Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የወገን አለኝታ!

ሰላም! ሰላም! በቀደም ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ምናለኝ መሰላችሁ? “ለሰላማችን የተከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት በከንቱ እንዳይራከስ፣ በእኩልነት የምንኖርባት ኢትዮጵያን ተባብረን መገንባት አለብን፡፡ ጀግኖች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እሳቱን ተጋፍጠው ያመጡልንን አንፃራዊ ሰላም የማንም ተልካሻ ፖለቲከኛ ተብዬዎች እንዲፈነጩበት መፍቀድ የለብንም…” ነበር ያለኝ፡፡ እውነት ነው ለሰላማችን የተከፈለው ዋጋ የማንም መጫወቻ እንዳይሆን መበርታት ይኖርብናል፡፡ በቀደም ዕለት አንድ ያገለገለ ሲኖትራክ አሻሽጬ ኮሚሽኔን ልቀበል የሆነ ካፌ በረንዳ ላይ ተጎልቼ የባጡን የቆጡን አስባለሁ። ለካ አንዱ ከጎኔ ይነድፈኝ ይዟል። መቼም የእናንተ ነገር አይታወቅም። ዘመኑን አስባችሁ እባብ ወይ ጊንጥ የነደፈኝ ይመስላችኋል ብዬ እኮ ነው። ይኼ አስመስሎ መሳል ነገር አለ አይደል? እንደ ፎቶግራፍ? ንድፍ ስል እሱን ነው። ለነገሩ ዘንድሮ ሳይቀነስ ሳይጨመር የማይገለበጥ ነገር የለም። ‘ኮፒ ፔስት’ ይለዋል እንግሊዝኛው። በጥበብ ስም ‘ኮፒ’ መብዛቱ ገርሞን ሳናበቃ ልብ ‘ኮፒ’ ለማድረግ የሚጥርም እያየን ነው። ልብ አውልቁ እኮ በየት በኩል ከች እንደሚል አይታወቅም። ልብ በሉ እንግዲህ!

እናላችሁ ያለ ፈቃድ በልሙጥ ወረቀት መገልበጤ ሳይሆን ያናደደኝ በእስክሪብቶ መሳሌ ነው። ቆፍጠን ብዬ፣ “እንዴት አንተ? እግዜር እኮ ሲፈጥረኝ እንድሳሳት ጭምር ነው። እንድሳሳት ብቻ ሳይሆን ተሳስቼ እንድታረም አድርጎ ነው። እንዴት አንተ በድፍረት በእስክሪቢቶ ትቸከችከኛለህ?” እለዋለሁ፣ ‹‹ሥልጣን የለኝማ እርሳስ ከየት አመጣለሁ?›› አይለኝ መሰላችሁ? እንዲያ ሲለኝ ላጲስ መዋጥ አማረኝ በቃ። የት አባቴ ልግባ? ነዶኝ ስለነበር፣ “እሺ እንዴት ሳታስፈቅድ ትስለኛለህ?” ብዬ ስደነፋ፣ ‹‹ለመተቸትና ለመሳደብ እንጂ ፈቃድ የሚያስፈልገው ለማየትና ለመስማት ሜዳው ነፃ ነው…”  ሲለኝ ‘አሃ ይኼ ሰው ከጀርባው ሌላ ተልኮ ይኖረዋል’ ብዬ ብድግ አልኩ። ኋላ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ሳገኘው እነግረዋለሁ፣ “ደግሞ ብለው ብለው ፒካሶንም ማኖ አስነኩት?” ብሎ እሱ ብሶብኝ ቁጭ። አሁን ፒካሶ ቢሰማ ምን ይላል? ሸማ አለፈርጁ ተለበሰ ብሎ ያብዳል ወይስ እሱም እንደ እኛ እንደ ዘመኑ ሰዎች ዋናው ጉዳይ ገንዘብ ነው ብሎ ምን ቸገረኝ ይላል? እንጃ!

   አንዳንዴ ራሴን የምወቅስበት ነገር ግን አላጣም፡፡ ምናልባት የኑሮ ውድነቱን በተለይ የዓውደ ዓመት ሰሞን ማጣፊያው እንደሚያጥር ጠርጥረህ ቢሆን ኖሮ እያልኩ ራሴን እታዘበዋለሁ፡፡ ዳሩ ማን ነገ የምንሆነውን ያውቅና? እንኳን የሚሆነውን የሆነውን በቅጡ አሰናድተውና አብራርተው የሚያቀርቡልንን ማግኘት አዳግቶናል፡፡ የሚገርማችሁ እንዲህም ሆነን ይኼው አንብቡልኝ እንላለን፡፡ የባሻዬ ልጅ በ350 ብር ገዝቶ አንድ መጽሐፍ ካነበበ በኋላ፣ “ይህንን እንጭጭ መጽሐፍ ከማንበብ ከአንበርብር ጋር ቢራ እየጠጣን ብናወጋ ይሻል ነበረ…” እያለ ሲቆጭ ሰምቸዋለሁ። እሱ በአፉ ቢራ ቢለውም እኔ ግን ዶሮ ብንበላበት ይሻል ነበር ብዬ ለራሴ ተርጉሜ፣ መጪውን ዓውደ ዓመት እንዴት አድርገን መዋል ይኖርብን ይሆን እያልኩ ሳስብ ነበር፡፡ ዓውደ ዓመቱን ሳስብ ግን በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖቼ ትዝ ሲሉኝ፣ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ለማን ቅድሚያ መስጠት እንደሚኖርብን ገባኝ፡፡ የዘንድሮ ዓውደ ዓመት ወጪያችን ለወገኖቻችን ይውላል፡፡ ተወሰነ በቃ!

      የባሻዬ ልጅ ያነሳሁነትን ርዕሰ ጉዳይና የጀመርነውን ውይይት ሲታዘብ ቆይቶ ድምፁን መጠራረግ ሲጀምር፣ ሙያዊ ሒስ የሚሰጥ በሚመስል ግርማ ሞገስ ታጅቦ ነው፡፡ የባሻዬን ልጅ ሳይ እውነቴን ነው የምላችሁ ውስጤ ቁስል ይላል፡፡ ስንቱ አላጋጭ ተማርኩ ባይ ሞራው ያልተገፈፈ የአስተሳሰብ ድህነት አንጎሉን ተቆጣጥሮበት፣ የመመረቂያ ጹሑፉን ጊዜ በጣለው ብራችን አስሞንጭሮ ተመርቆ ሳይ እንባ ነው የሚቀረኝ። “ቻንስ ከሌለህ ምን ትሆናለህ…” ነበር የሚባለው? በቃ ልክ እንደዚያ ሆኖ ሳየው አዝንለታለሁ፡፡ መቼም እኛን በማዘን የሚወዳደረን እንደሌለ ታውቃላችሁ፡፡ በራሳችን ነው እንጂ የማናዝነው ለሰው ማዘንና በሰው ማዘን የሚደርስብን የለም፡፡ አዎ! ስንቱ ደሃ እየተጨፈለቀ የመኖር ሰብዓዊ መብቱን እኛ ዕድገት ባልነው መዳመጫችን ስንጨፈልቀው ትንሽ እንኳ በራሳችን አናዝንም። መቼስ ልቦና ይስጠን እንጂ ሌላማ ምን ይባላል ብለችሁ ነው፡፡ የሚቆጨው ግን ህሊና የሚባለው ትልቅ ሸክም ለአንዳንዶቹ የገለባ ያህል ቀሎአቸው ሲያተራምሱን ውስጤ ያዝናል፡፡ በደላላ ሰው ተጉላላ እንዳትሉኝ እንጂ!

የባሻዬ ልጅ ብሶቱ ሰላሙን የነሳው በሚመስል በስሜት መናገር ጀመረ፡፡ “በጣም የሚገርመኝ እኮ ለአገር ደንታ የሌላቸው ጦርነት ቀስቅሰው ሕዝባችንን መግደላቸውና ማፈናቀላቸው ነው፡፡ ይህም አልበቃ ብሏቸው የደሃ ንብረት ማውደማቸው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የሚልሱት የሚቀምሱት የላቸውም፡፡ ለእነሱ በዓል ማለት ከባድ ቅንጦት ነው፡፡ በተቻለን አቅም እነሱን መደገፍ ያለብን ለበዓል ብቻ ሳይሆን፣ ለዘለቄታው የሚቋቋሙበትን ጭምር እያሰብን ነው፡፡ በሌላ በኩል የሚያናድደኝ በጦርነቱ ጦስ ሕዝባችን ሜዳ ላይ ወድቆ ያንን የማይረባ ከንቱ ፖለቲካቸውን እየዘረጉ ነገር የሚያሸቱ መኖራቸው ነው፡፡ አሁን እነዚህን ጭምር ነው መታገል ያለብን…” አለ፡፡ ባለሙያዋ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ የጠመቀችውን የዶሮ ዓይን የመሰለ ጠላ ቀድቼለት አንዴ ገርገጭ አድርጎ ጉሮሮውን ጠራርጎ፣ “አደጉ የተባሉ አገሮችን እያየን እነሱን ለመምሰል መሮጥ መልካም ቢሆንም፣ እኛም ለዘመናት በገነባናቸው እሴቶቻችን በመታገዝ መረዳዳት አለብን…” ብሎ ንግግሩን ገታ አደረገ፡፡ ይህ ሰው እርግጥም ጠቢብ ነው!

እናንተዬ “እንዳያልፉት የለ ያ ሁሉ ታለፈ…” እያሉን ገብተው ለ27 ዓመታት የመከራ ቀንበር ያሸከሙን፣ ላለፉት አራት ዓመታት ደግሞ ሲያምሱን ከርመው ጦርነት ውስጥ የከተቱን ወንበዴዎች ጉዳይ በጣም ነው የሚያሳስበኝ፡፡ እነዚህ በልካቸውና በመጠናቸው መኖር የማይፈልጉ፣ ሁሌም ከላይ ሆነው እንዳሻቸው ካልገዙን የማይረኩ፣ ሰብዓዊነት የሚባል ነገር ከልባቸው ውስጥ የሌለና ከሰይጣን የባሱ ጉዶችን ሳስብ ያመኛል፡፡ ከእነዚህ ጋር እንኳንስ ለመደራደር ለመነጋገር እኮ አይቻልም፡፡ ሰይጣንን ያስንቃሉ የሚባሉትን እነዚህን ጉዶች በተመለከተ በአንድ ወቅት የሰማሁትን ልንገራችሁ፡፡ እነዚህ ከሰይጣን የሚያስንቁ ጉዶች እኮ ብዙ ታሪክ አላቸው፡፡ “ለማያውቅሽ ታጠኝ…” የሚባለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ሳስታውስ የእነዚህ ጉዶች ታሪክ መቼም አይረሳኝም፡፡ እንዴት ይረሳል!

አንዲት እናት ቪላ ቤታቸውን ማከራየት ይፈልጉና ለአንዱ ደላላ ይነግሩታል፡፡ ደላላውም ተከራይ ሲያፈላልግ የእነዚህን ጉዶች ወኪል ያገኘዋል፡፡ ወኪሉም ቤቱን ለማየት ሌሎች ባልደረቦቹን ይዞ ከደላላው ጋር ይሄዱና ለመከራየት ይስማማሉ፡፡ በወር 50 ሺሕ ብር ለመከራየት የሦስት ወር ቅድሚያ ከፍለው ይሄዳሉ፡፡ አከራይዋ ደላላውን የሰዎቹን ማንነት ሲጠይቃቸው “ወያኔዎች ናቸው…” ሲላቸው፣ “በል በቅናሽም ቢሆን ለሌላ አከራየዋለሁ ሌላ ተከራይ ፈልግ በቶሎ…” ብለውት ለሌላ ተከራይ በ40 ሺሕ ብር ያከራዩና ደውለው የመጀመሪያዎቹን ገንዘባችሁን ውሰዱ ይሏቸዋል፡፡ ደላላው በቅናሽ ማከራየታቸውን ስለነገራቸው አንደኛው፣ “ምነው እማማ እኛ የተሻለ ዋጋ ሰጥተንዎት እንዴት ለሌላ በቅናሽ ያከራያሉ…” እያለ ሲነጫነጭ፣ “እኔ ከእናንተ ይልቅ ለሰይጣን በነፃም ቢሆን ባከራይ እመርጣለሁ…” ሲሉት ሰውዬው ገርሞት፣ “ለምን ሲባል…” ይላቸዋል፡፡ አከራይዋም፣ “ሰይጣንን በፀበል ማስወጣት እችላለሁ… እናንተን ግን እንኳን ፀበል ሌላም አይበግራችሁም…” ብለው መለሱለት አሉ፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ ነገሩ!

እንዲያው ስለይሉኝታ አንስተን ትንሽ መጨዋወት ይኖርብናል። በአሁኑ ጊዜ በጣም ያስቸገረው የአብዛኛው የእኛ ሰው ዝምታና ይሉኝታ ነው። በይሉኝታ ሳናውቀው የጥፋት ተባባሪ የምንሆን ብዙ ነን፡፡ ጥፋት እያየን ላንናገር የተለጎምን ያህል ዝም። ትውልድ ሲበላሽ እያየን ምን አገባኝ ብለን ጭጭ፡፡ በእኔ እስካልመጣ ድረስ እየተባለ በአጉል ይሉኝታ አገር ሲጠፋ እንለጎማለን፡፡ በራሳችን የመጣብን ሲመስለን ግን አገር ይያዝልኝ ማለታችን ያበሳጫል። ወንበዴዎቹ እኮ ውሸትን ከፊት አስቀድመው በፕሮፓጋንዳቸው ሊበታትኑን የነበረው ይሉኝታችንን ተጠቅመው ነው፡፡ እነሱ ዓይናቸውን በጥሬ ጨው አጥበው ሜዳውን ጫካ፣ ገደሉን ተራራ፣ ወንዙን ውቅያኖስ፣ ንፋሱን እሳት እያሉ ለጥፋት የተነሱት የእኛ ዝምታ ስለጠቀማቸው ነው፡፡ በአግባቡ መጠየቅና መተቸት ሲገባን በአሉባልታ እንታሰራለን፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ “መንግሥት ሲያጠፋ አጥፍተሃል ብለህ ማፋጠጥ አለብህ እንጂ፣ እንደ መንደር ወሬኛ በአሉባልታ አገር ማካለል የለብህም፡፡ ለየት ያለ ነገር ሲገጥምህ ለምን ብለህ ትጠይቃለህ እንጂ በወሬ መፈታት አይገባህም…” ያለኝ አይረሳኝም፡፡ ልላችሁ የፈለግኩት በአጭሩ ይሉኝታ ቦታ ይበጅለት እንጂ፣ የአገር ህልውናን ሊያሳጣን አይገባም ለማለት ነው። ተግባባን መሰል!

ደላላ ከወዲያ ወዲህ እንደ እንዝርት እየተሽከረከረ ኮሚሽኑን ሲያሳድድ ጆሮው ውስጥ ጥልቅ የሚሉ በርካታ ወሬዎች አሉ፡፡ የሰማነውን ሁሉ እንዘርግፍ ካልን ደግሞ ወሬው ሱናሚ ሆኖ ጠራርጎ ያጠፋናል፡፡ አንዱ የሰማውን መቋጠር የማይችል ደላላ ወዳጄ እየሮጠ መጥቶ፣ “የተባለውን ሰማህ ወይ?” አለኝ፡፡ እኔ ያልሰማሁት ምን ይሆን ብዬ፣ “ምን ተባለ?” በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ “አልሰሜን ግባ በለው…” ብሎኝ፣ “አገሩ አውርቶ የጨረሰውን ምን ተባለ ትላለህ እንዴ?” አለኝ፡፡ አሁን ጆሮዎቼ እንደ አንቴና ተዘረጋጉ፡፡ “ምን ይሆን?” አልኩት፡፡ ለወሬ ማሰፍሰፌን ዓይቶ ነው መሰል ችላ እያለኝ፣ “ለመረጃ ሩቅ ነህ ማለት ነው፡፡ እኔ እኮ ብቃት ያለህ ደላላ ትመስለኝ ነበር…” ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ይኼኔ ውስጤ በንዴት ጋየ፡፡ ይኼ እንኳ ቀን ወጥቶለት እንዲህ ይዘባነንብኝ? ወይኔ አንበርብር ምንተስኖት፡፡ በንዴት ውስጥ ሆኜ፣ “ይኼኔ እኮ የማይረባ ነገር ይዘህ ነው የምትኮፈሰው?” ስለው ሳቀ፡፡ ሳቀ ከማለት ይልቅ እንደ ቄብ ዶሮ አሽካካ ማለት ይቀላል፡፡ ዘንድሮ እህ ብላችሁ ካዳመጣችሁ እኮ ብዙ ነገር ትሰማላችሁ፡፡ መርጦ ማዳመጥ ግን የእኛ ፋንታ ነው!

አሁን የወሬው መቆርፈድ ሳይሆን ሳቁ አበገነኝ፡፡ “እኔ መቼም እንደ አንተ ዓይነት ተራ የመንደር ወሬ ሳሳድድ አልውልም፡፡ ለመንደር ወሬህ ከሆነ የምትዘባነነው ተወው…” ብዬ መንገዴን ስቀጥል ደንገጥ ብሎ ይከተለኝ ጀመር፡፡ “አንበርብር ምን መሰለህ? እኔ እኮ ላናድድህ ሳይሆን እንዴት አልሰማህም ለማለት ነው…” ብሎኝ፣ “ልነግርህ የፈለግኩት ካሁን በኋላ በደላላ አማካይነት የበሬና የበግ ግብይት አይካሄድም፡፡ በግና በሬ ተራ ደላላ ድርሽ እንዳይል መባሉን ልነግርህ ነው…” ሲለኝ ከት ብዬ ሳቅኩበት፡፡ ደንግጦ እያየኝ፣ “ምነው?” አለ፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ጋር ቆሞ ማውራቱ ስለከበደኝ፣ “እንኳን ከበግ ተራ አይደለም ገና ከሰው ተራ ትባረራለህ…” ብዬው መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ነጃሳ! በዓመት ዋዜማ በዓል ነጀሰኝ፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ይህ ሰውዬ እኔን ተከልሎ ሊያሠራጭ ያሰበውን ወሬ አገሩን ሊያዳርስ ነው፡፡ እኔ የእሱ አሸንዳ ወይም ቦይ ሆኜ ወሬውን ስነዛለት በእሱ ቤት ትርምስ ለመፍጠር እየሞከረ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲህም ዓይነት አሉ!

አዛውንቱ ባሻዬ ሰሞኑን ኑሮን በብልኃት ያሉ ይመስላሉ፡፡ ጎረቤቶቻቸውንና ቢጤዎቻቸውን ሰብስበው ላለፉት ሁለት ወራት የቆጠቡትን ገንዘብ ሲቆጥሩ ደረስኩባቸው፡፡ “አንበርብር ቆጥብ ስልህ እምቢ ብለህ ይኼው አርባ ሺሕ ብር ደርሶልናል፡፡ ዓውደ ዓመቱ በአንድ ጊዜ ክፍያ ስለማይቻል በትንሽ በትንሹ ቆጥበን ለበሬ መግዣ ያሰብነውን ለወገኖቻችን ድጋፍ የሚሆን አገኘን፡፡ እዚያ ግሮሰሪ እየሄድክ ገንዘብህን መለኪያ ውስጥ ባትከተው ኖሮ ይኼው ኮራ ብለህ ለወገን ድጋፍ በረከቱን ትካፈል ነበር…” ሲሉኝ አስገረሙኝ፡፡ “ዕድሜ በመደራጀት ነፃነት ሰብሰብ ብለህ ችግርህን በጋራ ትወጣዋለህ፡፡ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው እኛም ወግ ደርሶን ወገኖቻቸንን ባለችን አቅም አለንላችሁ ልንላቸው ነው…” ብለው ሳቁ፡፡ ይኼ ሐሳብ እንዴት እንደመጣላቸው ብጠይቃቸው፣ “አንበርብር ብዙዎች ለወገኖቻቸው የሚያደርጉትን ርብርብ በቴሌቪዥን ካየሁ በኋላ እኛስ ብዬ ተነሳሁ፡፡ አንድ ነገር ተደርጎ ውጤቱ መልካም ከሆነ ልምድ መቅሰም ይሉሃል ይኼ ነው፡፡ ግራ የሚያጋባና ውዥንብር ውስጥ የሚከት የሰው አገር ልምድ ይዘው እየመጡ ከሚያወዛግቡን፣ እንዲህ እንደ እኛ ሰብዓዊነቱን ቢመርጡ የተሻለ ነበር…” ሲሉኝ ቅኔያቸው ገባኝ፡፡ ባሻዬ እንደገና፣ “አንበርብር ትልቁ ቁምነገር ፈጣሪ የሰጠን አዕምሮን በአግባቡ መጠቀም ነው…” አሉኝ፡፡ አይ ባሻዬ አረጁ እንጂ ነገር የገባቸው ነበሩ፡፡ ጠቃሚውን መርጣችሁ ተጠቀሙበት እንጂ አታግበስብሱ ማለታቸው ነበር፡፡ አዕምሮአችንን ከተጠቀምንበት ለወገናችን አለኝታ መሆን እንችላለን ነው ያሉት፡፡ ያኑርልን ብዬ ባርኔጣዬን አነሳሁላቸው፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት