Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሚታየውን የትብብር መንፈስና መነቃቃት ኢኮኖሚውን ለመታደግ ልንጠቀምበት ይገባል!

የአገር ህልውናን ከአደጋ ከመጠበቅና ፀጥታን ከማስፈን ጎን ለጎን ሕወሓት በከፈተብን ጦርነትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ ቀውሶች የተጎዳውን ኢኮኖሚ ማከምና ማዳን ቀዳሚ ከሚባሉ አጀንዳዎቻችን መካከል አንዱ መሆን ይገባዋል፡፡

በጦርነቱ የተናጋውን የቢዝነስ እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ መከፈል ያለበት መስዋዕትነት ሁሉ መከፈል ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ የየራሱን ድርሻ ሊያበረክት የሚገባው ሲሆን፣ በተለይ በሁሉ ረገድ እየታየ ያለው የትብብር መንፈስና መነቃቃትን ኢኮኖሚውን ለመታደግ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ለአገራችን ከዜጎቿ በላይ ሊመጣ የሚችል ማንም የሌለ በመሆኑና ለአገራችን ያለነው እኛው መሆናችንን በመረዳት በኢኮኖሚና በቢዝነስ እንቅስቃሴ ውስጥ የአገር ልጆች እጅ በብርቱ የሚፈለግበት መሆኑን ተገንዝቦ ፊታችንን ወደ አገር መገንባት ማዞር የግድ ይለናል፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ለገባችበት ችግር የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድንና መሰሎቹ የፈጠሩት ቀውስ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ለማዳከም ከተቻለም ለማፈራረስ የተጠነሰሰው ሴራ የአንዳንድ ምዕራባውያንና ታሪካዊ የምንላቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች እጅ ጭምር እንዳለበት በግልጽ የታየ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ይህንንም በአደባባይ በግልጽ ከማሳየታቸውም በላይ እንዲህ እናደርጋችኋለን ከማለት አልፈው ኢትዮጵያን ሊጎዱ የሚችሉ ውሳኔዎችን እያሳለፉም ነው፡፡ እንደ ምሳሌ በቅርቡ አሜሪካ ኢትዮጵያን የአግዋ ተጠቃሚ እንዳትሆን ያስተላለፈችውን ውሳኔ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌሎች ማዕቀቦችም እንጥላለን እያሉ እያስፈራሩን ያሉት አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች ዛሬም ከጭንቅላታችን ያልወረዱ፣ ነገም ሊወስኑ የሚችሉት ውሳኔ አይታወቅምና ኢኮኖሚያችንን መታደግ አለብን ብለን ስንነሳ እነዚህን ተፅዕኖዎች ሁሉ ታሳቢ በማድረግ ጭምር ነው፡፡

በተለይ አንዳንድ የምዕራባውያን በሚድያዎቻቸው ኢትዮጵያን የተመለከቱ ፍፁም ሐሰት ዘገባዎቻቸው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፉት ወይም ሊያሳርፉት የሚችሉት ተፅዕኖዎች ቀላል ሊባል የሚችል ባለመሆኑ ይህንን የመመከት ሥራ መሠራት አለበት፡፡

ይህ ፅንፍና ምቀኝነት ጭምር ያዘለ የሐሰት ፕሮፓጋንዳቸውን የሚያከሽፉ ሥራዎችን በመሥራት የውጭ ኢንቨስትመንት እዳይስተጓጎል ለማድረግ ነገረ ሥራቸው ሁሉ ከሀቅ የራቀ ኢትዮጵያን የማይገልጽ መሆኑን ማጋለጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ ባለሀብቶች የውጭ ሚዲያዎችን የተረት ተረት ወሬ ሰምተው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዳያደርጉ ስለሚያደርግ ይህንን በግልም ሆነ በተናጠል መታገል ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ በተለያዩ አገሮች ያሉ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በሚገባ ማስረዳትና እውነታውን አሳይተው አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ አገር እንዲገባ የማድረግ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ዲፕሎማቶቻችን የሚመዘኑትና የሚለኩበት አንዱና ዋናው ነገር ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል፣ ምን ሠርተዋል የሚል መሆን አለበት፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ ራሷን የሚመስል አገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲዋን ወቅታዊውን የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት በማድረግ እንዲቃኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በተለይ በአገሪቱ በእጅ ያለ ሀብትን በአግባቡ መጠቀምና በተለይም ግብርና ላይ ሊውል የሚችለው ኢንቨስትመንት በተለየ መታየት አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ላይ በርትተው እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ግብርናው ላይ አተኩሮ ምርታማነትን ማሳደግ እንደ ህልውና ጉዳይ መታየት አለበት፡፡

ዛሬ እጅ ለመጠምዘዝ ያለ ይሉኝታ እየፈተኑን ያሉ አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች እንዲህ ከሚዳፈሩበት ደረጃ የደረሰበት ዋና ምክንያት ራሳችንን መመገብ አለመቻላችን ነው፡፡ ስለዚህ ከተፅዕኖ ለመላቀቅ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ ቀርፆ ወደ ሥራ ከተገባ ለኢኮኖሚው ማገገም ከፍተኛውን ድርሻ የሚጫወት ሲሆን፣ የዋጋ ንረትም ለመቆጣጠር ከልመናና ዕርዳታ ለመውጣት ያግዘናል፡፡  

ይህንን ለማድረግ በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የበለጠ እንዲሠሩ ማድረግ አንዱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለአገር አለኝታነታቸውን እያሳዩ ያሉ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከየትኛውም የኢንቨስትመንት መስክ በተሻለ እዚህ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሁን ያለውን አጋጣሚ መጠቀም ይገባል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ወደ አገር እየገቡ ያሉ ዳያስፖራዎች በጋራ ሆነው ግብርና ላይ ኢንቨስትመንት የሚያደርጉበት ኩባንያ እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ላይ የቱንም ዓይነት ጫና ቢፈጠር በግብርና ላይ የምናስመዘግበው ውጤት ብዙ ነገሮችን ይቀይራል፡፡

አሁን ያለንበት ወቅት አገርን በቶሎ ከገባችበት ችግር ማውጣት ላይ ያተኮረ በመሆኑ በየዘርፉ የሚፈለጉ ኢንቨስትመንቶችን በቶሎ ለመተግበር ደግሞ የተንዛዛ ቢሮክራሲን ማስቀረት ቀልጣፋ ውሳኔ ሰጪ አመራሮችን ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ማስቀመጥ የግድ ይላል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት