Saturday, February 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን፣ ‹‹በቀላሉ ማስረዳት ካቃተህ ጉዳዩ አልገባህም ማለት ነው…›› ብሏል ተብሎ የሚጠቀስለት አባባል ለእኛ የተጠቀሰ ይመስለኛል፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አንደኛ ዓመት ሲዘከር፣ በወቅቱ ባለሥልጣኖቻችን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኳስ ሜዳ ገብተው ሲጫወቱ ማየታችን አይረሳም፡፡ እኛ ተራ ዜጎች የምንደሰትበት ነገር እነሱንም እንደሚያስደስታቸው ሁሉ፣ ለሚያስከፋን ነገር ደግሞ ጀርባ መስጠታቸው አናዶኝም ነበር፡፡ በአገራችን ተርታው ዜጋና ባለሥልጣናቱ የተራራቁ ስለሆኑ እንዲህ ዓይነት ፍላጎቶችን ለመረዳት ይከብዳል ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስት ሁላችንም ያለፍንበት መንገድ በአመዛኙ ተመሳሳይ ነውና፡፡ ለማንኛውም አቀማመጣችን ባይራራቅምና ፍላጎታችን ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ሊያግባቡን ሲችሉ የሚያጣሉን መብዛታቸው ይገርመኝ ነበር፡፡ ወደ ጉዳዩ ልመለስና የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በተመለከተ በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የምሰማቸው ነገሮች አናዳጅ ነበሩ፡፡

የአገሪቱ ዋና ቴሌቪዥን ከግድቡ ጋር በተያያዘ እየተካሄዱ ያሉ ሥራዎችን ከቦታው ላይ ሆኖ ካቀረበልን ዘገባ በኋላ፣ ወዲያው የዓባይን ጉዳይ ተረት ያስመስለዋል፡፡ ዓባይን ከጂኦ ፖለቲካዊ፣ ከፍትሐዊ ክፍፍል ተጠቃሚነት፣ ሰፋ ካለው ዲፕሎማሲያዊ ምልከታ፣ ከተፋሰስ አገሮች ስሜት፣ ከብሔራዊ ፖሊሲያችን፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጥልቅ ፍላጎት፣ ወዘተ አንፃር ትልቅ ሥራ ይዞ ይቀርባል ሲባል እያልኮሰኮሰ የመንደር ወሬ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ያንን የሰለቸንን ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው…›› ስንክሳርና እሮሮ ይቀጥላል፡፡ እንደ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ የሚቀርብ ታላቅ ጉዳይ ትልቁ ምሥል ጠፍቶበት እንቶ ፈንቶ ሆኖ ይቀራል፡፡ ለካ በወቅቱ የወያኔ ሰዎች ሆን ብለው ነበር ትልቁን ጉዳይ አንሶ እንዲታይ የሚፈልጉት፡፡

በዚያን ዘመን ሬዲዮኖቹን ስትከፍቱ እንደ በቀቀን አንድ ዓይነት ተረት ሲዘበዝቡ ትሰማላችሁ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ልሂቃን፣ አዛውንቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ ሙያተኞች፣ ወዘተ እያሉ የሠፈር ልጆች ወሬ ያደርጉታል፡፡ ከዜና ባለፈ መነገር ያለባቸው እንደ ዋርካ የገዘፉ ነገሮች ተረስተው እንደ እምቧጮ ያነሱ ወጎች አየሩን ይሞሉታል፡፡ ለዘፈንና ለዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ክንውኖች ላባቸውን ጠብ እያደረጉ የአድማጮቻቸውን ጆሮ ለመያዝ ሲባዝኑ የሚውሉት ጣቢያዎች፣ ታላቁን ጉዳይ ተቀጥላ አድርገው ያሽመደምዱታል፡፡ ይህም የወያኔዎች ሴራ እንደነበር የሰማነው ዘግይቶ ነው፡፡

እኔ በወቅቱ የምታዘበው ነገር አናዳጅ ሆኖብኝ ብቆጭም፣ አንዳንዴ ቁጭ ብዬ ሳስበው መንግሥት የሚዲያዎቹ ባለቤት ያልሆነ ይመስል በአገር ላይ ማላገጡ የተቀነባበረ ሴራ ነበረው፡፡ እሱ የሚፈልገው ጉዳይ፣ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዓይነት ሆኖ ከቀረበለት በኋላ ስለሌላው ጉዳይ የሚመለከተውም አይመስልም፡፡ ወኪሎቼ ብሎ ያስቀመጣቸውም ሥራቸው ሕዝቡን ማደንዘዝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሕፃናት ሳይቀሩ የሚሳተፉባቸው አንዳንድ ፕሮግራሞች እኮ እዚህ አገር የተሠሩ አይመስሉም፡፡ እንጨት እንጨት የሚሉ ዜናዎችና ሐተታዎች ካበቁ በኋላ የሰውን ጆሮ የሚያስቆሙና ዓይንን የሚያስፈጥጡ በርካታ ድሪቶ ነገሮችም ነበሩ፡፡ እርግጥ ነው ዛሬም አሉ፡፡

በመግቢያዬ ላይ የአልበርት አንስታይንን ጥቅስ ያመጣሁትም ለዚህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እጅግ አስገራሚና አስደንጋጭ የሆኑ ግለሰቦች በእንግድነት ወይም በስልክ አሳብረው ይገቡና ከባህላችን፣ ከልማዳችንና ከጠቅላላው አኗኗራችን ውጪ የሆነ ግራ አጋቢ ነገሮችን ይናገራሉ፡፡ ፕሮግራሞቹን የሚያስፈጽሙ ግለሰቦች ደግሞ ‹‹አዲስ ግኝት›› ብቅ ያለ ይመስል ራሳቸውን እዚያ ውስጥ ይዘፍቁና አድማጮችን ያዋክባሉ፡፡ ስለማናውቀው ወይም በበቂ ሁኔታ መረጃው ስለሌለን ነገር ውይይት ለመክፈት ምን እንደሚያጣድፍም ግራ ያጋባል፡፡ ይህንን ደግሞ በስፖርት፣ በልጆች፣ በሴቶች፣ በሥነ ፆታ፣ ወዘተ ውይይቶች ላይ በሰፊው እንሰማለን፡፡

አሁን ችግሩ ያለው አልበርት አንስታይን እንዳለው ማስረዳት ብቻ ሳይሆን፣ ስለምንነጋገረው ጉዳይ አለማወቅ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በሬዲዮ ጥያቄና መልስ ፕሮግራም ላይ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የት እንደ ዘመተች ጠያቂው ጥያቄ ያቀርባል፡፡ አንድ ጎበዝ መላሽ፣ ‹‹ከቅርቡ ልጀምርልህና አቢዬ፣ ዳርፉር፣ ላይቤሪያ፣ ብሩንዲና ሩዋንዳ…›› ብሎት፣ ‹‹ከሩቁ ደግሞ ኮንጎና ኮሪያ አሉልህ…›› ሲለው፣ የሬዲዮው ጠያቂ፣ ‹‹የመጀመሪያዎቹን ልክ ብለሃል ስለሁለቱ ግን መረጃ የለንም…›› ሲል ታክሲ ውስጥ ሆነን ስናዳምጥ የነበርን አንጋፋዎች በድንጋጤ ተኮማተርን፡፡ ልብ በሉ ኢትዮጵያ በሰላም አስከባሪነት የፈጸመችው ገድል እየተወሳ በነበረበት ሳምንት ውስጥ ነው እንዲህ ዓይነት ጉድ ገጥሞን የነበረው፡፡

ወደ ህዳሴ ግድብ ልመልሳችሁና ትልቁን አገራዊ ምሥል እያሳነሱ ትንንሽ ሲያደርጉብን የነበሩ ሰዎች ናቸው እንግዲህ ዘረፋ ሲያካሂዱበት የነበረው፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያ ቁርጥ ቀን ልጆች እንዲመሩት ከተደረገ ወዲህ በርካታ ሥራዎች ተከናውነው፣ አሁን የተወሰኑ ተርባይኖች ኃይል ለማመንጨት ተዘጋጅተዋል፡፡ ዘራፊዎቹ ግን የእነ ግብፅ ተላላኪ ሆነው አገር ለማፍረስ ተነስተው ጦርነት ውስጥ ነበር የከተቱን፡፡ የግድቡን ገንዘብ ሲዘርፉ ኖረው ሲባረሩ ግድቡ ሊሸጥ ነው ብለው ሲያስወሩ የነበሩ ከንቱዎች አሁን ኃይል ለማመንጨት ዝግጁ ሲሆን ምን እንደሚሉ ባይታወቅም፣ ሌላ ማደናገሪያ ይዘው እንደሚቀርቡ ግን የታወቀ ነው፡፡ የእኛ መልስ መሆን ያለበት ግድባችን ብርሃን ሊሰጥ ስለሆነ ጨለማ ውስጥ ሆናችሁ አትረብሹ ማለት ነው፡፡ ሌባ የሚወደው ጨለማ ስለሆነ እውነትና ብርሃን ፊት መቅረብ አይችልም፡፡ አንስታይን እንዳለው እነሱ ካልገባቸው፣ እኛ የእነሱ አጥፊ ድርጊቶች በሚገባ ስለገቡን ሥራ ላይ ነን ለማለት ነው፡፡ 

(መሃረነ ገድለ ጊዮርጊስ፣ ከዘነበወርቅ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ

የፌዴራል መንግሥትና የህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር...

ማስተካከያ

በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም...

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...