Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት 301 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሮሚያ ባንክ በተጠናቀቀው የ2013 ሒሳብ ዓመት የአስቀማጭ ደንበኞቹን መጠን በ800 ሺሕ በመጨመር 2.5 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉንና በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ካገኘው 1.13 ቢሊዮን ብር ትርፍ ውስጥ 301 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተገኘ መሆኑን አመለከተ፡፡

ባንኩ የ2013 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደገለጸው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ እመርታ ያሳየበት  የተቀማጭ ገንዘብ ደንበኞቹን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉ ነው፡፡ በባንኩን ሪፖርት መሠረት፣ በተጠናቀቀው ዓመት የደንበኞቹን ቁጥር 45 በመቶ በማሳደግ በአጠቃላይ ለተቀማጭ ገንዘቡ ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመላክቷል፡፡

ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያፈራው የደንበኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በሪፖርቱ እንደተመለከተውም፣ ባንኩ ካለው 2.5 ሚሊዮን ያህል የአስቀማጮች ቁጥር ውስጥ 610,758 ከወለድ ነፃ አስቀማጮች ናቸው፡፡ በ2013 ብቻ ከወለድ ነፃ አስቀማጮችን በ62 በመቶ ወይም በ375,980 አስቀማጮች ማሳደግ ችሏል፡፡  

የኦሮሚያ ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ባንኩ የአስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር ይበልጥ ለማሳደግና የባንክ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት አሁንም ተጨማሪ ሥራዎችን የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በዚህን ያህል ደረጃ የአስቀማጭ ደንበኞችን ቁጥር ማስፋቱም በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩን የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ24 በመቶ ለማሳደግ እንዳስቻለውና አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 34.3 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ታውቋል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ካስመዘገበው መካከል፣ ከታክስ በፊት 1.13 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ270 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ነው፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ዕድገቱ ስድስት በመቶ ነው፡፡ የኦሮሚያ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ካገኘው ትርፍ ውስጥ 301 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ያገኘው ስለመሆኑ የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በ2013 ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ ከታክስ በፊት ያገኘው 301 ሚሊዮን ብር ትርፍ ከአንዳንድ ባንኮች ጥቅል ዓመታዊ ትርፍ ብልጫ ያለው መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ33.4 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ በባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ ያሰባሰበው የቁጠባ ሒሳብ ከ4.84 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ23.6 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለብድር የሰጠው የገንዘብ መጠን በ638.6 ሚሊዮን ብር ጨምሮ 3.54 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ኦሮሚያ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በመስኮት ደረጃ በመስጠት የመጀመርያው ባንክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ዘርፍ የተገኘውም ዓመታዊ ገቢ 416 ሚሊዮን ብር መድረሱን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ ይህ ገቢ በ72 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ ባንኩ በ2012 ያገኘው 242 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ 15.3 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ካገኘው ጠቅላላ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ውስጥ ስምንት በመቶ ያህል ድርሻ አለው፡፡

የባንኩን የ2013 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም በተመለከተ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) እንዳመለከቱትም፣ በሒሳብ ዓመቱ በኢንዱስትሪው ላይ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ባንካቸው ከቀዳሚው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም አሳይቷል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ24 በመቶ ማሳደግ መቻሉ፣ በሒሳብ ዓመቱ ለብድር የዋለው አጠቃላይ መጠኑ በ27 በመቶ ጨምሮ 25.77 መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ይህ ብድር በመደበኛውና ከወለድ ነፃ የተሰጠውን ብድር የሚያጠቃልል ነው፡፡ የባንኩ የትርፍ ምጣኔም ከቀዳሚው ዓመት የ270 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ያመለከቱት አቶ ገመቹ፣ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን በ23 በመቶ በማሳደግ 41.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የተከፈለ ካፒታሉም 3.46 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አመልክተዋል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ገቢ ደግሞ ከ18 በመቶ አድጎ 4.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነም የባንኩ መረጃ ያመለከተ ሲሆን፣ ስድስት በመቶ የሚሆነው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተገኘ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡   

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ እንደ ስኬት ከጠቀሳቸው ተግባራት መካከል ባንኩ በአዲስ ዓርማ መቅረቡ ነው፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ በሪፖርታቸው፣ ዓርማ፣ ምልክትና ቀለማቱን ማንነታቸውን በጉልህ ለመግለጽና ለበለጠ ተወዳዳሪነት የሚጠቀሙበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ባንኩ መረጃ ከሆነ፣ የባንኩን ተበዳሪዎች ቁጥር በዘጠኝ በመቶ አሳድጎ 11,760 አድርሷል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ የካፒታል መጠን ደግሞ 5.5 ቢሊዮን ብር ነው፡፡   ኦሮሚያ ባንክ 316 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ አጠቃላይ የሠራተኞቹ ቁጥር 6,418 እንደሆነ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች