Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ መራዘምና ውስጣዊ ሽኩቻ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቀጣይ ወር አካሂደዋለሁ ያለውን ጠቅላላ ጉባዔ አሁንም ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቀደም ብሎ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ያልቻለ መሆኑን በመግለጽ፣ በቅርቡ ቦርዱ ባካሄደው ስብሰባ በጥር 2014 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔው እንዲካሄድ ቢወስንም፣ እንደገና ጠቅላላ ጉባዔው ተራዝሟል፡፡ ይህም አግባብ አለመሆኑን ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ይገልጻሉ፡፡

 ምክር ቤቱ፣ ‹‹ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ ከነበረበት ወደ ሦስት ዓመት እየሆነው ነው›› በማለት የቦርዱን ውሳኔ ይሞግታሉ፡፡

ቀድሞም ቢሆን በኮቪድ-19 ከማሳበብ በውክልና ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ ይቻል እንደነበር የሚገልጹት እኚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ ከምክር ቤቱ አባላት በላይ ተሰብሳቢ ያላቸው ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ስብሰባ እያደረጉ ከሁለት ዓመት በላይ በኮቪድ-19 ማሳበብ እንዳልነበረበትም ይጠቅሳሉ፡፡

በዚህ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጤ ግን፣ በእርግጥም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በወቅቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ ሳይችል ስለመቅረቱ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ በምንዘጋጅበት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና የወቅታዊው አገራዊ ጉዳይ መከሰት ጉባዔው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም አስገድዶናል ይላሉ፡፡

በተለይ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ በተዘጋጀንበት በዚህ ሰዓት ብዙ አባላት መቅደም ያለበት ‹ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ነው› በማለታቸውና ጠቅላላ ጉባዔውን ከማድረግ በፊት ቅድሚያ ወገኖቻችንን ለመደገፍ ይሰጥ በማለታቸው ጠቅላላ ጉባዔውን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ መደረጉንም አክለዋል፡፡

አሁን ሊራዘም የቻለው በንግድ ምክር ቤቱ ትልልቅ አባል ነጋዴዎች ጥያቄ ጭምር መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔው ወቅቱን ጠብቆ ካለመደረጉ ባሻገር በምክር ቤቱ ውስጥ አለመግባባቶች እንዳሉም እየተጠቆመ ነው፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ በንግድ ምክር ቤቱ ቦርድና በዋና ጸሐፊ መካከል ተፈጥሯል በተባለው አለመግባባት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ባልተጠበቀ መንገድ ለመጀመርያ ጊዜ ፈቃድ ወስደው የወጡት ከዚሁ ተፈጥሯል ከተባለው አለመግባባት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡

ወ/ሮ መሰንበት ግን የተፈጠረ አለመግባባት የለም ይላሉ፡፡ አቶ ጌታቸው አሥር ዓመት ሲያገለግሉ አንድም ጊዜ ፈቃድ ወጥተው አያውቁም፡፡ ስለዚህ የ30 የሥራ ቀናት ፈቃድ ለመውጣት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ እንደተፈቀደላቸው ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች እንደሚሉት ግን፣ ምክር ቤቱ ውስጥ በተለይ አዲስ ለመተግበር ከታቀደው አሠራር ጋር ተያይዞ የተለያዩ አመለካከቶች እየታዩ ነው፡፡  

በንግድ ምክር ቤቱ ቦርድና ዋና ጸሐፊው መካከል የተፈጠረው አለመግባባትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ያለመግባባቱ አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው ምክር ቤቱ ማካሄድ ከነበረበት ምርጫና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ አመራር ለመምጣት እየተደረገ ነበር የተባለው እንቅስቃሴ ነው፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በሕጉ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ አካሄዶ አዳዲስ የቦርድ አባላትን ማስመረጥ ከነበረበት ጊዜ ከሁለት ዓመታት በላይ የቆየ መሆኑ የሚታወቅ  ሲሆን፣ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዳለሁ ባለበት ወቅት አዲስ ቦርድ አባላትን ለማስመረጥ ውስጥ ውስጡን እየተሠራ ነበር የተባለ እንቅስቃሴ ቦርዱ ደርሶበት የተፈጠረ ችግር ነው ይላሉ፡፡  

ይህም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደሚደረገው በጽሕፈት ቤት አካባቢ ያሉ አንዳንድ ወገኖች በራሳቸው መንገድ አዳዲስ ቦርድ አመራር ለመምጣት የሚፈልጉ ወገኖች ተቧድነው ቦታውን እንዲይዙ ለማድረግ መካሪዎች ከመኖራቸው ጋር ያያይዙታል፡፡ ይህንንም ጉዳይ በተመለከተ ወ/ሮ መሰንበት በሰጡት አስተያየት፣ እንዲህ ያሉ ነገሮች ከዚህ ቀደም ሲደረጉ ይሰማ እንደነበር፣ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ነገሮች እንዳይኖሩ በቀጣይ የሚደረገው ምርጫ ከዚህ በተለየ መልኩ እንዲካሄድ ቦርዱ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ነበሩ የተባሉ ችግሮችን ለመቅረፍም ለመጀመርያ ጊዜ ምርጫው በኤሌክትሮኒክስ እንዲካሄድ ውሳኔ የተላለፈ ስለመሆኑ አመልክተው፣ ይህም ከምርጫ ጋር የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል ተብሎ ታምኖበት፣ ይህንን የኤሌክትሮኒክስ የምርጫ ሒደት ለማካሄድ ለዚህ ሥራ ከሚመረጥ ኩባንያ ጋር ይሠራል ብለዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ብዙ ጊዜ በቦርድ ምርጫ ውስጥ እጁን ያስገባ ስለነበር፣ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች መታየታቸው አሁንም ከምርጫ ጋር በተያያዘ ንግድ ምክር ቤቱ ያልጠራ አሠራር እንዳለው የሚያመለክት ነው ቢባልም፣ ወ/ሮ መሰንበት ይህ እንዳይሆን ተሰናባቹ ቦርድ አስፈላጊውን ሥራ እየሠራ ነው ይላሉ፡፡  

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በተደጋጋሚ ከቦርዱ ምርጫ ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ የቆዩ መሆኑን ያስታወሱት ምንጮች፣ አሁንም ተመሳሳይ ችግር እየታየ ነው ብለዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ አለ የተባለው አለመግባባት በተለይ ጎልቶ የወጣው የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድና ማኔጅመንት የንግድ ምክር ቤቱን አሠራር አጠቃላይ ግምገማ ለማካሄድ ከተሰበሰበ በኋላ ስለመሆኑ ምንጮች ሲገልጹ፣ ወ/ሮ መሰንበት ግን ይህ ግምገማ እስከዛሬ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት አዳዲስ ውሳኔ እንዲወሰን ያደረገ ነው ይላሉ፡፡  

ወደ 32 ነጥቦች ተቀምጠው በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ አሠራሮች እንዲሻሻሉ የተደረገ ሲሆን፣ አግባብ አይደሉም የተባሉ አሠራሮች እንዲሻሩ ተደርገዋል፡፡ እንደ ችግር የታዩ አሠራሮች በሙሉ እንዲወጡ ተደርገዋልም ተብሏል፡፡ እንደ ውጭ ያሉ ጉዞዎችም ለጊዜው እንዲቋረጡ መደረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡ ከውጭ አገሮች ጋር የሚደረግ አላስፈላጊ ግንኙነትና መሰል ጉዳዮችን በመመልከትም ቦርዱ አስፈላጊውን ዕርምጃ ስለመውሰዱም ይጠቅሳሉ፡፡

ሌላው በቅርቡ ተደረገ የተባለው አነጋጋሪ ጉዳይ ደግሞ ባልተጠበቀ መንገድ ፈቃድ ለወጡት የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ቦርዱ አበረከተ የተባለው ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ አውቶሞቢል ነው፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ቦርዱ ለዋና ጸሐፊው ሁለት ሚሊዮን ብር ግምት ያለውን የቤት አውቶሞቢል ማስተላለፉ ግልጽ አለመሆኑን በመተቸት ለምን ይህ ሆነ ይላሉ? ተሽከርካሪ የተላለፈበትም መንገድ አግባብ እንዳልሆነ የሚገልጹት ወገኖች እንዲህ ያሉ ሽልማቶች የሚሰጡት አትራፊ በሆኑ ኩባንያዎች እንጂ፣ እንዲህ ላለ ማኅበር አይደለም በማለትም ይሞግታሉ፡፡

 በዚህም ጉዳይ ላይ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ወ/ሮ መሰንበት፣ የቀድሞው ቦርድ በወሰነውና ትጋት ላሳዩ ሠራተኞች ሽልማት እንደሚሰጥ በደነገገው መሠረት ሽልማቱ መሰጠቱን ይገልጻሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሽልማቶች ከዚህ በፊት ይሰጡ እንደነበር በማስታወስም፣ ከዚህ ቀደም የወርቅ ሽልማት ተሰጥቶ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

አሁንም ሽልማቱ ለዋና ጸሐፊው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሠራተኞችም የተለያዩ ሽልማቶች ተሰጥተዋል ተብሏል፡፡ ይህም በተለያዩ ፕሮጀክቶች ያስገኙት ከፍተኛ ገቢ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነም ጠቅሰው፣ ይህ አሠራር የተለመደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አቶ ጌታቸው በበኩላቸው፣ ተፈጠሩ የተባሉትን ችግሮች አስተባብለው ምንም የተፈጠረ ነገር የሌለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፈቃድም የወጣሁት ላለፉት አሥር ዓመታት ፈቃድ ወጥቼ ስለማላውቅ ቢሆንም፣ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሥራ እመለሳለሁ፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ተፈጠረ የተባለው ችግር ሁሉ አሉባልታ መሆኑን፣ ፈቃድም ሲወጡ ለምክትላቸው ውክልና ሰጥተው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች