳይ 30፣ ለ‹‹ቢ›› 25 እና ለ‹‹ኤ›› 20 ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡ ይህ ካፍ ለጥራት ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀስ እንደሆነ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ እንደሌለ በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡

ዳይሬክተሩ ቁጥራቸው 10 የሚደርስ የጎረቤት አገር ሙያተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጠና ለመውሰድ ፍላጎት እንዳላቸውም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በፕሮፌሽናል ደረጃ እግር ኳስ የተጫወቱ በሥልጠናው ለመሳተፍ ፍላጎቱ ካላቸው የ‹‹ዲ›› እና የ‹‹ሲ›› ደረጃዎችን ዘለው ቀጥታ የ‹‹ቢ›› ደረጃን መውሰድ እንደሚችሉ ካፍ አጭር (ፋስት ትራክ) የሚባል አሠራር ማመቻቸቱን የሚናሩት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህ ጉዳይ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ተጫውተው ‹‹ያለፉ›› እና ‹‹ያላለፉ›› በሚል ትልቅ ክርክር ሲያስነሳ መቆየቱ ጭምር ያስታውሳሉ፡፡ ካፍ በአዲሱ አሠራር መሠረት ‹‹ዲ›› ለመውሰድ 60 ሰዓት፣ ለ‹‹ሲ›› 120 ሰዓት፣ ለ‹‹ቢ›› 180 ሰዓትና ለ‹‹ኤ›› 240 ሰዓት ማሟላት እንደሚያስፈልግና  ከ‹‹ሲ›› ወደ ‹‹ቢ›› አሊያም ወደ ‹‹ኤ›› ለመሸጋገር ደግሞ በሥራው ላይ ቆይታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጭምር ተናግረዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...