የኢትዮጵያ ባህርና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ወቅት በኮንቴይነሮች ላይ የደረሰው ጉዳት ከቁጥጥሩ ውጪ (Force Majeure) በመሆኑ፣ ተጠያቂ ሊሆን እንደማይችልና ካሳ እንደማይከፍል አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ዕቃ ይዘው የነበሩ 252 ኮንቴይነሮች በአሸባሪነት በተፈረጀው ሕወሓት ታጣቂ ቡድን ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል።
ኮንቴይነሮቹ ከውጭ የገቡ ማሽኖችን፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን፣ ምግብና መድኃኒቶችና ሌሎች የደንበኞች ዕቃዎችን የያዙ ነበሩ።
‹‹ኮንቴይነሮቹ የተለያዩ ዕቃዎችን ይዘው ነበር። በተጨማሪም የራሳችን ቢሮዎችና ንብረቶች ወድመዋል። ችግሮቹ ከቁጥጥራችን ውጭ የተፈጠሩ ስለሆኑ ካሳ መክፈል አንችልም። ነገር ግን ጉዳቶቹን ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር ሆነን በጋራ እያጠናን ነው፤›› ብለዋል።
ኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ከሞጆና ከቃሊቲ ቀጥሎ ትልቁ ደረቅ ወደብ ሲሆን፣ ለሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ዋነኛው የወጪ ንግድ ማዕከል ነበረ። ድርጅቱ በመቀሌም ደረቅ ወደብ ያለው ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት ማንቀሳቀስም ሆነ ስላለበት ሁኔታ መናገር ባይቻልም፣ ከኮምቦልቻ የተለየ ዕጣ ፈንታ ይኖረዋል ተስፋ እንደሌለ ጠቁሟል፡፡
የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ በዓመት እስከ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ገቢ ያስገኝ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ዓመት ግን ገቢው ሊያሽቆለቁል እንደሚችል አቶ ሮባ ጨምረው ገልጸዋል።
ለአንድ ዓመት በነበረው ጦርነት በንብረትና በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ መንግሥት ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው መመለስ እንዴት እንደሚቻል ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።