Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርያለንን ማወቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል

ያለንን ማወቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል

ቀን:

በበየነ ሞገስ

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን ወደ እስር ቤት ለመላክ ወያኔ በሚዳዳበት ወቅት፣ ለሥራ ጉዳይ ከመጣ ዲፕሎማት ጋር የሚያገናኝ ሁኔታ አጋጥሞኝ ነበር፡፡ ይህ ሰው የመጀመርያ የኩባ ዝርያ አሜሪካዊ ሲሆን፣ በጨዋታችን መሀል ‹ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአሜሪካ መንግሥት ያለው አመለካከት ምን ይመስላል?› የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ እኔም በልቤ ይጉላላ የነበረውን ስሜት በማውጣት ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ አንተ ትናንት ጽሕፈት ቤታቸው ሄደህ ያነጋገርካቸው ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ባልሠሩት ኃጢያት ነገሮችን እያወለጋገደ፣ ያለው መንግሥት ሊያሥራቸው ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው፡፡

በቅርቡ ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ሁኔታ ተካቷል፡፡ አንብቤዋለሁ አንተም እንደ ተመለከትከው ቅድም ነግረኸኛል፡፡ በዚህ ዘገባ የፕሮፌሰሩንም ሆነ ሌሎች በኢትዮጵያ የሚፈጸሙትን የሰባዓዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች ወገኖቼ በዚህና በመሳሰለው የአሜሪካ መንግሥት አቋም ተገርመናል፣ አዝነናልም የሚል ምላሽ ሰጠሁት፡፡

ሰውዬው ለዚህ ጥያቄ የሰጠኝ መልስ እስከ ዛሬ ከአዕምሮዬ የማይጠፋ ሲሆን ያለኝም፣ ‹አንተም ሆንክ ሌሎች ወገኖች ራሳችሁን አታታሉ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊ መብቱ ተከበረ፣ ረሃብ አቆራመደው፣ ወዘተ. ጉዳዩ አይደለም፡፡ የሰብዓዊ መብት የተባለውም ሆነ ሌሎች ሪፖርቶች፣ እንዲሁም በአሜሪካ መንግሥት ሥር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሽከረከሩት እንደ ዓለም ባንክ፣ የዓለም ፋይናንስ ድርጅት፣ የኤክስፖርት ኢንፖርት ባንክ የመሳሰሉት የፖሊሲው ማስፈጸሚያ መሣሪያዎች እንጂ እናንተንና ለመሳሰሉ አገሮች/ሕዝቦች እንዲጠቅሙ ብለው የተዋቀሩ አይደሉም› የሚል ነበር፡፡

የዚህን ሰው አባባል ዘወትር በአንክሮ የማስታውሰው ሲሆን፣ በይበልጥም ከሦስት ዓመት ወዲህ በአገራችን በተከተለው ክስተት አሜሪካም ሆነች አውሮፓዊያኑ፣ እንዲሁም ‹ታዋቂ› እንላቸው የነበሩ የሚዲያ አካሎቻቸው የሚያደርጉትን ስንመለከት በእውነተኛነቱ የማልጠራጠረው ሆኗል፡፡ አሁንም የሆነውንና የሚደረገውን እንመልከት፡፡ አሜሪካና ኩባንያዎቿ (ከላይ የጠቀስኳቸውን አጋሮቿን ለማለት ነው) የሚናገሩትና የሚሠሩት ለትግራይ ሕዝብ አስበውና ተቆርቁረው የሚመስላቸው አሉ፡፡ በዚህም በአሜሪካ ከተሞች አስፋልት ላይ የሚንከባለሉት የወያኔ አፈ ቀላጤዎች ይህንኑ ያራግባሉ፡፡ ነገሩ ግን ‹እሾህን በእሾህ› እንደሚባለው ከአገራችን የሚፈልጉትን ለማግኘትና እነሱ ሊሠሩ ያልፈለጉትን ቆሻሻ ሥራ ወያኔዎች እንዲፈጽሙላቸው ነው፡፡ በአፈነገጡት ወገኖች በመጠቀምና እርስ በርሳቸው በማዋጋት ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት ዕኩይ ተግባር ነው፡፡

ለትግራይ ሕዝብ አስበው ቢሆንና የሚሠሩት ከሰብዓዊነት የመነጨ ቢሆን ኖሮ፣ ለሁሉም የሚጠቅመው በሁለቱ ወገኖች ሰላም ሰፍኖ፣ በምጣኔ ሀብት የደቀቀውንና እየደቀቀ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም እንዲሰፍንለት ማድረግ ነበር፡፡ ግን ይህ እንዲሆን አይፈልጉም፡፡ ፍላጎታቸው፣ በእየ ዓመቱና በእየ ጊዜው እጃችንን እየዘረጋን የአሜሪካና የሌሎች ምዕራባዊያንን ምፅዋት ጠያቂዎች ማድረግ ነው፡፡

‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል› የሚለው አባባል ኢትዮጵያ ያለችበትንም ሁኔታ ይገልጻል፡፡ የእነዚህ አገሮች ፍላጎት እኛንና በሦስተኛው ዓለም የመደቡን አገሮች ለእነሱ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ አቅራቢ እንድንሆን ሲሆን፣ በዚህም ከእኛና ከመሰሎቻችን የወሰዱትን ጥሬ ዕቃ ለኢንዱስትሪዎቻቸው ግብዓት በማድረግ የተመረቱ ዕቃዎችን ዝንተ ዓለም ተቀባይ ሆነን እንድንቀር ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ላይ የዘመቱት አሜሪካ፣ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በተለይ ከአገራችን የሚፈልጉት ምንድነው? ብሎ መጠየቅ አግባብነት አለው፡፡ ከዚህ ዓለም ከማለፋቸው በፊት ዕውቁ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ኢንጂነር ቅጣው በቪዲዮ በተቀረፀ መልዕክታቸው፣ ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯ የተለያዩና በጣም ጠቃሚ የሆኑ ማዕድናትና ሌሎች ሀብቶችም እንዳላት ገልጸው ነበር፡፡

ኢንጂነሩ ለዚህ አባባላቸው እውነተኝነት ሙያቸው የሚፈቅድ ሲሆን፣ ይህም ሀብት ብዙ የውጭ ኃይሎችን የሚያጓጓ እንደ መሆኑ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ለማወቅ በትምህርትና በምርምር ትኩረት ባለማድረግ በሌሎች ጉዳዮች ተወጥራ ያላትን እንዳታውቅ፣ እንዳትነቃና ጥቅም ላይ እንዳታውል ርብርብ ቢያደርጉ አይገርምም፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለንን ካወቅንና ልንጠቀምበት ከቻልን ምዕራባዊያኑ በፈለጉ ጊዜ ተቀማጭ ሆኖ የሚጠብቃቸው ሀብት ስለማይኖር በዕድገት መንገዳችን ላይ የተለያዩ መሰናክሎችን በመደንቀር ያለ የሌለ ኃይላቸውን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ወያኔን የመሰለ በበታችነት ስሜት ዕድሜ ልኩን ሲሰቃይ የኖረ አካል መልምሎና በጥቅም ደልሎ ማሰማራት ነው፡፡ እየሆነ ያለው ይኼው ነው፡፡

የእኛ ኢትዮጵያዊያን ቀዳሚ ተግባር ሊሆን የሚገባው ያለንን የተፈጥሮ ሀብት ማዕድናትን ጨምሮ ለማወቅ በከፍተኛ ደረጃና አቅጣጫ ጥረት ማድረግና ከድህነታችን ልንወጣበት የምንችለውን ሥልት መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ምን አለን? ምን የለንም? ይህንን በአግባቡ ማወቁ ለዕድገታችን ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ከምሁሩ የሚጠበቀው ከውጭ ለልመና ፕሮጀክት ከማዘጋጀት ይልቅ፣ ያለንን አውቀን በዚህም በልማት ልንሳተፍ የምንችልበትን ፕሮጀክት ማዘጋጀቱ ወደ ታላቅነትና ከልመናም አውጥቶ ራስን ወደ መቻል ሊያሸጋግረን ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የሚሰማው ሁሉም እየተነሳ ‹ያለንን አናውቅም›፣ ለዚህም ነው የውጭ ኃይሎች ያንዣበቡብን ይላል፡፡ ታዲያ ያለንን ለማወቅ ማን ከለከለን? ራስን ማወቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ እዚህ ላይ መበርታት ይኖርብናል፡፡

ያለንን ለማወቅ ምርምር ባለማድረጋችን፣ አገራችን ስላላት ዕምቅ ሀብት ብዙም ሳናውቅ ቆይተናል፡፡ አሁን ያሉን የተለያዩ ቅርሶች እንዴትና በምን ሁኔታ ተሠሩ ለሚለው ራሳችን ለማወቅ ከምናደርገው ጥረት ይልቅ፣ በውጭዎቹ ግኝትና መላ ምት የመተማመን ዝንባሌ ይታይብናል፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በእርሻ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህስ በኩል ከሞፈርና ከቀንበር ያልተላቀቀው እርሻችንን ለመለወጥና ለማዘመን ምን አደረግን? ሴቷ በእንስራ ጀርባዋን እያስቀጠቀጠችና እያጎበጠች ውኃ ከወንዝ ስታመላልስ አለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ከዚሁ ኑሮ የወጣነውና ተማርን የምንለው፣ እንዲሁም በተለያዩ አገሮች በትምህርትም ሆነ በጉብኝት ለመመልከት የቻልነው፣ የመንፈስ ቅናት አድሮብን በተመለከትነው መልክ የአገራችንን ብሎም የገበሬውንና የሴቷን ድካም ለማቃለል ያደረግነው ጥረት ብዙም አይታይም፡፡

አመለካከታችን ከትምህርታችን ይዘት የመጣ ይመስላል፡፡ የትምህርታችን ሥርዓት የራሳችንን እንድንጠላ ወይም እንድንንቅ፣ በአንፃሩ የምዕራባውያኑን እንድናደንቅ አድርጎናል፡፡ ለዚህም ብዙ ምሳሌዎች መስጠት የሚቻል ቢሆንም፣ ሁላችንም በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ክስተቶች በመመልከት መረዳት ይቻላል፡፡ አሁን ትልቁ ጉዳይ የራሳችን የሆነውን ሀብትም ሆነ ታሪክ ማወቅና መረዳት፣ ይህንንም ተተኪው ትውልድ የማያፍርበትን ታሪክ ትተን ማለፍ ነው፡፡ በዚህም ሥሌት የትምህርት ሥርዓቱ እጅግ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል ማለት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ሥራቸውን በዚሁ መልክ በመቃኘት በራሳችን ማንነትና ዕድገት ላይ ሊያደርጉ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...