Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ኖ ሞር ብላክ ማርኬት›› በሚል የኢትዮጵያ ባንኮች ኤግዚቢሽን ሊካሄድ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ መሠረት እየገቡ የሚገኙ ዳያስፖራዎች ዶላራቸውን በሕጋዊ መንገድ እንዲመነዝሩ የሚያስችል የኢትዮጵያ ባንኮች ኤግዚቢሽን ማዘጋጀቱን ሰፍ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ ሐሙስ ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ኤግዚቢሽኑ በግሮቭ ጋርደን ዋክ ከጥር 3 እስከ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚከናወን ሲሆን፣ ‹‹ኖ ሞር ብላክ ማርኬት›› በሚል መሪ ቃል ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

የኤግዚቢሽኑ አዘጋጅ ወ/ሮ ኩኪ አስፋው እንደገለጹት፣ ኤግዚቢሽኑ ሕገወጥ የዶላር ምንዛሪን ለማስቀረት፣ ዳያስፖራው በአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ እንዲኖራቸውና ያጠራቀሙትን ገንዘብ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ ከባንኮች  ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ ነው፡፡   

በኢትዮጵያ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት በአንድ ቦታ ላይ የሚገናኙበትን መንገድ የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት አዘጋጇ፣ ለዳያስፖራዎች በቅርበት ምርትና አገልግሎቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ እንዲሁም የዘመናዊ አሠራር ሒደትን እንዲከተሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ለሚገኙ ዳያስፖራዎች የተቀላጠፈና ዘመናዊ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ወ/ሮ ኩኪ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የዶላር እጥረት ለመቀነስ ያነገበ ኤግዚቢሽን እንደሆነ አክለው፣ ይኼም በሕገወጥ መንገድ የሚመነዝሩ ግለሰቦችን ቁጥር በከፊልም ቢሆን ሊቀንስ ይችላል ሲሉ አብራርተዋል፡፡   

መግለጫ እስከተሰጠበት ሰዓት ድረስ 85 በመቶ የሚሆኑ ባንኮች ኤዚቢሽኑ ላይ ለመግባት ፈቃደኛ ሆነው በፊርማ ማረጋገጣቸውን፣ በቀጣይም ሌሎች ባንኮች ፈቃደኝነታቸውን ያሳያሉ ተብሎ እንደሚታሰብ አዘጋጇ አክለዋል፡፡  

በኤግዚቢሽኑ ከባንኮች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተቋማት ጭምር የሚካፈሉበት መሆኑን፣ እነዚህም ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን በአንድ ቦታ ሆነው እንዲያስተዋውቁ እንዲሁም ማኅበረሰቡ በዚህ አገራዊ ኤግዚቢሽን ላይ በመገኘት የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ተፅዕኖ ሲቃወሙና የተለያዩ መልዕክቶችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያስተጋቡ የነበሩ ዳያስፖራዎችን በመቀበል የኢትዮጵያን ህልውና ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይም ‹‹በቃ›› (ኖ ሞር) የሚለው እንቅስቃሴ አገራዊ ተልዕኮ ያለበት መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፣ ከዚህ ውስጥም ‹‹ኖ ሞር ብላክ ማርኬት›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ኤግዚቢሽን ኢንቨስትመንትን፣ ቱሪዝምን ለማሳደግና ሌሎች ነገሮችን ለማከናወን ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡

አንዳንድ ተቋማት ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ በመጣል የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንስ ጥረት ማድረጋቸውን፣ ይሁን እንጂ ይህንን ተፅዕኖ ለመቋቋምና ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ በዳያስፖራው በኩል የውጭ ከረንሲን መቀየር ተገቢ እንደሆነ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ተልዕኮ ለማሳካት ኤግዚቢሽኑ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚሉት አምባሳደሩ፣ የዳያስፖራውን መምጣት ተከትሎ ቀልጣፋ የሆኑ አሠራሮችን ለማካሄድ በውጭ ጉዳይ በኩል የሚመራ ኮሚቴ መዋቀሩን አብራርተዋል፡፡  

ኮሚቴውም በውጭ ጉዳይ በኩል ይመራ እንጂ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶችንና የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዳያስፖራው ያለውን ዕውቀት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ በማምጣት እንዲሁም ደግሞ በንግድ፣ በቱሪዝምና በኢንቨስትመንቱ ላይ አሻራውን ትቶ እንዲያልፍ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ግርማ ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን የተለያዩ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ያስታወሱት ኃላፊው፣ በዳያስፖራው በኩል ከሚላከው የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ የሚመነዘረው ከ30 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ2013 ሒሳብ ዓመት ከዳያስፖራው 3.6 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን፣ ከዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛ በታች የሚሆነው በሕጋዊ መልኩ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን አብዛኛውን ጊዜም ሕገወጥ የሆነ ምንዛሪ እንደሚፈጸም አቶ ወንድወሰን አክለዋል፡፡

በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ሕገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ኢትዮጵያ ከዳያስፖራው ማግኘት የሚገባትን ገንዘብ በቀላሉ እንዳታገኝና ላልተፈለገ ዓላማ እንዲውል እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኤጀንሲው የሕገወጥ የውጭ ምንዛሪን ለማስቆም ከዳያስፖራው ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ከተነሱ አንኳር ነጥቦች መካከል ምንዛሪ አንድ ዓይነት ይሁን፣ ሌሎች አማራጮችን ባንኮች መዘርጋት አለባቸው የሚሉት እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

ለሕገወጥ ምንዛሪ መስፋፋት መንስዔ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ የመላኪያ ዋጋ እስከ 14 በመቶ በመሆኑ እንደሆነ፣ ይህንንም ለመቅረፍ ባንኮች እስከ 10 በመቶ ማድረግ እንደሚገባቸው ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጥሪ መሠረት ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡ ዳያስፖራዎች በሕጋዊ መንገድ ምንዛሪ እንዲፈጽሙ ከአየር መንገድ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች