የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቅርቡ ከኢትዮ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር በአሜሪካ ባዘጋጀው ‹‹ኢትዮ-አሜሪካ 2021 የንግድ ትርዒት›› ላይ ተሳታፊ የነበሩት የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊና የንግድና ኢንቨስትመንት ኃላፊ በዚያው መቅረታቸው ታወቀ፡፡
በንግድ ምክር ቤቱ አስተባባሪነት ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የተጓዘውን የንግድ ልዑካን የመሩት የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ የሱፍ አደም ኑር ሲሆኑ፣ የንግድ ትርዒቱ ካለቀ በኋላ ኃላፊነታቸውን ለቀው እዚያው መቅረታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የንግድ ትርዒቱ ካለቀ በኋላ ሌሎች የንግድ ልዑካንና የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ወደ አገር ሲመለሱ አቶ የሱፍ በአሜሪካ የተወሰኑ ቀናት እንደሚቆዩ አሳውቀው ነበር፡፡
ከቀናት በኋላ ግን ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ለንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ አሳውቀው፣ እዚያው መቅረታቸው ታውቋል፡፡ ቦርዱም የእሳቸውን በዚያው መቅረት በማረጋገጥ ምክትል ዋና ጸሐፊውን አቶ ውቤ መንግሥቱን በተጠባባቂ ዋና ጸሐፊነት ሰይሞ አዲስ ዋና ጸሐፊ ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቷል፡፡
እንደ አቶ ዮሴፍ ሁሉ ከንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ልዑካኑን በመምራት ወደ አሜሪካ አቅንተው የነበሩት የንግድ ምክር ቤቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምስግና በተመሳሳይ፣ በንግድ ትርዒቱ ላይ ከተሳተፉ በኋላ እዚያው ቀርተዋል፡፡ ሁለቱ የንግድ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን እዚያው ሆነው ለንግድ ምክር ቤቱ ማሳወቃቸውም ታውቋል፡፡
የንግድ ትርዒቱ በአሜሪካ ሀያት ሪጀንሲ ክሪስታል ከተማ ጥቅምት 26 እና 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ተካሂዶ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ዋና ጸሐፊው ወደ ኢትዮጵያ ያልመጡና እስካሁንም በሥራ ገበታቸው ላይ አለመሆናቸው ታውቋል፡፡
በአሜሪካው የንግድ ትርዒት ላይ ተሳታፊ ለመሆን በንግድ ምክር ቤቱ ተመርጠው ከተጓዙት የተለያዩ ኩባንያዎችን ከወከሉ ግለሰቦች መካከል አንዳንዶች ሳይመለሱ ስለመቅረታቸውም እየተነገረ ነው፡፡
በዚህ የንግድ ትርዒት ላይ ወደ 40 የሚሆኑ ኩባንያዎች የተሳተፉበት እንደነበር በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን የንግድ ትርዒት ለማዘጋጀት ከኢትዮ-ፕሮሞሽን ጋር ውለታ ፈጽሞ የነበረው ዓምና ሲሆን፣ የንግድ ትርዒቱም በሰኔ ወር ለማካሄድ ታቅዶ እንዲራዘም ተደርጎ ጥቅምት 2014 ዓ.ም. ላይ ተከናውኗል፡፡