Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየእልህ ፖለቲካና ብልጭ ያለው የዴሞክራሲ ዕጣ ፈንታ!

የእልህ ፖለቲካና ብልጭ ያለው የዴሞክራሲ ዕጣ ፈንታ!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

አለመደማመጥ አለመግባባትን ይወልዳል፡፡ ‹‹እኔ ብቻ ልወቅልህ፣ ልወስን››፣ ‹‹ከእኔ በላይ ላሳር›› ባይነትም እልህና ግጭትን ይወልዳል፡፡ በእርግጥ ዓለም የባለፀጎችና የጉልበተኞች እንጂ ለእውነት፣ ለፍትሕና ለሕዝብ የቆሙ ሁሉ የአገር አደራ የሚረከቡባት እንዳልሆበች ይታወቃል፡፡ ሕዝብ ግን  አንድ ጊዜ ተሞክረው የወደቁትን ከመመለስ ምንጊዜም አዲስ መመኘቱ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይህ ምድራዊ ሀቅ ደግሞ ከአፅናፍ አፅናፍ ሲከናወን የታየ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በእኛም አገር ለዘመናት የተሠራበት መሆኑ በታሪክ ተመዝግቦ የኖረ ነው፡፡

1983 .. በፊት በአገራችን ሌላው ቀርቶ ፓርቲ ማቋቋም በራሱ ከባድ ወንጀል እንደነበር ይታወቃል። በዚህ የተነሳ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብ 1983 .. በፊት ለነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባዳ ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ የተደራጀና ተቋማዊ ተቃውሞን ማስተናገድ ለቅድመ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ልሂቃን የማይታሰብ የሆነበት አምባገነናዊ ሥርዓቶች ስለኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ በእርስ በርስ ሽኩቻና በፖለቲካ ትግል ሰበብ ብዙዎች ሰለባ ስለነበሩም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      እናም ሕወሓት/ኢሕአዴግ የደርግን ሥርዓት አስወግዶ ሥልጣኑን ሲያደላድል ስለዴሞክራሲና መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተስፋ ያደረጉ ብዙዎች ነበሩ፡፡ እንኳንስ የአገሩ ዜጎች  ምዕራባዊያንና አንዳንድ አጋር አካላትም ቀድመው ማመሥገን ነበር የጀመሩት፡፡ ይህን ሥርዓት በመዘርጋት ሒደት የመጀመርያዎቹ  ዓመታት በአገራችን የፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ላይ ከባድ ልዩነትና ተጠራጣሪነት ሰፍኖ የነበረ ቢሆንም፣ ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላ መልሶ ወደ አዘቅት የሚወረድበት መንገድ የተቀየሰው በዚያው ሥርዓት መሪዎች መሆኑ ሲታይ ግን አሳዛኙ የታሪካችን ክፍል ሆኗል፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ ገዥው ፓርቲ በኢትዮጵያ ብዙኃነትን ከቀደምት አስተዳደሮች በተለየ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለመያዝና ለማስተዳደር እንደሚፈልግ ቢያሳውቅም፣ በአንድ ፓርቲ (ሕወሓት) የበላይነት ቀይዶ ነበር ሊመራ የሞከረው፡፡ በዚህም ብዙኃኑ ዜጋ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዲታይና እርስ በርሱ እየተናጨ እንዲኖር ዕቅድ ወጥቶ፣ ፈጻሚና አስፈጻሚ ተመድቦለት በመዋቅራዊ አካሄድ ለሁለት አሥርትና ተኩል ዓመታት በላይ ተሠርቶበታል፡፡ ይህም የአገር ተቆርቋሪነት እዲኮሰምን፣ ዘረፋና ኢፍትሐዊነት እዲበረታ፣ አፈናና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እንዲነግሥ ወደ ማድረግ ደርሶ ነበር፡፡

ለአብነት ያክል በማንኛውም ነፃ አዕምሮ ባለው ሰው እምነት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማጠናከር፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እጅግ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑ ግልጽ ነበር፡፡ የእነሱ መኖር በርካታ አዳዲስና ተጨማሪ የአገር ዕድገት ግብዓቶችን ይዞ ይመጣል፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ግን ተገዳዳሪዎቹን በማጥፋት፣ በማሳደድና በማሰር ላይ ከማተኮር አልፎ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ማራመድ ክፉኛ ዋጋ የሚያስከፍል ተግባር አድርጎት ነበር፡፡ እናም ወደ ሥርዓቱ ዕድሜ መጨረሻ ገደማ በውስጥ ያለ ደጋፊ አይባል፣ ተቃዋሚ፣ እስከ ውጭ ያለው ተዋናይ ድረስ በአንድ ተሠልፎ ሊረባረብበት በቅቷል፡፡

በመሠረቱ ዛሬም ሆነ ነገ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ሊንቀሳቀሱ የሚገባቸው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ሊሆን ግድ ነው፡፡ ትናንት እንደ ታለፈው ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም አገሪቱን እንደ ገጠማት ባለው የእልህ ፖለቲካና ግጭት ጠብ የሚል ውጤት ማግኘት ከንቱ ድካም ነው፡፡ በሠለጠነው ዓለም እንደሚታየው ከፓርቲዎች የተተነተነ፣ በሥርዓት የተደራጀና የተሻለ አማራጭ ለማግኘት የሚሻው ሕዝብም ሊጠቀም አይችልም፡፡ ፀብ ብቻ አይደለም በምድር በሰማይም የመከራ በር ከፋች ነው፡፡

 እንደ ፖለቲካ ጉዞ ስናየው ደግሞ በሰላምና በሠለጠነ መንገድ መራመድ ከሌለ፣ የተሻሉ የፖሊሲ አማራጮችን ማመንጨት አይቻልም፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅም የሚሞከር አይደለም፡፡ ምሁራንና ብዙኃኑ ልሂቃን አማራጭ ሐሳቦችን በማመንጨት ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ሐሳቦች በኅብረተሰቡም ሆነ በአጠቃላይ ሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ለመሥራትም አያስችልም፡፡ መካረሩና አለመደማመጡ አሁን እንደ ደረስንበት ወደ ለየለት ጦርነት ሲያድግም የለማውም ይፈርሳል፣ አገር ይጠፋል፣ ሕዝብ ለመከራና ለስቃይ ይዳረጋል፡፡

ይህን ሁሉ እንደ መግቢያ ለማንሳት የተሞከረው እርሾው ኢሕአዴግ የሆነው የአገራችን አብዛኛው የፖለቲካ ኃይል በዴሞክራሲና በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየማለ፣ ስለፍትሕና እኩልነት እየተገዘተ ቢቆይም ሥልጣኑን ያውም በሕዝብ ፍላጎት ወደ ሌላ ወገን ያካፈለ ሲመስለው ወደ ለየለት ጦርነት ሲገባ በማየታችን ነው፡፡ ይህ የተከሰተውም ሥርዓቱ ሥልጣንን ለአንድ ወገን መጠቀሚያ፣ ሕዝብን ለመበዝበዣና ላልተጋባ ዓላማ ማዋያ ከማድረግ ባሻገር፣ ዴሞክራሲያዊነትና ተጠያቂነት የነጠፈበት አካሄድ ተንሰራፍቶ በመቆየቱ ነው፡፡

ከሁሉ በላይ ኢሕአዴግን በግንባር ቀደምንት ሲመራ የነበረው ሕወሓት በተጨባጭ ከአራት ዓመት በፊት ገፍቶ የመጣውን አገራዊ ለውጥ በኃይል ጨፍልቆ ለማለፍ ሞክሮ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ባዶ እጃቸውን የመብት ጥያቄ ባነሱ ንፁኃን ላይ የወሰደውን ዕርምጃ መዘንጋት አይቻልም፡፡ ይካሄድ የነበረው ፀረ ዴሞክራሲያዊና ፅንፈኛ ዕርምጃ ረጅም ርቀት እንደማይወስድ የተረዳው ቀሪው የኢሕአዴግ ኃይል፣ በውስጥ ተሃድሶ ስም በሠለጠነ መንገድ ማሻሻያ ለማድረግ ሲሞክርም፣ አንዱ ክንፍ ከእልህ መንገድ አለመወጣቱ ነው የዛሬውን ቀን ያመጣው፡፡

አለመታደል ሆኖብን እንጂ ከአራት ዓመታት ወዲህ በአገራችን የመጣው የለውጥ ተስፋ እየወደቀ እየተነሳ ለሦስት አሥርት ዓመታት የተጓዘውን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ሊያጠናክር የሚችል መሆን ነበረበት፡፡ ቢያንስ ‹‹በሕዝቦች መስዋዕትነት የተገኘ ድል›› መሪዎች የሆኑት ኢሕአዴጋዊያን ያውም ከውጭ በማይባል የውስጥ አብላጫ ድምፅ ያሸነፈውን የለውጥ መሻት፣ በሥርዓትና በሠለጠነ መንገድ ነገሮችን በዘዴና በብልኃት፣ በመቻቻልና በመግባባት፣ በዴሞክራሲ አግባብና በሰላም መፍታት አለመቻላቸው የታሪካቸው ውርደት ሆኖ የሚመዘገበውም ለዚሁ ነው፡፡ ለዚህም ከሕወሓት በላይ ቀድሞ ተወቃሽ ሊኖር አይችልም፡፡

የአገሪቱን አጠቃላይ ዕድገትና ልማት ለማፋጠንና ለማስቀጠል በሚያስችል አግባብ ችግሮችን በሠለጠነ አካሄድ እየፈቱ የመሄድን በር የዘጋው ይኼው ዴሞክራሲን በተግባር የማያውቀው ኃይል ነው፡፡ በሚለው ጭብጥ ላይ ልዩነቱ የበዛ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ለሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ የመጣበትን የተቃርኖ ፖለቲካ ሳያስተካክል፣ በማንነትና ዘውግ ላይ መንጠልጠልን ትንሽም ቢሆን ሳያረግብ፣ ከታሪክና ከነባራዊው ሁኔታ እየተጣላ፣ በተዳከመ አገረ መንግሥት ለመቀጠል መመኘቱ የውድቀቱ ሁሉ መነሻዎች ናቸው፡፡

ከሁሉ በላይ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም በመሻት በሴራና ሽኩቻ የተሞላው ዘር ተኮር ፖለቲካ እዚህም እዚያም እንዲራመድና እንዲባባስ  ዳግም መፍቀድ፣ አገሪቱ ከነበረችበት በባሰ አዘቅት ላይ እየጣላት ነበር፡፡ በሐዘንም ሆነ በደስታ ወቅት ወይም በሆነ ምክንያት ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ በማናቆር ወደ ፍጀት ሲወስዱትም ታይቷል፡፡ በመጨረሻ አሁን በምንገኝብት የእርስ በርስ ጦርነት ራሳቸው በቀጥታ የተሳተፉባቸው የዘር ፍጅቶች እስከ መፈጸም መድረሳቸው ምን ያህል ከሕዝብ የራቁና ካልበላሁት ልድፋው ባዮች መሆናቸውን በገቢር አስመስክረዋል፡፡

ይህ አካሄዳቸውም እንኳንስ በዴሞክራሲ የሚምል ፓርቲ ይፈጽመዋል ተብሎ ሊታሰብ ይቅርና ከዘመናት በፊት የነበሩ አምባገነኖችና ኋላቀሮች አላደረጉትም፡፡ እውነት ለመናገር በቀጥታ አባባል እንተቸው ብንል የጨቅላነት በሽታ (Infantile Disorder) የሚያሳይ ኃላፊነት የማይሰማቸው ስግብግቦች ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም የእርስ በርስ ፉክክርን ወደ ሽኩቻና እልህ ወስዶ አገርን መማገድ፣ ሕዝብን ማሳቀቅና ማዋረድ ምንም ተባለ ምንም  በራስ ላይ የቀረበ የእጅ ከፍንጅ ወንጀል ማስረጃ ነው፡፡ በዚህም ታሪክ ፍርዱን የሚሰጥ ሆኗል፡፡

እውነት ለመናገር ሕወሓት/ኢሕአዴግ ከአራት ዓመታት በፊት ተሸንፏል (ራሳቸው የድርጅቱ መሥራች ታጋይና አሁን በማረሚያ ቤት ያሉት ዓቦይ ስብሃት የሞትነው ከዓመታት በፊት ነው አሁን ቀብራችን እየተፈጸመ ነው እንዳሉት)፡፡ ይህ ደግሞ የመኖርና አለመኖር አልፋና ኦሜጋ ክስተት አልነበረም፡፡ እንደ ተጀመረው ሁሉንም የለውጥ ገጽታዎች በመነጋገርና በመደማመጥ፣ በትዕግሥትና በሰጥቶ መቀበል፣ በእኩልነትና በፍትሕ ዕሳቤ ማስቀጠል ቢቻል ኖሮ በምንም ተዓምር አሁን የደረሰውን አገራዊ ኪሳራ ያህል ጉዳት ባልደረሰ ነበር፡፡ የመጭው ጊዜ አገራዊ ዕጣ ፈንታችንም ቅርቃር ውስጥ የገባ ባልመሰለ ነበር፡፡

በመሠረቱ አሁን በምንገኝበት ዘመን በየትኛውም የምድር ክፍል ቢሆን ሥልጣን በድንጋይ ውርወራ፣ በሁከትና በአመፅ፣ በውዥንብር ብዛት የሚነጠቅበት ዘመን አልፏል፡፡ እንዲህ ያለ ዕብሪትና የግጭት ዕሳቤ ለጊዜው መሪዎችን ከሥልጣን ቢወርድም፣ ዘላቂ ሰላምና የአገር መረጋጋትን ማምጣት አይችልም፡፡ አገር በጩኸት የምትፈርስበት ታሪክም ከኢያሪኮ ጋር አብሮ አክትሟል፡፡ ይህን በውል ይረዱታል የሚባሉት የትናንት የአገሪቱ መሪዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ዳግም የራሴ የሚሉትን ሕዝብ ወደ አዘቀት እንዲወርድ የፈረዱበት፣ ያሳዝናል፡፡

 ወደድነውም ጠላነውም ያለንበት ዘመን ዓለም የሠለጠነበትና ችግሮች ሁሉ በሠለጠነ መንገድ የሚፈቱበት ዘመን ነው፡፡ እውነተኛ የመንግሥት ሥልጣን የሚገኘውም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው፣ በድርድር ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ፓርቲ እምነቱና የውስጥ አሠራሩ ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የመገንባትና የመምራት አቅም የሌለው በመሆኑ፣ በሕዝብ ድምፅ ዳኝነት ለመገዛት ፈቃደኛና ዝግጁ አለመሆኑን በተግባር ያሳየን ሕወሓት ካለማቅማማት በሁሉም ኃይሎች መወገዝ ያለበትም ለዚሁ ነው፡፡ ዳግም ወደ ኃይልና እልህ የኪሳራ መንገድ አገርን ከትቷልና፡፡

እዚህ ላይ ግጭቱ ወደ ሁለት በተሰነጠቁት የቀድሞው የኢሕአዴግ ኃይሎች  መካከል ስለሆነ፣ ዓለምን አንዱ ወገን ብቻ ይወቀሳል ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ታሪክ የቅርብ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የልባችን ትርታ ያህል ስንከታተለው እንደቆየነው አኩራፊው፣ የግጭቱ ጠንሳሽና የእልህ መንገድን በግልጽ የጀመረው ሕወሓት ነበር፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን አገር እየመራ ያለው የለውጥ ኃይል የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ ሁሉንም አኩራፊ ኃይሎች በማሳተፍ፣ የሐሳብ ነፃነትን በመፍቀድ፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር የዕርቅ ዕሳቤን በማራመድ፣ የሕዝቦችን አንድነት በማጠናከር፣ ወዘተ. ተግባራት ላይ ሲያተኩር ኩርፊያ ጀምሮ የነበረው ያው ኃይል ነበር፡፡

ከዚህም በላይ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በሦስት ሰኔዎች አገር ለማተራመስ የሞከረው፣ በየአካባቢው ዘር ተኮር ጥቃት፣ መፈናቀልና የሀብት ውድመት እንዲከሰት በእጅ አዙር ያስተባበረው፣ በሕግ የተከለከለ ምርጫ ያካሄደውና በመጨረሻም የሰሜን ዕዝን በግላጭ በማጥቃት፣ የአገር ክህደት ድርጊት ውስጥ የገባው ሕወሓት መሆኑን መንግሥት በማስረጃ አስረግጦ ሲከስ ተደምጧል፡፡ እነሆ አሁን በምንገኝበት የእልህና የግጭት ፖለቲካ አሉታዊ ውጤት የፈጠረው ጊዜ ላይም የጦርነቱ ተዋናይ ይኼው ኃይል በመሆኑ፣ የአገርን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ሲባል ፍልሚያው ከእሱው ጋር ሆኗል፡፡

በመሠረቱ ምርጫም ይባል የተሃድሶና የለውጥ ጉዞ፣ ኢሕአዴግ አብሮም ይሁን ተሰንጥቆ በምንም መሥፈርት ወደ ግጭትና አገር ማተራመስ ሊገባ የሚችል ፓርቲ አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ በሥር ነቀል አብዮትና ከዚህ ቀደም ለዘመናት በአገራችን እንደለመድናቸው ያሉ የመጠፋፋት የሥልጣን ሽግግሮች ውስጥስ ቢገባ ኖሮ ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ ይችል ነበር? በምንገኝበት አውዳሚ ጦርነት እኮ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀዋል፡፡ የአገር ሀብትና ንብረት አሰቃቂ በሚባል ደረጃ ወድሟል፡፡ የአገር ክብር ተዋርዷል፡፡ ይኼ ደግሞ ከአፈጣጠሩ አንስቶ ዴሞክራሲን በስም እንጂ በገቢር የማያውቀው ሥርዓት ውጤት ነው፡፡ ከዚህ አውጣን ነው ብሎ መነሳት፡፡

 ከባህሩ ዳርቻ ያሉ ሕፃናት ልጆች ባህሩ እየገፋ በሚያመጣላቸው አሸዋ ደስ እያላቸው ሲሠሩ የዋሉትን ቤት፣ በስተመጨረሻ ላይ ደስ እያላቸው አፍርሰው የሚሄዱበት ጨዋታ አላቸው፡፡ ፖለቲካና አገር የመምራት ዕሳቤ ግን የልጆች ጨዋታ አይደለም፡፡ ብዙ ዕውቀት፣ ጉልበት፣ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ወዘተ ወጥቶበት፣ እኛን በመሰሉ ታዳጊ አገሮች ደግሞ ስንትና ስንት መስዋዕትነት ተከፍሎበት የሕዝብ ሥልጣን የሚጨበጥበት ውጤት ነው፡፡ እናም እንደ አሸዋ ቤት በቀላሉ የሚፈርስ ዕሳቤና ተግባር መሆን አልነበረበትም፡፡ በዋናነት ሕወሓት ግን ይህ እንዲሆን ነው ያደረገው፡፡

ሌላው ይቅር ኢሕአዴግ እየወደቅንና እየተነሳን በሦስት አሥርት ዓመታቱ ያስመዘገብናቸው ውጤቶች የሚሏቸውን እሴቶች እንኳን ማስጠበቅ ለምን አልቻለም ሲባል፣ መልሱ ያው የእልህና የመጠፋፋት አዙሪቱ ያለቀቃቸው ስለሆኑ ነው፡፡ የመጪው ዘመን የአገራችን ሁኔታና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደቱ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚለው ሥጋት የሚበረታውም፣ ከዚሁ ፍትጊያ አስተሳሰብ ስለመውጣት የተጀመረ መሠረት ባለመታየቱ ነው፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ለአገራዊ ምክክር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ አንድ ተስፋ ሊሆን ይችላል፡፡

እውነት ለመናገር እኮ! እኛ እንዲሆንልን ከምንፈልገው ወይም ከምንመኘው አንፃር በቂ ነው ባንልም፣ አገራችን ወደፊት የመጣችባቸው ዘርፎች እደነበሩ መካድ አይቻልም ነበር፡፡ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በመሠረተ ልማትና በቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት (የዓለም ሁኔታም እየረዳን)… ያፈራናቸው መልካም ፀጋዎች እንደ ሀብት መቆጠር ነበረባቸው፡፡ በ1983 ዓ.ም. ስንት የአንደኛ፣ የሁለተኛና የከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ነበሩን? ስንት ጤና ጣቢያ? ስንት ሆስፒታል ነበረን? ስንት ኪሎ ሜትር ዘመናዊ መንገድ ነበረን? ስንት የመስኖ ሥራ? ስንት ኩንታል ምርት በሔክታር ነበረን?  ዛሬስ? ብለን በማመዛዘን መቀጠል ሲገባ ዛሬ ስንት ተቋማት ወደሙ? ስንት ሴቶች ተደፈሩ? ስንት ዜጎች ሞቱ? ብሎ ከመናገር በላይ የሚያሳፍር ነገር የለም፡፡ ይኼ ደግሞ  ለኢሕአዴግ ትውልድ እንደ ኪሳራ የሚቆጠር ነው፡፡

 በዴሞክራሲ ምኅዳር አስተሳሰብ ሲለካም እንኳንስ በአንድ ፕሮግራምና ሕገ ደንብ ሲመሩ የነበሩ የአንድ ግንባር ኃይሎች ቀርተው፣ በተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች የተፎካከሩ ፓርቲዎችስ ቢሆኑ ወደ ጦርነት ገብተው አገር ማውረድ ለምን ያስፈልጋል? ግለሰቦችም ሆኑ ፓርቲዎች እኮ ዘለዓለማዊ አይደሉም፣ ቀሪ ሕዝብና አገር ነው፡፡ በባለፈው ጊዜ የለውጥ ምርጫ በለስ ያልቀናቸው የሚመስሉ ፓርቲዎችና ግለሰቦችስ፣ ‹‹ዛሬ ካልሆነ መቼም አይሆንም›› ወደሚል አቋም ስለምን መውረድ ፈለጉ የሚሉት የታሪክ ጥያቄዎች በእነ ሕወሓት መቃብር ላይ መቆማቸው አይቀሬ ነው፡፡

 አገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጉዞ ልትገባ ነው ከተባለችበት የያኔው (1983) የሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ዝግጅት ጀምሮ፣ ሕገ መንግሥቱን እስከ ማፅደቅ መሪ የነበረው ሕወሓትና አጋሮቹ መወቀሳቸው አንድ ነገር ሆኖ፣ አሁንም መፍትሔው በዋናነት ይህን ኃይል ካስወገደው ሕዝብና መንግሥት እንዲመነጭ ይጠበቃል፡፡ አንድም አማፅያንና የእልህ ፖለቲከኞችን በሕግ፣ በፖለቲካም ሆነ በኃይል አሸንፎ አገርን ከጥቃት በመታደግ፣ ሁለትም ያኔ ተወጥኖ በመሀል የከሸፈውን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በማጠናከርና የአገር አንድነትን በማጥበቅ አገርን ከቅርቃር ለማውጣት ኃላፊነት መውሰድ ግድ ይላቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙኃኑን የኢሕአዴግ ቅሪት የያዘውና ሌሎች አጋር፣ ተፎካካሪና ገለልተኛ አካላትን አቅፎ በብዙኃኑ የምርጫ ድምፅ ሥልጣን የያዘው ብልፅግና ፓርቲ የአንበሳውን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡

 ይህ ኃይል ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት በመውሰድ፣ መጪውን የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ በተስተካከለ ሜዳ ላይ ለማሳረፍ ዘርፈ ብዙ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡም አሁን በሉዓላዊነት ዘመቻው በግልጽ እንደታየው በሙሉ ኃይሉ አጋር ሊሆነው ግድ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ግን አሁንም ለመደማመጥ፣ የዴሞክራሲ ዕሳቤዎች ለማጎልበትና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት መስጠት ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው፡፡ በሒደቱ ሆደ ሰፊነት እንጂ ‹‹አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ›› እንደሚባለው መሆን አይጠበቅም፡፡

የአገራችን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ልሂቃን ከሕዝቡ በወረደ ደረጃ በዘር ጥላቻና ሽኩቻ ታውረው ከመባላት በመውጣት፣ ሥልጣን ወይም ሞት ከሚለው የስግብግብነት ልክፍት በመላቀቅ፣ አሁን አገር ምድሩን እያስቸገሩ ካሉት የአመፅና የሁከት ፖለቲከኞች (ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ) አስተሳሰብ ፍፁም በመራቅ ለትውልድ የምትተርፍ አገር ማቆየት አለባቸው፡፡ የሚኖራቸውንም የትኛውንም ልዩነት በሕግና በሥርዓት፣ እንዲሁም በሕዝቡ አብላጫ የውሳኔ ድምፅ በመገዛት ከታሪክ ዕዳ ሊላቀቁ ግድ ነው፡፡

ይህን ቢያደርጉ የኢትዮጵያ ሕዝብም በመከባበር፣ በመረዳዳትና ባለው የኑሮ መጠን በደስታ ተረጋግቶ የሚኖርበት ዕድል ይሰፋል፡፡ በልጆቹና በአገሩ ይኮራል፡፡ በየትኛውም የዴሞክራሲ ሒደት ውስጥ ለሕዝብ ድምፅ መገዛት፣ ተሸናፊነትን መቀበል፣ አሸናፊውን ማክበር፣ በአጠቃላይ ለአገሪቱ ዕድገት፣ ልማትና ሰላም ሲባል ሁኔታዎችን በትዕግሥትና በመቻቻል ማለፍ፣ መግባባትና መስማማት ለሕዝብ የሚሰጠው ደስታና በዓለም ፊት የሚያስገኘው ሞገስ በምንም መለኪያ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠብቀውም ይህንን ነው፡፡ የአገራችን ዕጣ ፈንታ እንዳይመክን ሁሉም እንዲሁ ይትጋ ነው የምለው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...